ኑ ወራሪውን ብቻ ሳይሆን ወራሪው ያወደመውንም ጦርነት እንግጠመው?!
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
የተወሰኑ ቦታዎችን በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ሌሎቹን እንደ ዜጋ በቴሌቨዥን ተመልክቻለሁ፡፡ ቴሌቨዥን ያልደረሰባቸውን ደግሞ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ ሀገር ጦርነቱ ያለቀ ሊመስለው ይችላል፡፡ በዚህ ወኔ በዚህ ህብረትና በዚህ መንፈስ ሌላው የህልውና ዘመቻ በወደመው ሀብት ላይ መቀጠል አለበት፡፡
የግለሰቦች ህይወት ጨለማ ውጦታል፡፡ ዜጎች የኑሮ ዋስትናቸው አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ከተሞች ተራቁተዋል፡፡ ሆስፒታሎች ተዘርፈዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ጠላት ይሄንን አድርጓል፡፡ ጠላት ላይ እንደዘመትነው ሁሉ ጠላት የፈጸመው ጥፋት ላይም መዝመት ይገባናል፡፡
አሁን ውድመታችንን ጦር ሰብቀን ልንሄድበት ይገባል፡፡ የፈረሱ ከተሞችን መስራት፣ የወደቁ ቤቶችን ማንሳት፣ ጨለማ ለሆነባቸው ዜጎች ብርሃን መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይሄም አንድነት፣ ይሄም ሙዚቃ፣ ይሄም ሰልፍ፣ ይሄም ሆ ብሎ መነሳትን ይፈልጋል፡፡
ወራሪው ድል ተደርጎ ኪሳራው አሸንፎን ከቀረ ማሸነፋችን ከንቱ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ጦርነቱ ሁሉ ኪሳራው ላይ ዘምተን አብረን ቆመን የገጠመንን ፈተና ማለፍ አለብን፡፡ ትናንት ቤት የነበራቸው ዛሬ ሜዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ ትናንት ሁሉ የሟላላቸው የጤና ተቋማት ዛሬ ፍርስራሽ ሆነዋል፡፡ ተዘርፈው ከወደሙ ሀብቶቻችን ጋር ጦርነት ገጥመን ድል ማድረግ ይኖርብናል፡፡
ተስፋ ከቆረጠው ወገናችን ስሜት ጋር ጎሬላ ተናንቀን ወደ ተስፋው መመለስ አለብን፡፡ አበቃለት የተባለው ልማት ዳግም በሞት ሽረት ትግል እኛ እንዲህ ነን የምንልበት ውጤት ካልተመዘገበ ድሉ ከንቱ ነው፡፡
ድል ያስፈልገናል፡፡ ያ ድል ጠላትን ብቻ ሳይሆን የጠላትን ኪሳራና ውድመትም በማሸነፍ መደምደም አለበት፡፡ ጠላት ያጠፋውን በማልማት መበሰር አለበት፡፡
ብዙ መከራ ገጥሞናል፡፡ በጥቃቅን የተደራጁ ዜጎቻችን ጎዳና አፋፍ የከፈቷቸው ሱቆች ተዘርፈዋል ወድመዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎችና ሆቴሎች እንዳልነበር ሆነዋል፡፡ ሆስፒታልና ፋርማሲ ከሰው ፍጥረት ተቃራኒ ከሰማይ የተወረወረ እስኪመስል ዘግናኝ ጥፋት ደርሶባቸዋል፡፡
ጦርነቱ ረዥም ነው፡፡ መሳሪያ ያልያዙ ወገኖች ነገ ዛሬ ሳይሉ ዶማ ይዘው የፈረሰውን መስራት የወደመውን ማልማት ያስፈልጋል፡፡ በመከራ ውስጥ አንድ ቀን ብዙ አመት ነው፡፡ ድል ወገንን ከስቆቃ፣ ሀገርን ከጥፋት ማዳን ጭምር ስለሆነ እንደ አጥፊው ሁሉ የወራሪውን ጥፋትም ድል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ለዘመቻ እንደተጠራራነው የጠፋውን ለማልማት ወገንን ከጨለማ ለማውጣት መሰረተ ልማቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ በዚያ የተጋድሎ ህብረት መንፈስ ከዳር ዳር ሆ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያለ ዘመቻ የሚፈልጉ የአማራና የአፋር አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ እኛ ከችግሮቻችን የምንበዛ መፍትሔዎች ስለሆንን አሁን ሀገራዊ በሆነ፣ ማዕከላዊነት ባለው ህብረት በጋራ ልንቆም ይገባል፡፡