#ሕገመንግስቱ ግለሰቦችንና ዜጎችን አግላይና አዋካቢ ስለሆነ ይፈተሽ
(ሙሼ ሰሙ)
እንደ መነሻ
ተቃርኖ 1 ሉዐላዊ ማን ነው ምንድንስ ነው?
አንቀጽ 8: የሕዝብ ሉዓላዊነት
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 8 ላይ ሁለንተናዊ ሉዕላዊነትን የሚያጎናጽፈው ለብሔር ብሔረሰቦች ነው። ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እንደሆነ ይደነግጋል።
መለስ ብሎ ደግሞ ብሔሮች ልዩ መገለጫቸው ከሆነው ግለሰብ ውጭ በራሳቸው ስለማይቆሙ አንቀጽ 38 ላይ የሉዕላዊነት ዋነኛ መገለጫ የሆነውን በዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ተወካዮችን የመምረጥና የመመረጥ መብትን ለዜጎች ይሰጣል።
እርግጥ ነው፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በኑባሬ ገዝፈው እንደ ዜጋ ለመምረጥና ለመመረጥ የሚችሉት የብሔሩ አባላት አንጎል በአንድ ላይ ታጭቆ፣ የግለሰብ ሲሆንና እንደ ግለሰብ ሲያስቡ ብቻ ነው።
ተቃርኖ 2 ከብሔርና ክልል ውክልና ውጪ ኢትዮጵያዊ ብቻ ስለመሆን
አንቀጽ 6 ቁጥር 2 ላይ “የውጭ ሀገር ዜጎች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ ይላል። የብሔር ውክልናቸው ግን አያወሳም።
በቅጡ ላጤነው እንደ እንቁላሉና ዶሮዋ ዓይነት ሙግት ነው።
ያለ ክልልና ብሔር ቅድመ ውክልና ኢትዮጵያዊነትን የማይቀበለው ሕገ መንግስት የውጭ ሀገር ዜጎችን እንዴት ይስተናግዳል? ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ሉዕላዊነታቸውስ በምን ይገለጻል? ከሚቀርብላቸው የብሔር ዝርዝር ውስጥ አንዱን በመምረጥ ብሔርን ይቀላቀላሉ ወይስ በራሳቸው ስም የሚጠራ ልዩ ሉዕላዊ ብሔር ይሆናሉ።
ለውጭ ሀገር ዜጋ በውልደት ሳይሆን “በይሁንታ” ብቻ ያለ ብሔርና ክልል መገለጫና ውክልና ኢትዮጵያዊ መሆን ከተቻለ በደሙ ኢትዮጵያዊ የሆነውንስ ያለ ብሔርና የክልል ውክልና ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆንን ሕገ መንግስቱ ለምን ይነፈገዋል?
ተቃርኖ 3 “ለራስ ምስክርነት ራስን በራስ መጥቀስ”
አንቀጽ 8: የሕዝብ ሉዓላዊነት አስመልክቶ ሕገ መንግስቱ
- የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡
- ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫቸው ነው፡፡ ይላል።
ነብይነቱን ለማረጋገጥ ልዩ መገለጫ አድርጎ የራሱን ድርሰት በምስክርነት እንደሚያቀርበው የዘመኑ “ዘመናይ ነብይ” ዓይነት ሕገ መንግስቱም ብሄሮች ሉዐላዊ መሆናቸውን ራሱ አውጆ፣ ማረጋገጫና ምስክር ሲፈልግ ደግሞ፣ ዘወር ብሎ እራሱን በራሱ ይጠቅሳል። ይህ እንግዲህ የለየለት ተጨፈኑ ላሞኛችሁ መሆኑ ነው።
ተቃርኖ 4 ለሕገ መንግስቱ ተገዢና አክባሪ ብሔር ወይስ ዘውጌ
አንቀጽ 9: የሕገ መንግሥት የበላይነት ቁጥር 2 ላይ
“ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡” ይላል።
የሀገራችን የአፈጣጠር ትርክት መነሻና መድረሻ የተደረጉትና የሕገ መንግስቱ ልዩ መገለጫ የሚባሉት ብሔሮችና ብሔረሰቦች በሕገ መንግስቱ የበላይነትና ተገዢነት ዙርያ አንዳችም ኋላፊነት ሆነ ተጠያቂነት የለባቸውም። ብሔሮች ሕግ ቢጥሱ፣ ቢያፈናቅሉ፣ ቢያሰድዱና ግፍ ቢፈጽሙ ሕግ አያግዳቸውም።
በሕገ መንግስቱ ውስጥ የብሔርና ብሔረሰቦች ተቀጥላ ሆነው የሚቀርቡት ዜጎች ግን በሕገ መንግስቱ የበላይነትና ተገዢነት ዙርያ ቀዳሚ ተጠርጣሪ ስለሆኑ ሉዐላዊነታቸውን እውቅና የነሳው ሕገ መንግስት ጣቱን ዜጎቹ ላይ መቀሰሩ “taxation with out representation ” ነው። No more pseudo representation.