የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሕዝብ እያወያየ ነው
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተደዳር ከዛላንበሣ፣ ከውቅሮ፣ ከአዲግራት እና እዳጋ ሐሙስ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄደ፡፡
በመቀሌ ከተማም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር መክሯል።
በውይይቱም ነዋሪዎቹ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮሚቴ አባል አቶ ሃብታይ ገብረ ማርያም እንዳሉት፤ ውይይት በተደረገባቸው ሁሉም አካባቢዎች የመንግሥት ተቋማት ወደ ስራ ገብተው አገልግሎት እንዲሰጧቸው ጥያቄ ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ‘የጤና ተቋማት፣ የመብራት፣ የቴሌኮምና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት በአፋጣኝ ሥራ ይጀምሩልን’ የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት መነሳታቸውን ተናግረዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በከተሞችም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች ፈጥኖ መዋቅሩን በመዘርጋት ህዝቡ ሰላሙ ተጠብቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ጠይቀዋል።
የህወሓት ጁንታ በመንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻ ከተወገደ በኋላ ሕዝቡ በፍትሃዊነት የሚያስተዳድረው አካል እንደሚፈልግ መጠየቁንም ገልጸዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሳባ ገብረማርያም በበኩላቸው በመጪዎቹ ቀናት ቅድሚያ በከተሞች ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎችን በማቋቋም የሕዝቡ ጥያቄዎች በሂደት እንዲፈቱ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ህዝቡን በማወያየት ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።
በተያያዘም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በመቀሌ ከተማ ከአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር በመቀሌ ከተማና አጠቃላይ በክልሉ መልሶ ግንባታ፣ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ የማስፈን ጉዳይ ትኩረት አድርገውበት መክረዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግና የልማት ተግባራትን ለማስቀጠል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ዶክተር ሙሉ ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አጠቃላይ ወጣቶችና ሴቶች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙም ጠይቀዋል።
በመቀሌ ከተማ በየደረጃው ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎችን በአጭር ጊዜ በማቋቋም የሕዝቡን የአገልግሎትና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት እንደሚሰራም ዶክተር ሙሉ አረጋግጠዋል።(ኢዜአ)