ደገመው!
(ኢንጅነር ጌታሁን ሄራሞ)
ቢቢሲ በጁላይ 1 2021 ዘገባው የዓለም አቀፍ የደህንነት ተንታኞችን በመጥቀስ ጄኔራል ፃዲቃን ገብረ ትንሳኤን “one of the finest military strategists of his generation in Africa” በማለት ማሞካሸቱ ይታወሳል።
ታዲያ ከ6 ወራት በፊት በአፍሪካ ረቂቁ የጦር ስልት አዋቂ እንደሆነ የተነገረን ጄኔራል ፃዲቃን ከበረሃ በDW TV ቀርቦ ለወቅቱ ሽንፈት በምክንያትነት ያስቀመጠው የኢትዮጵያ ጦር የድሮን ትጥቅን ነበር።
ዛሬ ከሰዓታት በፊት በቢቢሲ የአማርኛ ዜና ድረ ገፅ ላይ በተለቀቀው ቃለ መጠይቅ ጄኔራል ፃዲቃን ስለ ትግራይ ጦር ማፈግፈግ በጋዜጠኛው ጠበቅ ተደርጎ ሲጠየቅ ለሁለተኛ ጊዜ አሁንም ድሮኗ ሰበብ እንደሆነች በድጋሚ ተናግሯል። ጋዜጠኛው “የድሮን ጥቃት መቋቋም አለመቻላችሁ ነው ወደ ትግራይ እንድትመለሱ ያደረጋችሁ፤ አይደለም እንዴ?” በማለት በጠየቀው ጊዜ ጄኔራል ፃዲቃን የመለሰው እንደዚህ በማለት ነበር፦
“ያ አንድ ምክንያት አይደለም አልልህም። ነገር ግን ብቸኛው ምክንያት አይደለም። ወደ አዲስ አበባ በምንገሰግስበት ጊዜ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሂደቶች ከወታደራዊ አካሄዳችን ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም። የዲፕሎማቲክ ሁኔታዎች በሚፈለገው መልኩ እየሄዱ አልነበሩም። ይህም አንድ ምክንያት ነበር።
በተለይ ግዙፍ ሠራዊታችንን በስንቅና ትጥቅ ሙሉ ለማድረግ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ረዥም ርቀት በሚጓዙበት ጊዜ ለድሮን ጥቃት ተጋልጠው ቆይተዋል። በዚህም ድሮኖቹ በግብአት አቅርቦታችን ላይ ተጽእኖ ፈጥረዋል።”
ልብ በሉልኝ እንግዲህ ፦ ከ6 ወራት በፊትና ዛሬም ድሮኗ ለሽንፈቱ በሰበብነት ተጠቅሳለች። ተሽከርካሪዎቻቸው ረዥም ርቀት በሚጓዙበት ወቅት ለድሮን ጥቃት እንደተጋለጡም አብራርቶልናል። እኔ የውትድርና ጥበብ ተንታኝ አይደለሁም፤ አለመሆኔ ግን በሌሎች የተመሰከራላቸውን የጄኔራሉን የጦርነት ውሳኔን አመክንዮአዊነት ከመጠየቅ የሚያግደኝ አይመስለኝም፤ እናም ማመዛዘን የሚችል አዕምሮ ያለው ማንም ሰው ሊጠይቃቸው የሚችላቸውን ሁለት ጥያቄዎችን ልጠይቅ ፦
- በውትድርና ጥበብ አንዱና መሠረታዊ ግብዓት ጦርነትን ከመግጠም በፊት የጠላትን ጦር የትጥቅ ብዛትና ዓይነት መገምገም ነው። ከስድስት ወራት በፊት ይህ መረጃ በጄኔራሉ ዘንድ አልነበረም እንበል፤ ጄኔራል ፃዲቃን የኢትዮጵያ ጦር መቀሌን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በአማራና በአፋር ግንባር ጦርነትን ሲያውጅ ድሮኗን ረስቷት ነው? ካለፈው የሽንፈት ታሪኩ ትምህርት ቀስሞ ድሮኗ ለሁለተኛ ዙር የሽንፈት ሰበብ እንዳትሆን ምን መላ ይዞ ነው ወደ ጦር ሜዳው የገባው? ለሁለተኛ ጊዜ ድሮኗ እንቅስቃሴአቸውን እንደገታች ለመገንዘብስ ይህ ሁሉ ወጣት መሰዋት ነበረበት? ጄኔራል ፃዲቃን ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነቱን ሲያውጅ ኢትዮጵያ ድሮኖቿን እንዳትታጠቅ “disarm” እንደተደረገች መረጃ ደርሶት ነው?(በነገራችን ላይ ይህቺን የ “Disarmament” ድራማ አሁን ብዙ ወጣት ካለቀ በኋላ በአሜሪካ አማካይነት ከመሸ ጀምረውታል)። ከሁሉም ከሁሉም ተሽከርካሪዎቹ ለ”ግዙፍ” ሠራዊቱ ስንቅ ይዘው ረዥም ርቀት እንደሚጓዙ የተገለጠለት ደብረ ሲና ከደረሰ በኋላ ነው? እንደዚህ ዓይነት መደዴ ስህተት ከ”one of the finest military strategists of his generation in Africa” ይጠበቃል? ግራ ያጋባል!!!
- ጄኔራል ፃዲቃን ከድሮኗ በተጨማሪ ለማፈግፈጉ ሰበቡን ያስቀመጠው “ወደ አዲስ አበባ በምንገሰግስበት ጊዜ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሂደቶች ከወታደራዊ አካሄዳችን ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም። የዲፕሎማቲክ ሁኔታዎች በሚፈለገው መልኩ እየሄዱ አልነበሩም።” በማለት ነው። በተለይ “የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሂደቶች ከወታደራዊ አካሄዳችን ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም።” የሚለው አባባል ዝርዝር የሚያሻው ነው። ለመሆኑ በዲፕሎማሲው ከኢትዮጵያ ይልቅ ለወያኔ ቀኝ እጃቸውን የሰጡ ኃያለን ሀገራት አይበልጡም? ከሚዲያዎቹ እነ CNN, BBC, REUTERS, AFP ከማን ጎን ነበሩ? የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ ፣ የአየርላንድ ወዘተ መንግስታትስ ቅጥ ያጣ ወገንተኝነት እንዴት ይረሳል? ወይስ የዲፕሎማሲው አለመሳካት የተባለው በተባበሩት መንግስታት ቻይናና ራሺያ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን ተጠቅመው የነአሜሪካንን ደባ ማክሸፋቸው ነው? መንስኤው ይህ ከሆነ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካና የእንግሊዝ ጫና በቻይናና ራሺያ መክሸፉ እየታወቀ ጦርነቱ እስከ ደብረ ሲና ለምን ቀጠለ? ዲፕሎማሲው መክሸፉን ለመረዳት ይህን ሁሉ ኪሎ ሜትሮች መዝለቅ ያስፈልግ ነበር?
ከዚህ ሁሉ ይልቅ “one of the finest military strategists of his generation in Africa” ራሱን ለተሳሳተ ግምትና ትንበያ አጋልጦ ሰጥቷል ቢባል ይሻላል። ምክንያቱም ጁላይ 26/ 2021 ቆቦና ወልዲያ ከተቆጣጠሩ በኋላ ጄኔራሉ ethiopanarom.com ላይ እንደዚህ ብሎ ነበር፦
“አሁን የኃይሎች ሚዛን ሙሉ በሙሉ ለእኛ ሞገስ ሆኗል… የሐይል ሚዛኑ በእጃችን ስለሆነ አዲስ አበባን በቅርብ ጊዜ እንቆጣጠራለን” ከማለቱም ባለፈ “የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ተቃዋሚ በሌለበት ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ መሄድ እንደሚችል” በእርግጠኝነት ተናግሮ ነበር።
ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያን ጥምር ጦር ፈጣንና ፈርጣማውን ክንዱን እንኳን ለጊዜው አቆይተን፣ ከዛሬው የጄኔራል ፃዲቃን ገ/ትንሳኤ የቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ብቻ እንኳን ብንደረደር ቀደም ሲል ትህነግ ለ”ሰላም ስል ወጥቼአለሁ” በማለት ያስተጋባቺው የሐሰት ትርክት መቀመቅ ውሸት መሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፦ ይህን ቀድመን የምናውቀው ቢሆንም አሁን ግን ጄኔራል ፃዲቃን በራሱ ተናሳሽነት አረጋግጦልናል። እናም በእሱ ማብራሪያ መሠረት የተረፈው ሠራዊቱ ያፈገፈገው፦
ሀ. ድሮኗን ማቋቋም አቅቶት
ለ. የትህነግ ሠራዊት ወደ አዲስ አበባ በሚገሰግስበት ጊዜ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሂደት ከወታደራዊ አካሄዳቸው ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ።
ታዲያ እነዚህን ሁለቱን ምክንያቶች “ለሰላም ሲባል ከማፈግፈግ ጋር ምን ያገናኛቸዋል?” ምንም!