Connect with us

ጄኖሳይድ ለመባል ስንት ሰው መሞት ይኖርበታል?

ፍቱን ታደሰ

ነፃ ሃሳብ

ጄኖሳይድ ለመባል ስንት ሰው መሞት ይኖርበታል?

ጄኖሳይድ ለመባል ስንት ሰው መሞት ይኖርበታል?
(ፍቱን ታደሰ … ለድሬቲዩብ)

የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ (Genocide) ድርጊት በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም እጅግ ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ነው። አንድ ዘር ወይም ብሔር ላይ አነጣጥሮ በርካታ አባላቱን መፍጀት በሰው ልጆች ታሪክ አሰቃቂ ጠባሳ ትቶ ያለፈባቸው ወቅቶች በክፉ ይታወሳሉ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመናውያን ናዚዎች አይሁዳውያንን ዘራቸውን ከምድር ገጽ ለማጥፋት በጅምላ የጨፈጨፉበት ወቅት በሰው ዘር ላይ ከተፈጸሙ ክፉ ድርጊቶች በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።

ፋሺስት ኢጣሊያ ሃገራችንን በወረረበት ጊዜ በተለይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ስድስት ኪሎ አካባቢ በፈጸመው ጭፍጨፋ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፏል፡፡ በግራዚያኒ ትዕዛዝ ጭፍጨፋው ጣልያን በተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ ለሶስት ቀናት ቀጥሎ ከ125 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከህጻን እስከ አዋቂ በአካፋና በመርዝ ጋዝ በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡

የጣሊያንን ጭፍጨፋ እስከ ዛሬ ጄኖሳይድ ብሎ የጠራው የለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በምዕራባውያን የሚፈጸም የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በጄኖሳይድ አይመዘገብም፡፡

በምስራቅ አውሮፓ ዩጎዝላቪያ ውስጥ ከተፈጸመው የዘር ማጥፋት በኋላ በዘግናኝነቱ የተመዘገበው በሩዋንዳ 800 ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች የተጨፈጨፉበትና በሱዳን መንግስት ድጋፍ የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ከ400 ሺህ በላይ በሚሆኑ የዳርፉር ህዝብ ላይ ያደረሱት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ነው፡፡

በሌሎች ሃገራት ላይ ሲፈጸም በርቀት ስናየው የነበረውን ጄኖሳይድ ወያኔ ስልጣን በያዘ ማግስት በአማራና በጋምቤላ ህዝብ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር የሰብአዊ መብት ጠበቃ ነን የሚሉት ምዕራባውያን አይተው እንዳላየ ነበር ያለፉት፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጸመው ጄኖሳይድ በተወሰነ ጊዜ ተከናውኖ የቆመ ሳይሆን ሰላሳ አመት ሙሉ ተካሂዶ አሁን ደግሞ እየተባባሰ ነው የመጣው፡፡

በ1984 በምስራቅ ሃረርጌ በደኖ፣ ወተር፣ ቀርሳ እንዲሁም አርባጉጉ በወያኔና በኦነግ በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ታርደዋል፡፡ በ1993፣ በ1996፣ በ1997 ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ፣ የኦሮሞና የጋምቤላ ብሔር ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለየ ሁኔታ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ጄኖሳይድ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በለውጡ መንግስት የተቋቋመውና በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሥራ ከጀመረ በኋላ በማይካድራ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወለጋ፣ በቤንሻንጉል እየተፈጸሙ ያሉ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ጄኖሳይድ ብሎ ለመጥራት ሲያመነታና ሲሽኮረመም አይተናል፡፡ ገለልተኛ ተብሎ የተቋቋመው ተቋም ጄኖሳይድ እየፈጸሙ ያሉትን አረመኔ ቡድኖች ወንጀላቸው እንዳይጋለጥ የሚደረገው መሸፋፈን ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡

ከሕግ ትርጓሜ አንጻር የዘር ማጥፋት የሚባሉት ምን  አይነት ጭፍጨፋዎች ናቸው? የሚል ጥያቄ ይሰነዘራል። የዘር ማጥፋት የሚለው አገላለጽ የሚሠራው በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው? የሚለውም እንዲሁ። የዘር ጭፍጨፋ ወይም በእንግሊዘኛው ጄኖሳይድ [Genocide] የሚለው ቃል፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ1943 በአይሁድ ፓላንዳዊው ጠበቃ ዶ/ር ራፋኤል ለምኪን ነው ጥቅም ላይ የዋለው።

ቃሉ የግሪኩ ጄኖስ [Genos] እና የላቲኑ ሳይድ [Cide] ቃላት ጥምረት ነው። ጄኖስ ዘር ወይም ብሔር ማለት ሲሆን ሳይድ ደግሞ ግድያን ያመለክታል።

ከአንድ ወንድሙ ውጪ መላ ቤተሰቡን በአይሁዳውያን ላይ በተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ (ሆሎኮስት) ወቅት ያጣው ዶ/ር ራፋኤል፤ የዘር ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ተብሎ እንዲመዘገብ ንቅናቄ አድርጓል። ንቅናቄው፤ የተባበሩት መንግሥታት የዘር ጭፍጨፋን በሚመለከት ስምምነት ላይ እንዲደርስ አስችሏል።

ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ በ1948 ሲሆን፤ ስምምነቱ መተግበር የጀመረው ከሰኔ 1951 ወዲህ ነው።
የስምምነቱ ሁለተኛ አንቀጽ የዘር ጭፍጨፋን የሚተረጉመው “የአንድ አገር፣ ብሔር፣ ዘር ወይም ሐይማኖት አባላትን ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ለማጥፋት የተቃጣ” ብሎ ነው። ይህም የአንድ ቡድን አባላትን መግደል፣ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ማድረስን ያካትታል።

በተጨማሪም የቡድኑ አባላት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ማሴር፣ የቡድኑ አባላት ልጆች እንዳይወልዱ ማድረግ እና ልጆችን በግዳጅ ወደ ሌላ ቡድን መውሰድን ያካትታል። በአገራችን እነዚህ ነገሮች ሁሉ በይፋ ተፈጽመዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ በቤተሰብ ምጣኔ ስም ወንዶችን እንዳይወልዱና መሃን ሆነው እንዲቀሩ የማድረግ ተንኮል በወያኔና አማራ ሆነው የወያኔን አላማ በሚያስፈጽሙ የብአዴን አመራሮች አስፈጻሚነት ተከናውኗል፡፡

በአገራችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሃን በግልጽ በሚታወቅ ሁኔታ የዘር ጥፋት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋናው የግፉ ሰለባ አማራ ነው፡፡ ይሄ ነገር ከዚህ በላይ የሰው ህይወት ሳይበላ እንዲቆም ሊደረግና ጄኖሳይድ መፈጸሙ በይፋ ተገልጾ በዚህ ሂደት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ሁሉ ህግ ፊት ሊቀርቡ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም መሽኮርመሙን ትቶ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡  (ማስታወሻ:- ይህ ፅሁፍ የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም)

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top