Connect with us

#አርፈዋል!

አንጋፋው የኪነ ጥበብ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለዩ።
Photo: Social media

ዜና

#አርፈዋል!

#አርፈዋል!

አንጋፋው የኪነ ጥበብ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለዩ።

( ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ)

አንጋፋው የቴአትር ምሁር፣ ደራሲና ተርጓሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ “የመጨረሽታ መጀመርታ”- የተሰኘ ታሪክና ህይወት ቀመስ ሽሙጥ ልቦለድ መፅሀፍ በቅርቡ ለንባብ አብቅተው ነበር፡፡ ደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሄርንና ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማን ማዕከል አድርጎ የተፃፈው ልቦለድ፤ የሁለቱን ሰዎች ህይወትና ታሪክ በቀልድና ጨዋታ አዋዝቶ የሚያስቃኝ ነበር።

ከትወና በተጨማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ከዚህ ቀደም የኡመር ኻያምን ሩቢያቶች የግጥም መድበል ጨምሮ በርካታ ድርሰቶችን፣ ትርጉሞችንና የተውኔት ፅሁፎችን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል።

በቅርቡ መስከረም 17 / 2013 የ84ኛ የልደትና የክብር በዓል ያዘጋጀላቸው ወዳጄ Getachew Alemu  እንደገለፀልኝ ጋሽ ተስፋዬ ሌሊት ነው ህይወታቸው ያለፈው። ኮሚቴ ተዋቅሮ የክብር አሸኛኘት እንዲደረግላቸው እየተሰራ መሆኑንም አረጋግጦልኛል።

—— 

ለትውስታ ጋሽ ተስፋዬ ከጀርመን ድምፅ ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ እነሆ

—–

በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ቴሌቭዝንም በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ቀደምትና አሉ በሚባሉት በብሔራዊ ትያትርና በአገር ፍቅር ትያትር ብሎም በአዲስ አበባ ዬንቨርስቲ የባህል ማዕከል በኃላፊነት ሰርተዋል። ለሠላሳ ዓመታት ደግሞ በመምህርነት አገልግለዋል። በአዲስ አበባዉ የዩንቨርስቲ ኮሌጅ በ22 ዓመታቸዉ ትምህርታቸዉን ሲያጠናቅቁ ሕግ ባለሞያ ለመሆን ትምህርታቸዉን ለመቀጠል አስበዉ ነበር። ነገር ግን በወጣቱ  በተስፋዬ ገሰሰ የመድረክ ጥበብ የተማረኩት ጃንሆይ ወጣቱን ተስፋዬን ጠርተዉ አነጋገሩት በሥራዉን አመሰገኑት የነፃ ትምህርት እድል እንዲያገኝ ትዕዛዝ አስተላለፉ፤በትያትር፤ 

« ልክ ነዉ። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪ በሆኑኩበት ጊዜ በ1950 ዓ,ም የአራተና ዓመት ትምህርቴን አጠናቅቄ ነበር። ትምህርቴን እንደጨረስኩ ተመራቂዉ ክፍል ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመተባበር፤  « እዮብ » የተባለ ትያትር አዘጋጀን ያኔ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትያትር ከተከፈተ ሁለት ዓመቱ ነበር ይህ ትያትር በ 1948 ዓ,ም እንደተከፈተ ይታወሳል። ያንን ትያትር ወስደን  በአዲሱ ትያትር ቤት አሳያየነዉ። እኔ መሪ ተዋናዩን ሆኜ ይህን ትያትር የሰራሁት 1950 ዓ,ም ነዉ። እኔ ደግሞ በዚህ ትያትር መሪ ተዋናዩን እዮብን ሆኜ ነበር የተጫወትኩት። ይህን ትያትር ጃንሆይ ከዘመዶቻቸዉ ከሹማምንታቸዉ ጋር ሆነዉ ተመልክተዉ በጣም ተደሰቱበት ። እናም በማግስቱ ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥታቸዉ አሁን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ወደ ሆነዉ ጠሩኝ። በዝያን ግዜ ጃንሆይ የትምህርት ሚንስቴሩንም የያዙት እሳቸዉ ነበር። እና ጃንሆይ ቢሮአቸዉ ጠርተዉኝ ሁድኩ

ለጥ ብዩ እጅ ነሳሁ፤ እናም እሳቸዉም በአፀፋዉ ኦ መድረክ ላይ ሳይህ ትልቅ ትመስለኝ ነበር፤ ለካስ አጠር ያልክ ነህ አሉ እንደመቀለድ ብለዉ፤ ያዩት ትያትርን መዉደዳቸዉና ምን እንደምማር ጠየቁኝ፤ ያኔ እንዳልካቸዉ መኮንን ምክትል ሚንስትራቸዉ ነበር፤ እና እሱም እዛዉ ነበር፤ ሕግ እንደምማርና የነጻ ትምህርት እድልን አንግቼ ወደ ፈረንሳይ ሃገር እንደምሄድ ስገልጽላቸዉ ለእንዳልካቸዉ መኮንን ምን ያሕል ሕግ የሚማሩ ሰዎች አሉን ብለዉ ጠየቁ፤ አንድ አስራ ሁለት ሰዉ ነዉ አለ። ጃንሆይ በበኩላቸዉ ፤ ታድያ አስራ ሁለት ሰዉ አይበዛም ለህግ ምናለ ይህ ልጅ ሄዶ ትያትር ቤትም በስማችሁ ተከፍቶአል ፤ ኦፔራዉ በዚህ መስክም የተማሩ ሰዎች ያስፈልጉናል አሉ። እኔንም ምን ታስባ,ህ ሲሉ ጠየቁኝ እኔም ለጥ ብዬ እጅ ነሳሁ ንጉስ የፈቀደዉን ነገር እንቢ ማለት አይቻልም። በሉ የሚማርበት ቦታ ይፈለግለትና የፈለገዉ ሃገር ሄዶ እንዲማር ብለዉ ትዕዛዝ ይሰጡታል ፤ አደ አሜሪካ ሃገር ተጻጽፎ «North western university» የሚባል ከፍተኛ ተቋም እንድማር ተደረገ።  ከዝያን እዝያ ተቅዋም ዉስጥ የትያትር ጥበባት ሞያን በሁለት ዓመት ዉስጥ ቀስሜ ወደ ሃገሪ ተመልስኩ። ጃንሆይ በእኔ ላይ ትልቅ የህይወት ለዉጥ ነዉ ያደረጉት፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ነዉ ብዩ የማስበዉ፤ ትልቅ ነገር ነዉ፤ ምክንያቱም የምወደዉ ሞያ ነዉ። በትወናም በአዘጋጅነትም በማስተባበርም በመምህርነትም ስሰራ እስከዛሬ ቆይቻለሁ።»       

ረጅም የትያትር ጥበባት ተሞክሮአቸዉን የሚተርኩት ተባባሪ ፕሮፊሰር ተስፋዬ ገሰሰ እኔ አሉ እኔ  ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት ከዝያም እስከ አዛዉንት እድሜዬ ባየሁትና በታዘብኩት መሰረት የመድረክ ጥበባትም ልዩ ልዩ ለዉጦችና እድገቶች እያሳዩ የአለንበት ደረጃ ደርሰዋል። 

ጋሽ ተስፋዩዬ እንግዲህ ለወጣቱ በተለይ ደግሞ በሞያዎ በትያትር ጥበባቱ ምክሮ ምንድን ነዉ?

ረዳት ፕ/ር ተስፋዬ ገሠሠ በበርካታ ተውኔቶች ላይ ተውነዋል፤ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ትርጉም ሐምሌት፣  የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ፤ የእሾህ አክሊል ፤ ቴዎድሮስ

እንዲሁም በመንግስቱ ለማ “ፀረ ኮሎኒያሊዝም ” የተሰኙት በድንቅ አጨዋወት ከሰርዋቸዉ ተውኔቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲም አሁንም ድረስ በቲያትር መምህርነት የሚያገለግሉት፤ ተባባሪ ፕሮፊሰር ተስፋዬ ገሰሰ የአንድ ሴት ልጅና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸዉ። የልጅ ልጆችም አልዋቸዉ። ተባባሪ ፕሮፊሰር ተስፋዬ ገሰሰን ለሰጡኝ ቃለምልልስ እያመሰገንኩ ጤና ደስታን በዶቼ ቬለና በባልደረቦቼ ስም እመኛለሁ።

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top