መከላከያ ሠራዊት ለመጨረሻው ምዕራፍ ትዕዛዝ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ
መንግሥት ለሕወሓት አመራሮችና ታጣቂዎች የሰጠውን የ72 ሰዓት እጅ መስጠት ማስጠንቀቂያ ተከትሎ መቀሌ ከተማን የከበበው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለሦስተኛውና ለመጨረሻው ምዕራፍ በተጠንቀቅ ቆሞ ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት ማክሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ሠራዊታችን የሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ ነው፡፡ በእስካሁኑ ጉዞው ሁለቱን ምዕራፎች በድል ቋጭቷል፤›› በማለት፣ ‹‹ውጊያ ‹ባህላዊ ጨዋታ› ሳይሆን ፍትሐዊነት፣ ጀግንነት፣ የአዕምሮ ብስለትና ሕዝባዊ ኃላፊነት መሆኑን በተግባር አሳይቷል፤›› ሲልም አስረድቷል፡፡
‹‹ሠራዊታችን በአሁኑ ሰዓት ለሦስተኛው ምዕራፍም በተጠንቀቅ ቆሞ ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፤›› ሲል መግለጫውን አጠቃሏል፡፡
የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ የሕወሓት ታጣቂ ኃይል በማይካድራ የፈጸመውን ዓይነት ጭፍጨፋ በመቀሌ ለመድገም ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የሕወሓት የጥፋት ኃይል ያሰበው ሴራ እየከሸፈበት ነው፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ የጥፋት ዕቅድ ማውጣቱን ደርሰንበታል፤›› ብለዋል፡፡ ይህንንም ድርጊት ለመፈጸም ልዩ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡
እሑድ ኅዳር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ በትግራይ ክልል የተጀመረው የሕግ ማስከበር ሁለተኛው ምዕራፍ መጠናቀቁንና የሕወሓት አመራሮች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የ72 ሰዓት መሰጠቱን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት የሁለተኛውን ምዕራፍ መቋጯ ያደረገው መቀሌ ከተማን በ50 ኪሎ ሜትር ከበባ ውስጥ በማድረግ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሠራዊቱ በዳንሻ፣ በሑመራ፣ በሽሬ፣ በሽራሮ፣ በአክሱም፣ በአድዋ፣ በአዲግራት፣ በአላማጣ፣ በጨርጨር፣ በመሆኒ፣ በኮረምና በሌሎችም ቦታዎች በወሰደው ዕርምጃ ሕዝብ እየታደገና ድል እያደረገ መቀሌ ዙሪያ መድረሱ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ከመንግሥት ጎን በመሆን፣ የሕወሓት አመራሮችን ለፍርድ ለማቅረብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹በጀመርነው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ቁልፍ ተዋንያን እንድትሆኑ፣ ከሠራዊታችን ጎን በመሆን የዚህን የክህደት ቡድን አባላት ለፍርድ በማቅረብ ወሳኝ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡
ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር በጽሑፍ መልዕክት አቋማቸውን ማስታወቃቸው የተገለጸው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ እጅ መስጠት አይሞከርም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደ ዘገበው፣ ርዕሰ መስተዳድሩ እስከ መጨረሻው ድረስ እሳቸውም ሆኑ ድርጅታቸው እንደሚፋለሙ ተናግረዋል፡፡
በአክሱም ከተማ በሚገኘው ኤርፖርትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱ የተነገረለት ሕወሓት፣ መቀሌ ከተማንም ተመሳሳይ ዕጣ እንዲገጥማት ሊያደርጋት ይችላል የሚለው የብዙዎች ግምት ነው፡፡ በአክሱም ኤርፖርትና በስድስት ድልድዮች ላይ የተፈጸመው የማፈራረስ ድርጊት፣ በመቀሌም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የኅብረት ዘመቻ መምርያ ኃላፊ ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ሰሞኑን በሰጡት ማብራሪያ፣ የሠራዊቱን ከባድ ምት መቋቋም ተስኖት የሸሸው የሕወሓት ኃይል፣ የአክሱም ኤርፖርትን በዶዞር ማፈራረሱን ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ አክሱምና አካባቢውን ሲቆጣጠር ነዋሪዎች ደስታቸውን በመግለጻቸው ምክንያት በብስጭት እንዳደረገው አክለዋል፡፡ ‹‹ነዋሪዎች ደስታቸውን ከመግለጽ ባለፈ ሠራዊቱን እንዲወጉበት ያስታጠቃቸውን መሣሪያ በነቂስ በማውጣት ለሠራዊቱ አስረክበዋል፤›› ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸው፣ ሠራዊቱ ባስለቀቃቸው አካባቢዎች የትግራይ ሕዝብ ተመሳሳይ ስሜት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብዓዊ ቀውሱ የከፋ እንዳይሆን የሚሠጉ ወገኖች፣ በተለይ በመቀሌና በዙሪያው ሊካሄድ በሚችለው ውጊያ ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ እያሳሰቡ ነው፡፡ መንግሥት በበኩሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ በከፍተኛ ጥበብና ትዕግሥት ሦስተኛውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማጣሪያ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት የሰጠውን የ72 ሰዓት በመጠቀም፣ እጅግ በርካታ የትግራይ ሚሊሻዎችና የልዩ ኃይል አባላት በየግንባሩ እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ገልጿል፡፡
በአፋር ክልል በኩል ብዙዎች ገብተው እጅ የሰጡ መሆኑን፣ በማይፀብሪ ተቆርጦ የቀረው ኃይል ደግሞ እጁን በሰላም በመስጠት ላይ እንደነበር በመግለጫው ተገልጿል፡፡
ጥሪውን ሰምተው እጅ በመስጠት ላይ ለሚገኙ የትግራይ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ለሕዝብ በማሰባቸው መንግሥት ምሥጋና ማቅረቡን ጠቁሞ፣ በተፅዕኖ ውስጥ ሆነው እጅ መስጠት ላልቻሉት በያሉበት ትጥቃቸውን ፈተው መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት እስኪደርስላቸው እንዲጠብቁ በአፅንኦት ማሳሰቡን አስታውቋል፡፡ (ምንጭ፡- ሪፖርተር)