መዘዞ-የመጨረሻው መጀመሪያ-
የአሞራው ገብርኤል ደጃፍ ታሪኮች
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
እየነገሩኝ አይደለም፤ እያየሁ ነው፡፡ ዓይኖቼ በየጥሻው ደም ተነክረው የወደቁ ሽርጦችን፣ ፕላስቲክ የትግል ጫማዎችን፣ የጀርባ የስንቅ ቦርሳዎችን ይመለከታሉ፡፡ ጣርማ በር ወረዳ ነኝ፤ ኮረብታማዋ ሥፍራ ወታደራዊ ሰዎች ገዢ መሬት የሚሏት ናት፡፡ ግን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን አርፎባታል፡፡ ሞሰቢት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን፤
ወደ መንደሯ የደረሱት ወራሪዎች 1983 የመጡበትን መንገድ ተከትለው ስለመሆኑ የቦታው አባቶች ነገሩኝ፡፡ እንደ ደረሱ የነበረው ጦርነት አበሳ ነው፡፡ እነሱ የገብርኤልን ቅጥር መሸጉበት፡፡ ከዚያ ሆነው የተኮሱትን ጥይት ብዛት ምን ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ረዥም ነው፡፡ በአጭሩ ልንገራችሁ-አናቱ የተመታው ቀደምቱ ደብር ፈቅ ብሎ አርፏል፡፡ ታሪካዊው ታቦት ከሞረትና ጅሩ ያለው መንገድ ሲሰራ ዶዘር ምድር ሲቆፍር ያገኘው ነው፡፡ ተጎድቷል፡፡
ዋናውና አዲሱ ቤተ ክርስቲያን ፈቅ ብሎ በሚያምር ቅጥር ውስጥ በድንቅ ሁኔታ ታንጾ ነበር፤ አሁን መገለጫው ነበር ነው፡፡ የጦር ምሽግ ባደረገው ወራሪ ፈርሷል፡፡ ብዙ ተጎድቷል፡፡ ውብ ሆኖ ይሰራ ዘንድ ብዙ የደከመው ሀገሬው ደስታውን ሳያጣጥም፣ ብዙ ታሳስ፣ ብዙ ሐምሌ ሳያነግስበት እንዲህ ሆኗል፡፡
የሚገርመው ህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሰራበት ክፍያ አላለቀም፤ ደብሩ ባህር ዛፌን ሸጬ እዳውን እከፍላለሁ ብሎ ነበር፡፡ ሰበካው አምስት መቶ ሺህ ብር ያስገመተው ባህር ዛፍ የጦር አውድማ ሆኖ ዶግ አመድ መሆኑን አየሁ፡፡
ሞሰቢት ትምህርት ቤትን አልፌ ነበር ወደ ቤተክርስቲያኑ ቅጥር የደረስኩት ትምህርት ቤቱ በጣም ተጎድቷል፡፡ ምድረ በዳ ያለ የጦርነት መለማመጃ ይመስል ነበር፡፡ እዚህም እዚያም የቦንብ ስብርባሪዎች፣ የተተኮሱ ቀለሃዎች፣ የከባድ መሳሪያ ጥይት ቅሪቶች ይታያሉ፡፡
አሞራው ገብርኤል የደብሩ ቅጽል መጠሪያ ነው፡፡ የገብርኤል ቀን የሆነውን ሲነግሩኝ ተደነቅሁ፡፡ የነገሩኝን ልንገራችሁ፤ ከየት መጣ ያልተባለ እባብና ጊንጥ ድንገት ወረራቸው፣ ያ ገዢ መሬት ነው፡፡ ወገን ከማዶ በእሳት ያጣድፋቸዋል፡፡ እዚህ እንዲህ ያለ ተአምር ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነው የሚገለጽ አይደለም፡፡ የመጨረሻው ጦርነት ተጀመረ፡፡ ድል ሆነ፡፡
ደግሞ ይሄንን ሰማሁ፤ ሰውዬው ገበሬ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ዘምቷል፡፡ ወጣት ሆኖ መትረየስ አቆሞ የተነሳውን ፎቶ ደሃ ጎጆው ግድግዳ ላይ ሰቅሏታል፡፡ ሲደርሱ አየቷ፤ ከዚያ ጠየቁት፡፡ መትረየሱን አምጣ? ብለው፤ አስረዳቸው፡፡ እንደጨረሰ ገደሉት፡፡
አንድ ገና ወጣት ለመሆን በራፉ ላይ ያለ ልጅ እግር የሆነውን አወጋኝ፡፡ የሞቱትን ሬሳ ጥለው ፈርጥጠዋል፡፡ ሊያውም የያዙትን ይዘው የቀበሩትን ቀብረው ነው አለኝ፡፡ ቀጠለና
“እነኛ መሪዎቻቸው ነበሩ እንጂ እነኚህማ መቼም ክፉ ቢሆኑም እንደኛ ሰው ናቸው፤ መቼስ ኢትዮጵያዊም ናቸው፤ አይደለንም ስላሉ አይሆን፤ ውሻ እንኳን ያሳዝናል እንኳን ሰው፡፡”
ሊገድሉት ሲሉ ያመለጠ፤ ራሱን አድኖ ከለበሳት ውጪ ያልተረፈችው አንድ ፍሬ ልጅ ይሄንን አሰበ፡፡ እድሜ ጠገቦቹ፣ ትግል ልምድ አለን የሚሉት፣ ወጣቶቻቸውን እንዲህ የማገዱት፤ እንደዚህ አንድ ፍሬ ልጅ ቢያስቡ ኖሩ አልኩ፤
ኖሮ ነው ታዲያ ምን ዋጋ አለው፤ እንቀጥል ወደ መንዝ ጓሳ…