የፓርላማ አባላቱ በኤጄንሲው አሰራር አልተደሰቱም
– የአሰራሩ ያለመዘመን የሀገሪቱን ገጽታ እንዳያበላሽ ሰግተዋል፣
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን የኢሚግሬሽን፣ ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጄንሲን በጎበኘበት ወቅት፤ በኤጄንሲው ምክንያት የሀገሪቷ ገጽታ መበላሸት እንደሌለበት አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ያሳሰበው፤ የተገልጋዮች ሰልፍ የሚፈጥረውን ግርግር እና ወረፋ በመጠበቅ የሚከሰተውን መጉላላት በመስክ ምልከታ ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦሌ ዓለም-አቀፍ አየር ማረፊያ ተርሚናል እና በአራት ኪሎ የሚገኙትን የኤጄንሲውን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ተዘዋውሮ የጎበኘው ኮሚቴው፤ ኤጄንሲው የአሠራር ስርዓቱን በማዘመን፣ ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ጥረትም በአድናቆት ተመልክቷል፡፡
በቦሌ ተርሚናል በሚገኘው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት የደንበኞችን መዳረሻ ለማዘመን ኤጄንሲው የተሻለ መንቀሳቀሱን ያረጋገጠው ቋሚ ኮሚቴው፤ አራት ኪሎ በሚገኘው ቅርንጫፍ ደግሞ የሠራተኛው ቁጥር እና የአገልግሎት ፈላጊው ብዛት ባለመመጣጠኑ፣ ደንበኞች ለእንግልት እና አላስፈላጊ መጉላላት እየተጋለጡ መሆኑን በአንጻሩ ታዝቧል፡፡
በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ሠራተኞች የደንብ ልብስ፣ የመጓጓዣ፣ የደመ-ወዝ እና የጥቅማ-ጥቅም ችግሮች እንዳሉባቸው መረዳቱን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው፤ አራት ኪሎ በሚገኘው ቅርንጫፍ ግን የተጠናከረ ፍተሻ እንደሌለ እና ኮቪድን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የፊት እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲሁም የሳኒታይዘር አጠቃቀም ውስንነት መኖሩን አመላክቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው አሠራሩን በማዘመን፣ ደንበኞችን በበይነ-መረብ በማገልገል፣ አለአስፈላጊ ሰልፍ እና መጉላላት ለመቅረፍ የሄደበትን ርቀት አወድሰዋል፡፡
የኤጄንሲውን ሥራ የበለጠ ለማጠናከር በትምህርት ዝግጅት፣ በዕውቀት እና ክህሎት ብቁ ባለሙያዎች መቀጠር እንዳለባቸው ያሳሰቡት የተከበሩ ነገሪ፤ በተቋሙ የሚገኙ ሠራተኞች 80 በመቶ የትምህርት ደረጃቸው ከዲግሪ በታች ሆኖ እንዴት እንደተቀጠሩ ግልጸኝነት የጎደለው አዝማሚያ ስላለ፤ የኋላ ታሪካቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸው እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ከወቅታዊ የሀገሪቱ ፀጥታ አንጻር መፈተሽ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የኢሚግሬሽን፣ ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በበኩላቸው፤ የሠራተኞችን ደመ-ወዝ እና ጥቅማ-ጥቅም በተመለከተ ኤጀንሲው ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች በተሻለ ሁኔታ ክፍያ የሚፈጽም መሆኑን ገልጸው፣ የደንብ ልብስን እና የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ የሠሩበት ሰዓት ተመዝግቦ ክፍያ የሚፈጸም መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በብልሹ አሠራር እና በኪራይ ሰብሳቢነት የተጠረጠሩ 13 የኤጄንሲው ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው መባረራቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ ተገልጋይ የሚፈልገውን አገልግሎት ሰጥቶ ከመሸኘት አንጻር አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ግን አምነው፣ በክፍተት ተቀብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አጠቃላይ ግብረ-መልስም፤ ከላይ የተጠቀሱት ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ የራሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ አለማዘጋጀቱ፣ በደንብ እና መመሪያ መሠረት ወደ ተግባር አለመግባቱ እንዲሁም የበይነ-መረብ ቪዛ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ለደንበኞች ግንዛቤ አለመፈጠሩን በዕጥረት አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር እና ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር በቋንቋ ተግባብቶ አግልግሎት ከመስጠት አንጻር ውስንነት መኖሩንም ቋሚ ኮሚቴው በክፍተት ጠቁሞ፤ ኤጄንሲው በአጠቃላይ የሀገሪቷን ገጽታ የሚያበላሹ አሠራሮችን በአስቸኳይ ማስተካከል እንዳለበትም አሳስቧል፡፡(የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ድረገጽ)