Connect with us

ዐጤ ምኒልካዊ ሰብአዊነት እና ርኅራኄ…!!

ዐጤ ምኒልካዊ ሰብአዊነት እና ርኅራኄ…!!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ዐጤ ምኒልካዊ ሰብአዊነት እና ርኅራኄ…!!

ዐጤ ምኒልካዊ ሰብአዊነት እና ርኅራኄ…!!

(ዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፡፡

ይድረስ ከሮም ሊቀ ጳጳሳት ሌዎን ፲፫ኛ፤ ሰላም ለርስዎ ይሁን፤

ክቡር ሊቀ ጳጳሳት ሆይ፡፡

በዚህ ደብዳቤ ቀጥሎ የሚጻፈውን ግፌን አስታውቅዎታለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ነጻነቷና ራሷን የቻለች መንግሥት ባጠገቧም ጎረቤት የሌላት መሆኗ አስቀድሞ በዮሮፓ መንግሥታት ሁሉ የታወቀ ነው። ከግራኝ ዠምሮ እስካሁን በአሕዛብ እጅ ተከባ ዘወትር በጦርነት ድካም ነው ኑሯችን። ከዮሮፓ የጦር መሳሪያ አስመጥቼ ሠራዊቴን ዘወትር ከጦርነት ድካም አሳርፋለሁ ስል ከንጉስ ዑምበርቶ አባት (ዳግማዊ ቪክቶር ኢማኑኤል) ጋራ የፍቅርን ነገር ዠመርኩ፡፡ ንጉሥ ዑምበርቶም መንግሥት በያዙ ጊዜ እኔም እንደአባቴ ፍቅርን እወዳለሁ ብለው ቢልኩብኝ እኔም እንደአባትዎ ታፈቀሩኝ እሺ ብዬ ፍቅርን ተቀበልሁ፡፡

ኮንት አንቶኔሊ የሚባል የኢጣልያ ሰው በገንዘብዎ ጠበንጃ ልግዛልዎ ቢለኝ ብዙ የዝሆን ጥርስና ወርቅ ሰጥቼው ይዞ ሄዶ ከንጉሥ ዑምበርቶ አስፈቅዶ ገዝቶልኝ ቢመጣ ከመንግሥት ፈቃድ በማግኘቱ እጅግ ደስ አለኝ፡፡ ሁለተኛም ንጉሥ ዑምበርቶ ኮንት አንቶኔሊን የመንግሥት መልክተኛ አድርገው ወደኔ ሰደዱት፡፡ ተልኮ ያመጣውም ቃል ይህ ነው፡፡ ነጋዴም እንዲነግድ የጦር መሳርያ እንዳይከለከል ይፈቀድልዋል፡፡ 

እርስዎም ባሪያ እንዳይሸጥ ይከለክላሉ በሌላ መንግሥት ያለ መሳርያ ሁሉ ብትፈልጉ በኛ በር ይወጣላችኋል አይከለከልም፡፡ እንደ ዮሮፓ ነገሥታት የተጠላው ውል (የውጫሌ ውል) በአምስት ዓመት ይለወጣል የተወደደው ይረጋል፡፡

… ምጥዋ ሐሩር ሆኖብናል ለሰዋችን ማሳረፊያ ጥቂት ነፋስ ያለበት ሥፍራ እንዲሰጡን የፍቅርን ውል ይህን እናድርግ ብለዋል አለኝ፡፡ እሺ ይሁን ብዬ እኔም ለመንግሥቴና ለኔ የሚስማማና የሚጠቅም ቃል በአማርኛ በትክክል አድርጌ አስጥፌ ብሰጠው አስራ ሰባተኛው ክፍል ላይ ቃሉን በኢጣልያ ቋንቋ ለውጠው ከጥንት ዠምሮ ነፃ የነበረውን መንግሥቴን የሚያዋርድ የማይስማማኝ ቃል ቢሆንብኝ እኔ ባስጣፍኩት በአማርኛው ቃል ይርጋ ኢጣልያው ቋንቋ ከኔ ከአማርኛው ጋር ያልተካከለ ነው አሁንም በትክክል እናድርገው ብዬ ወደ ንጉሥ ዑምበርቶ ብልክባቸው ምላሽ ሳይሰጡኝ ቀሩ፡፡

… እኔም ነገሩ ለተንኮል እንደሆነ አውቄ የክርስቲያን ደም በከንቱ እንዳይፈስ አስቀድሜ ለዮሮፓ ነገሥታት ሁሉ ከንጉሥ ዑምበርቶ በውሉ እንዳልተስማማን አስታወቅሁ፤ የእውነት ፍርድ አገኛለሁ ስል፡፡ ሁለተኛም አምስት ዓመቱ ሲደርስ የጠላነው እንዲቀር የወደድነው እንዲረጋ ሰው ይላኩልኝ ብዬ ብልክ እስከምላሹም አስቀሩት፡፡ ከዚህ ወዲህ ይልቅ ክፉ ነገር እየበረታ ሄደ። አሽከሬን ደጃች መሸሻን አለፍርድ አሰሩት፡፡

 ልክ አበጅቼ የሰጠኋቸውን አገር አልፈው የሾምኩትን ሹም ራስ መንገሻን ወግተው አባረው አገሬን ትግሬን በሙሉ ያዙት፡፡ ከዚያ አልፈው ላስታ መሬት እስከ አሸንጌ ድረስ ወጡ፡፡ ከዚህ ወዲያ አገር የሚጠብቁ መኳንንቶች ከኔ ብሰድ አምባላጌ ላይ በር ይዘው ቆይተው ተዋጉዋቸው የእግዚአብሔር ኃይል በኔ ሰዎች አድሮ ድል አደረጉዋቸው፡፡

እኔም ወደዚያው ተከትዬ ብሄድ መቀሌ እርድ ገብተው አገኘሁ። ጦርነት ተሆነ ከትልቁ ጋር እዋጋለሁ እናንተ ክርስቲያኖች በውኃ ጥም አትለቁ ብዬ እስከ መሳሪያቸው ከእርድ አሰጥቼ ለጀነራል ባራቲዬሪ ሰደድኩለት፡፡ እኔም ከዚያ ተጉዤ አድዋ እከተማዬ ሰፍሬ ጀነራል ባራቲዬሪ እውነት የመሰለ የእርቅ ቃል ላከብኝ፡፡ እኔም እርቅ ከፈለጉ ብዬ ሠራዊቴን ቀለብ ሰድጄ ሣለ እንደ ዮሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቁኝ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሠግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ዠመረ፡፡

… ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከኢጣሊያ ጋር ለዕርቀ-ሰላም ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፣ እናም የዐድዋ ጦርነት አይቀሬ ኾነ፡፡ ድሉም ለኢትዮጵያ ኾነ፡፡ ዐፄ ምኒልክ ከዐድዋ ድል በኋላ መጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸውም – ላቅ ያለ የሞራል ከፍታቸውን፣ ሰብአዊነታቸውንና ርኄራኄያቸውን የሚገልፅ ነበር፤

‘‘… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ ዕርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡’’

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top