“የኢትዮጵያ ሰላም የሚረጋገጠው አሸባሪው ትህነግ ከእነ-ሰንኮፉ ሲነቀል እና እስትንፋሱ ሲቋረጥ ነው!”
(ጃንጥራር አባይ ~ የአ/አ ከተማ ም/ከንቲባ)
የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ላይ ያልሞከሩት ሴራ፣ ያልጀመሩት ደባ አልነበረም። ሴራውና ደባው ትናንት ተሞክሮ ከሽፏል። ዛሬም በተባበረ ክንዳችን ወደ ትቢያነት እየተቀየረ ይገኛል። ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማኮሰስ የተነሳ ሁሉ የአድዋውን እጣ ፋንታ ይወርሳል።
በፍርስራሻቸው ላይም ዘላቂ ሰላምንና ዴሞክራሲን እንተክላለን። ባንዳዎች እና ጋላቢዎቻቸው እየከሰሙ ፤ ኢትዮጵያም በአለት ላይ መፅናቷን ለአለም አሳይታለች።
ከትናንት ወዲያ ከ500 በላይ የአዲስ አበባ ርእሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘር እና መምህራን ጋር እንዲሁም ትናንት ማለትም ታህሳስ 8/2014 ደግሞ ከዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ከልዩ ልዩ ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ምክክር አድርገናል።
በውይይቱ መልካም ግብአትም አግኝተንበታል። ምሁራኑ ከምንጊዜውም በላይ ሀሳባቸው ይፈለጋል። ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያስፈነጥር እውቀት ባለቤት ናቸውና!
መንግስትና ምሁራን ሆድና ጀርባ የነበሩበት ጊዜ አክትሟል። ዛሬ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሰፈሰፉት ሀይሎች፣ ትናንት የእውቀት አምባዎችን ሲወጉና ሲያፍኑ የነበሩ ናቸው። እነዚህን አፋኞች ጨርሶ የሚያከስም መፍትሔ ማምጣቱ ተገቢ ነው። አሸባሪው ትህነግ የሀገራችን የዘመናት ችግር ነው።
ችግሩ ከእነ-ሰንኮፉ የሚነቀለው ደግሞ የአሸባሪው እስትንፋስ እንዲቋረጥ ሁሉም ሕዝብ ጨርሶ ሲተፋው ነው። ያለ ጥርጥር አስተሳሰቡም አስትንፋሱም ይቋረጣል!
ከምሁራኑ ሁለት ነገር ይጠበቃል። የመጀመሪያው በአሸባሪው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች አዕምሮና መንፈስ ማከም መቻል ነው። የወደሙ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት በሚተኩበት መንገድ እውቀትና የተባበረ አቅም ከምሁራኑ የሚጠበቅ መፍትሔ ነው።
ኢትዮጵያ በዘላቂነት ከጦርነትና ከደም አፋሳሽ ታሪክ የምትላቀቅበት መንገድ ማመላከትም ሁለተኛኛው ከምሁራን የሚጠበቅ ተግባር ነው። ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ መስራት ተጀምሯል። አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት መዋቅርም የምሁራኑን ምክረ ሀሳብ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግና ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬም በአሸባሪው የተያዙ ቦታዎች አሉ። ጠላት በያዛቸው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በአሸባሪው እኩይ ምግባር ግፍ እየተፈፀመባቸው ነው። በጥምር ጦራችን ቆራጥ ተጋድሎና በሕዝባችን ዘላቂ ደጀንነት በአጠረ ጊዜ ነፃ እናደርጋቸዋለን። ሰላም፣ ዴሞክራሲና የኢትዮጵያ ብልፅግና የመጨረሻው ትልማችንም መዳረሻችንም ይሆናል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ብርቱ ትግል ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!