Connect with us

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ
ብልጽግና ፓርቲ

ዜና

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከታህሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየዉን መደበኛ ስብሰባ አጠናቋል፡፡

ኮሚቴዉ በሰላም፣ በልማት፣ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና መጪዉን አገራዊ ምርጫ በተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በዋናነት ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በአገራችን የታየዉ ለዉጥ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፈተናዎችን ተጋፍጦ የአገራችንን ብልጽግና እዉን ለማደረግ ሰፊ እድል የፈጠረና አገራችንን ከብተና አደጋ ያዳነ መሆኑ በዉይይቱ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

በተለይም ብልጽግና  ዉሁድ ህብረ ብሄራዊ አገራዊ ፓርቲ ሆኖ መደራጀቱ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ከፍተኛ እድል ከመፍጠሩም በላይ ከአገሪቱ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ተገለዉ የዳር ተመልካች የነበሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማቀፍና ለማሳተፍ የቻለ የመጪዉ ትዉልድ ፓርቲ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በአገራዊ ለዉጡ የተገኙ ድሎችን ጠብቆ በማስቀጠል ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን ለዚህም የፓርቲዉን መርሆዎች፣ እሴቶችና አሰራሮችን በጥብቅ ዲሲፕሊን ተግባራዊ ማድረግና ጠንካራ ተቋማዊ ባህል መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ኮሚቴዉ በሁለቱ ቀናት መደበኛ ስብሰባዉ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡

  1. አገራችንን ለመበታተን በከፍተኛ ሁኔታ ሲዘጋጅ ቆይቶ ፍጹም አረመኔያዊ በሆነ መልኩ በአገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ስግብግብ ጁንታ በአጭር ጊዜ እንዲፈርስና አገራችን ከዚህ ከሃዲ ሃይል ነጻ እንድትወጣ ጀግናዉ መከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራና አፋር ክልሎች ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ድጋፍ ላደረጉ መላዉ የሀገራችን ህዝቦች ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ጀግንነት ልምዳችን ስለሆነ በዚህ ድል ሳንኩራራ ይህንን አገራዊ የአንድነት ስሜትና ቁርጠኝነት በሌሎች የልማት ዘርፎችም በመድገም የአገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ ርብርብ እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
  2. የወንጀለኛዉን ከሃዲ ጁንታ አባላት ከተደበቁበት አድኖ ለፍርድ ለማቅረብ ከሚደረገዉ ርብርብ ጎን ለጎን በህግ ማስከበር እርምጃው ሂደት ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬያቸዉ ተመልሰዉ እንዲቋቋሙና እብሪተኛው ጁንታ ያፈራረሳቸዉ የህዝብ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ተጠግነዉ ለአገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የተጀመረዉ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በትግራይ ክልል የህዝብ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፣ የእለት ደራሽ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለማድረስና ህብረተሰቡ ወደ መደበኛ የእለት ተእለት ህይወቱ እንዲመለስ በሚደረገዉ ርብርብ ዉስጥ የፓርቲዉ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የአገራችን ህዝቦች   የቻሉትን አስተዋጽዖ ሁሉ እንዲያደርጉ ኮሚቴዉ ጥሪ ያቀርባል፡፡   
  3. በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስትና ብሄረ መንግስት ግንባታ ሂደት የተለያዩ የፖለቲካ ሃይል አሰላለፎች የሚታዩበት ነዉ፡፡ በአገራችን የሚታየዉን ዉስብስብ ብዝሃነት የሚያስተናግድ አገራዊ አንድነት ከመገንባት አንጻር በወንድማማችነት እሴት ላይ የተመሰረተ ህብረብሄራዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ የፌዴራል ስርዓት ግንባታ እዉን እንዲሆን የፓርቲያችን አመራሮችና አባላት በቁርጠኝነት እንዲታገሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
  4. በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቦች የሚያነሷቸዉ የማንነት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸዉ ፍትሃዊ የህዝብ ጥያቄዎች መሆናቸዉን ኮሚቴዉ ያምናል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ነባራዊ ሁኔታዉን መሰረት በማድረግ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲሁም የህዝቡን ነጻ ፍላጎት ከግምት ባስገባ መልኩ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ምላሸ እንዲሰጣቸዉ ኮሚቴዉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
  5. በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ተገቢዉ እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ኮሚቴዉ ከስምምነት ደርሷል፡፡ እነዚህን እኩይ ተግባራት የሚፈጽሙ የጥፋት ሀይሎች በቁጥጥር ሥር ለማዋልና እርምጃ ለመዉሰድ በሚደረገዉ ርብርብ በየደረጃዉ የሚገኙ የብልጽግና አመራሮች በከፍተኛ ጽናትና ቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
  6. የአገራችንን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች በየትኛዉም ቦታ የሚገኙ የብልጽግና አመራሮችና አባላት ከሚለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች ወጥተዉ ከፍ ያለ አገራዊ እይታ በመያዝ ኢትዮጵያንና የሁሉንም ዜጎቿን ሁለንተናዊ ብልጽግና እዉን በሚያደርግ መልኩ እንዲደጋገፉ፣እንዲረዳዱ፣በአብሮነትና በትብብር መንፈስ መስራት እንደሚገባቸዉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
  7. በ2013 ዓ.ም የሚካሄደዉ ምርጫ አገራችን ወደ እዉነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለምታደርገዉ ሽግግር ያለዉ ትርጉም እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል፡፡ የሚካሄደዉ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና በሂደቱም ሆነ በዉጤቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የብልጽግና አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
  8. ብልጽግና  ፓርቲ በመጪዉ ምርጫ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ በዉጤታማነት እንዲያጠናቅቅ በፓርቲዉ ማኒፌስቶ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ አጽድቆታል፡፡ መላዉ የፓርቲዉ አመራሮችና አባላት የጸደቀዉን ማኒፌስቶ መሰረት በማድረግ አስፈላጊዉን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
  9. በአገራችን በህጋዊ መንገድ ተመዝግበዉ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ እዉነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመሸጋገር የተወሰዱ የአገራዊ ለዉጥ እርምጃዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መጪዉ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና በሂደቱም ሆነ በዉጤቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸዉን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡   
  10. መላዉ የአገሪቱ ህዝቦች ባለፉት ሁለት ተኩል አመታት በኢትዮጵያ የታዩ ለዉጦችና የተገኙ ድሎች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ፣መጪዉ አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ እንዲጠናቀቅና  የዜጎች ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት ጠንካራ አገር ለመገንባት በሚደረገዉ ርብርብ ዉስጥ የሚጠበቅባቸዉን አስተዋጽዖ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ብልጽግና ፓርቲ

ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top