Connect with us

የወሎ ፍቅር

የወሎ ፍቅር
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የወሎ ፍቅር

የወሎ ፍቅር

(ጥበቡ በለጠ)

ወሎ የፍቅር ምድር ነች፡፡ ሁሉን እንደ አመሉ የምታኖር ድንቅ ስፍራ፡፡ አቤት ስወዳት! ወያኔ የክፋት በትሩን ጥሎባት አንጀቴን አሳርሮት ቆየ፡፡ እነዚህ አረመኔዎች ብዙ በደል ፈጽመውባታለል፡፡ እስኪ እንደው ተወዳጇን ወሎ ላነሳሳት፡፡

ጥንት ወሎ ጠቅላይ ግዛት ትባል ነበር፡፡ በዘመነ ደርግ ወሎ ክፍለ ሐገር ተባለች፡፡ በኢ.ሕ.አ.ዲ.ግ ዘመን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ እየተባለች ትጠራለች፡፡ መጠሪያዋ በየዘመኑ ቢለያይም ወሎ ግን ሁል ጊዜ በኢትዮጵያ የጥበብ፣ የታሪክ፣ የባሕል፣ የሐይማኖት፣ ጉዳዮች ላይ ብርሃናማነቷን እያንቦጐቦገች ቀጥላለች፡፡

በሐይማኖት ረገድ የሁለቱ ትልልቅ ሐይማኖቶች ዋነኛዋ መናሐሪያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሐይማኖት ውስጥ ቅዱስ እየተባሉ የሚጠሩ የጥበብ ሊቆች በተከታታይ የፈለቁባት ምድር ነች፡፡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ሐርቤይ ፣ቅዱስ ላሊበላ እና ቅዱስ ነአክቶለአብ፣ የሐይማኖት መሪዎቸ ብቻ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያንም ያስተዳደሩ መሪዎች ናቸው፡፡ ቤተ-ክርስትያኒቱ ሰው ከመሆን አስበልጣ የቅድስና አክሊል ያጐናፀፈቻቸው የኢትዮጵያ አስገራሚ መሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን ቅዱስ መሪዎች አርግዛ የወለደችው ወሎ ናት፡፡

በእስልምና ሐይማኖትም ብንሔድ ወሎ ውስጥ በርካታ አስገራሚ ጉዳዮችን እናገኛለን፡፡ በኢትዮጵያ የእስልምና ሐይማኖት ውስጥ ከመንፈሣዊ ድርሻው ባሻገር ጥበባዊ ድርሻውም እጅግ ግዙፍ የሆነው መንዙማ መገኛው ወሎ ነው፡፡ በእስልምና ሐይማኖት ውስጥ የሊቆች መገኛ መወለጃ ስፍራ ነች ወሎ፡፡ ክርስትና እና እስልምና ተከባብረው፣ ተወዳጅተው፣ ቤተሰብ ሆነው፣ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብስ እየተባባሉ ረጅም ዘመናት የቆዩባት አስገራሚ ምድር ወሎ ናት፡፡

ኧረ ወሎን እንዴት አድርጌ ልግለፃት? በሙዚቃ የአዘፋፈን ቃና ነፍሴን ብርብር የምታደርገው ማሪቱ ለገሰ፣ አምባሰልን ስትጫወት ደንዝዤ የማለቅስባቸው በርካታ ቀኖችን አስታውሼ አልጨርሳቸውም፡፡ ወሎ የማሪቱ ለገሰ/ማሬዋ/ መገኛ፣ መወለጃ ናት፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ዋነኛ ስልት የሆኑት የአምባሰል፣ የባቲ፣ እና የትዝታ ቅኝቶች መፍለቂያ ስፍራ ናት፡፡ የኢትዮጵያ የጥበብ ደብር እያሉ የሚጠሯትም አሉ፡፡

በዚህ በኛ ዘመን ውስጥ ካሉት ድምፃዊያን የሙዚቃ ምትሐተኞች መካከል ለእኔ ግንባር ቀደሟ እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ ናት፡፡ የጂጂ የአዘፋፈን ስልት የተቀዳው ወይም የተወረሰው ከወሎ ነው፡፡ የወሎን ስልት ይዛ፣ የአሚናዎችን ሙዚቃዊ ልመና፣ ሙዚቃዊ ፍቅርና አክብሮት፣ ተለማማጭነት፣ ታሪክ ነገራን፣ ትረካን ይዛ እጅጋየሁ ሽባባው የኢትዮጵያን ሙዚቃ እላይ አወጣችው፡፡

 የጂጂ ሙዚቃዎች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት ውስጥ ጉባኤ ቃናን፣ ከእስልምና ሐይማኖት ውስጥ የወሎን መንዙማ፣ ከሐገረሰብ ጥበባዊ ቅርሶች ውስጥ የወሎን የአሚናዎች የልመናን ዘዬ፣ በመውሰድና ሙዚቃዊ ቃና በማዋሐድ እያንጐራጐረች ወደ አለም የሙዚቃ መድረክ መጣች፡፡ CNN የተባለው ግዙፉ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጂጂ ላይ በሰራው ዶክመንተሪ African rising star ብሎ ጠርቷታል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ከመጡት ተስፋ ከተጣለባቸው ከዋክብት የሙዚቃ ጥበበኞች መካከል በዋናነት CNN አድናቆቱን ለጂጂ ሰጥቷታል፡፡ ይህች የሙዚቃ ታላቅ ስብዕና ጥበብን ዝቃ የወሰደችው ከወሎ ነው፡፡

እና፤ ስለ ወሎ የቱን አውርቼ የቱን ልተወው? የወሌዎች ምርቃት፣ ዝየራው፣ የወሌዎች የቋንቋ ቃና መች ተሰምቶ ይጠገባል፡፡ አማርኛ ቋንቋ ራሱ የተፈጠረው ወሎ ውስጥ ባለችው ወረዳ አማራ ሳይንት ነው ብለው የድሮ ታሪክ ጸሀፊዎች ነግረውናል፡፡ እንዴት ይህን ሁሉ ነገር ታደለችው? እያልኩ ዘወትር እያሰብኩ፣ እያደነኳት፣ እየወደድኳት፣ የተለያዩ ዶክመንተሪ ፊልሞችንም ብሰራባት፣ የወሎ ፍቅር እንደ አዲስ ሁሌም ያገረሽብኛል፡፡

ታሪካዊቷ መቅደላ አምባ የምትገኘው ወሎ ውስጥ ነው፡፡ የግዙፍ ሰብእናዎች ባለቤት የሆኑት ታላቁ ንጉስ አጼ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ፍቅር ብለው በገዛ ሽጉጣቸው መስዋዕት የሆኑባት መቅደላ ታሪክን እየዘከረች ዛሬም አለች፡፡ ኢትዮጵያ በእንግሊዝ ወታደሮች አማካይነት የጥበብ አንጡረ ሀብቶችዋ የተዘረፉባት መቅደላ አምባ ጭር ብላ ሳያት ስሜቴን እየነካችው በአመት አንዴ እየሄድኩ አያታለሁ፡፡ መቅደላ አምባ አጼ ቴዎድሮስ ከተሰው በኋላ 2 ቢሊዮን ፓውንድ /በዛሬው ምንዛሬ 60 ቢሊዮን ብር/ የሚያወጡ የብራና መጻሕፍት ተዘርፈውባታል፡፡ እነዚህ ብራናዎች አጼ ቴዎድሮስ ከጎንደር ወደ መቅደላ ያስመጥዋቸው ናቸው፡፡ መቅደላን ትልቅ የጥበብ ማዕከል አደርጋታለሁ ብለው ትልቅ ርዕይ ይዘው ተነስተው ነበር፡፡ ሕልማቸው አልተሳካም፡፡ መድፋቸው ሴፓስቶፖል ዛሬም መቅደላ ላይ ቁጭ ብሎ ቴዎድሮስን ያስታውሰናል፡፡ ከሴፓስቶፖል ባሻገር ባለው ሰንሰለታማ ቁልቁለት እየወረድን ስንሄድ እሮጌ የምትባል ሌላ ታሪካዊት ስፍራ እናገኛለን፡፡ በዚህች ስፍራ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ የምንግዜም አርበኛ ፊት አውራሪ ገብርዬ ተሰውቶባታል፡፡ ወሎ የሰማዕት ምድር ነች፡፡

ሁሌም አንስቸው ወደ ማልጠግበው ሌላኛው የፕላኔቷ ብርቅዬ ሰው ላምራ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ!

ቅዱስ ላሊበላ ከአለት እየፈለፈለ ያነጻቸው አብያተ-ክርስትያናት በምድሪቱ ላይ እስከ አሁን ድረስ ምስጢር ሆነው ቆይተዋል፡፡ የሰው ልጅ ከሰራቸው የኮንስትራከሽን ጥበቦች መካከል እንደ ትንገርት የሚቆጠሩት እነዚህ ኪነ-ሕንጻዎች ፍክትክት ብለው የሚገኙት ወሎ ወስጥ ነው፡፡ ያውም ላስታ ቡግና ወረዳ፣ ሮሐ ከተባለች የቅድስና ቦታ ላይ ነው፡፡ 

ቅዱስ ላሊበላ ዛሬ ኢትዮጵያ ወስጥ ጥምቀት እያልን የምናከብረውን በአል ልዩ ስርአቱን የጀመረው ይህ ጥበበኛ መሪ እና አርክቴክት ነው፡፡ ታቦታት ከመንበረ ከብራቸው ተነስተው ጉዞ አድርገው፣ ጥምቀተ ባህር አድረው፣ አንደገና ወደ መንበረ ክብራቸው የሚመለሱበትን እጅግ ደማቅ ኦርቶዶክሳዊ ትይንተ ሀይማኖት የጀመረው ቅዱስ ላሊበላ ነው፡፡ ቦታውም ወሎ ነው፡፡

ከላሊበላ ከተማ በ42 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሌላ የመድሪቱ አስደማሚ ኪነ-ሕንጻዎችአሉ፡፡ ከታነጹ 900 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ያነጻቸው ደግሞ ቅዱስ ይምርሀነክርሰቶስ ይባላል፡፡ ዋሻ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ቤተ-መንግስትና ቤተከርስቲያንን ፍጹም ውበትን ከግርማ ሞገስ ጋር አጣምረው የያዙ ድንቅ ጥበቦች ናቸው፡፡ ምንም አይነት ምስማርም ሆነ ማያያዣ ሳይኖራቸው ድንጋይ፣ እምነ-በረድ፣ እንጨት እርስ በርሳቸው እየተጣመሩ የቆሙበት ኪነ-ሕንጻ የሚገኘው ወሎ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ኪነ-ሕንጻ ውሀ ላይ ቁጭ ያለ ነው፡፡ ከስሩ ውሀ ነው፡፡ ተአምሩ እና ምስጢሩ ገና አልተጠናም፡፡

ዘርዝሬ የማልጨርሰውን ገዳይ ጀመርኩትና ግራ ገባኝ፡፡ እንደው ለማጠናቀቅ እንዲመቸኝ ከአማራ ክልል በሕልና ተሪዝም በሰበሰብኩዋቸው መረጃዎች ሰብሰብ ልበል፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም

በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በአነጋፋነታቸው ከሚታወቁ ቅዱስ ስፍራዎች ውስጥ ግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም አንዷ ናት፡፡ ከደሴ ከተማ ሰሜን-ምዕራብ 76 ኪ.ሜ ርቅት ላይ የምትገኘውና “ዳግማዊት ኢየሩሳሌም” በመባል የምትታወቀው ይህችው ገዳም ከዕምነትና ከአስተዳደር ጋር የተቆራኙ ታሪኮችን የያዘች ናት፡፡

ኢየስስ ክርስቶስ በቀራኒዮ ተሰቅሎበት ነበር የሚባለው መስቀል የቀኙ ክንፍ በክብር ያረፈው በዚች ገዳም ውስጥ እንደሆነ በከፍተኛ ደረጃ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ገራሸ የሆነቸው እንግሊዛዊት፣ ሲሊቪያ ፓንክረስት ይህን ጉዳይ “ካልቸራል ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ“ በተሰኘ ግዙፍ መጽሀፍዋ በሚገባ ገልጸዋለች፡፡

የግሸን አምባ በተፈጥሮ የመስቀል ቅርጽ አለው፡፡ የአመባው ዙሪያ ለመውጣትም ሆነ ለመውረድ ፍፁም በማይታሰብ እንደምሰሶ ቀጥ ብለው በሚታዩ ገደላ ገደል የመሬት ገፅታዎች የተከበበ ሲሆን ወደ አናቱ ለመውጣት የሚቻለው ተፈጥሮ በአዘጋጀችው አንዲት ብቸኛ ጠባብ መንገድ አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በንጣፍ ድንጋይ የመወጣጫ ደረጃ እስከተሰራለት ድረስ የገዳሟ መነኮሳት አምባውን ለመውጣትም ሆነ ለመውረድ ይጠቀሙበት የነበረው ብቸኛ ዘዴ ወገባቸውን በገመድ ወይንም በመጫኛ አስረው በመጐተት ነበር፡፡

በአምባው ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተተከሉ አራት አብያተ ክርስትያናት አሉ፡፡ የግሸን ማርያምና የእግዚአብሔር አብ አብያተክርስቲያናት መሠረታቸው የተተከለው በእፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ነው ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት ፈርሠው የመሠራትና የመታደስ ዕድል ተጥሟቸዋል፡፡

ግማደ መስቀሉ በመቅደሱ ውሰጥ ተቀብሮ ይገኝበታል ተብሎ የሚታመነው የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደገና የተሠራ ሲሆን በዳግማዊ ምሊኒክ እንዲታደስ ተደርጓል፡፡ አሠራሩ በሌሎች አካባቢዎች ከሚታየው የተለየና በመስቀል ቅርጽ የተሠራ ሆኖ ልዩ ውበት ያለው ነው፡፡

 የግድግዳ ላይ ስዕሎቹም በሌሎች አድባራት አንደሚታዩት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙ ሃይማኖታዊ ታሪኮችን የሚያፀባርቁ ሳይሆን የዘርዓያዕቆብ ስዕላዊ ትርጓሜዎች ናቸው፡፡ ከግማደ መስቀሉ መገኘት ጀምሮ ግሽን እስከገባበት ድረስ ያለውን የሚተርከው ስዕል በቤተመቅደሱ ግድግዳ ዙሪያ ይታያል፡፡ የነገስታቱ ሥዕልም እንዲሁ፡፡

በተመሣሣይ መልኩ የግሽን ማርያም ቤተክርስቲያን በአፄ ዘርዓያቆብ እህት በእማሆይ እሌኒ የተሠራችና በኋላም በአፄ ኃይለስላሴ ባለቤት በእቴጌ መነን እንደታደሰች ይነገራል፡፡ የአሁኗ ግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ቀደም ባሉት ጊዜያት ደብረ ነጐድጓድና ደብረ እግዚአብሔር በመባል ትጠራ ነበር፡፡ ንጉስ ላሊበላ ከድንጋይ ፈልፍሎ ያሰራው ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር አብ ይጠራ ስለነበር ነው ደብረ እግዚአብሔር ትባል የነበረው በማለት የገዳሟ ኃላፊ ይገልፃሉ፡፡ ብዛት ያላቸውን ታሪካዊ ቅርሶች በስርዓት የያዘው ዕቃ ቤት የገዳሟን ታሪካዊነት የሚመሰክር ሌላው መረጃ ነው፡፡

ሎጐ ሐይቅ

ከደሴ ወደ ወልድያ በሚወስደው ዋና መንገድ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ አንዲት አነስተኛ ከተማ ትገኛለች፡፡ ከዚች የሐይቅ ከተማ ወደቀኝ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሎጐ ሐይቅ ወይንም የሐይቅ ሐይቅ ተንጣሎ ይታያል፡፡ ከባህር ወለል 2030 ሜትር ከፍታ ላይ የሚኘው ሐይቅ የ35 አጸፋ ኪ.ሜ ስፋትን፣ 23 ሜትር ጥልቀትን የያዘ ነው፡፡

በዚህ ሀይቅ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ላይ በአንድ ጐኑ ሙሉ በሙሉ ከየብስ ጋር የተገናኘና ውሃውን ወደፊት የገፋ ባህረገብ መሬት ይገኛል፡፡ ይህ ቦታ ጥንት ዙሪያውን በውኃ የተከበበ ደሴት ነበር ይባላል፡፡

በአጼ ድልናኦድ ዘመነ መንገሥት /908-918 ዓ.ም/ ከግብፅ አገር በመጡ አባ ሰላማ በሚባሉ የኃይማኖት አባት አማካኝነት ቤተመቅደስ ተሠርቶ ደሴቱ ላይ ጥንታዊው የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ተገደመ፡፡ በገዳሙ ኢየሱስ ሞኣና አቡነ ተክለኃይማኖት አገልግለዋል፡፡ አፄ ይኩኖ አምላክ ተምረውታል፡፡ በዛጉዌ ሥርወ መንግስት የመጨረሻው ነጋሲ የነበሩትን ይትባረክን ከስልጣን አውርዶ በምትኩ የሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት አካል የነበሩትን ይኩኖ አምላክን ለመተካት ከነአቡነ ተክለኃይማኖት ጋር ሚሲጢራዊ ተግበር የተካሄደው በዚሁ ለወንዶች ብቻ በተፈቀደው ገደም ውስጥ ነበር ይባላል፡፡

ገደሙ በቅርስ ሃብቶች የበለፀገ፣ በተለያየ ጊዜ የገነሡት ነገሥተት በስጦታ መልክ ያበረከቷቸው ውድ ዕቃዎችና ንዋዬ ቅዱሳት እጅግ በርካታ የብራና መጻህፍትን ገድሎችንና ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩ ልዩ ልዩ ቅርሶችን የያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም ወንጌላዊው ሉቃስ ከሣላቸው አራቱ ስዕለማርያም ውስጥ አንዷ በዚሁ ገዳም ውስጥ መኖሯን የገዳሙ ኃላፊ ይገልፃሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በገዳሙ ዙሪያ የተንጣለለውን ሀይቅ፣ የአካባቢውን ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ፣ ከሐይቁ ምግባቸውን አፈላልገው በዙሪያው ባሉት ዛፎች ላይ ተጠልለው የሚኖሩትንና መሥመር ሰርተው በሀይቁ አናት ላይ ከአንዱ ዳርቻ ወደሌላው የሚበሩ የአዕዋፍ ዝርያዎችን፣ የአሣ አጥማጆችን ሕብራዊ እንቅስቃሴን አጣምሮ ማየት ልዩ  ደስታንና የመዝናናት ስሜትን ይፈጥራል፡፡

ጀመዶ ማርያም ገዳም

የጀመዶ ማርያም ገዳም ከወልዲያ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው የዋጃ ከተማ ተገንጥሎ በሚወስደው አስቸጋሪ የእግር መንገድ የሰዓታት ጉዞን በሚጠይቀው የግዳን ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ እንደ ገዳሟ የሃይማኖት አባቶች ገለጻ ጀመዶ ማርያም ከተመሰረተች 1000 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ገዳሟ የምትገኘው ከትልቅ የባልጩት አለት ገደል ስር ርዝመቱ 15 ሜትር፣ ወርዱ 7 ሜትር ቁመቱ ደገሞ በአማካይ 20 ሜትር ከሚሆን ዋሻ ውስጥ ነው፡፡

በዋሻው መሀል በልዩ የግንባታ ጥበብ የታነጸውና ዙሪያውን በቅዱሳን ስዕል ያሸበረቀው የገዳሟ ቤተመቅደስ የረቂቅ ጥበብ አሻራ ነው፡፡ ከስዕሉ መካከል በወንጌላዊው ሉቃስ እንደተሳለች የሚገርላትና ”ምስለ ፍቁር ወልዳ” በሚል መጠሪያ የምትታወቀው የቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል የገዳሟ ልዩ የክብር ምንጭ ናት፡፡ በየዓመቱ ጥቅምት 4 እና ግንቦት 1 ቀን በሚውሉት ክብረ በዓላት “የምስለ ፍቁር ወልዳ” ስዕል በመጋረጃ ተሸፍና፣ ለመቆሚያ በተዘጋጀው የስጋጃ ምንጣፍ ላይ ሲደረስ መሸፈኛው ተገልጦ ስዕሏ ለምዕመናን እንድትታይ ከቀኝ ወደ ግራ ሦስት ጊዜ ይዞራል፡፡ ምዕመናን “ለምስለ ፍቁር ወልዳ” ያላቸውን ሃይማኖታዊ ክብር በእልልታ፣ በሆታና በስግደት ይገልጻሉ፡፡

ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎች የተለያዩ ነዋየ ቅዱሳት በተለይም ከ950 ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት መቋሚያ ከጀመዶ ማርያም ውድ ቅርሶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አሸተን ማርያም

የአሸተን ማርያም ደብረ በቡግና ወረዳ 024 ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ከላሊበላ በስተምስራቅ በተራራ ላይ የምትገኝ ውቅር ቤተክርስቲያን ስትሆን ቦታው ለመድረስ ከላሊበላ ከተማ በበቅሎና በእግር ሁለት ሰዓት ተኩል ያስኬዳል፡፡ ቤተክርስቲያኗ የተሰራችው በአፄ ነአኩቶለአብ መዘነ መንግሥት /1207-1247 ዓ.ም/ ሲሆን ከአንድ ቋጥኝ መፈልፈሏ ከላሊበላ አብያተክርስቲያናት ጋር ያመሳስላታል፡፡ ቤተክርስቲያኗ መጀመሪያ ስትፈለፈል በሦስት በኩል አምዶች ተሰርተውላት የነበረ ሲሆን የአካባቢው ህዝብ በአምዶቹ መካከል የነበረውን ባዶ ቦታ  በድንጋይና በጭቃ በመሙላት እንደ ቤት ተጠቅሞበታል፡፡ ደብሯ ከመደረሱ በፊት በተራራው ውስጥ የተሰራ ሃያ ሜትር ርቀት ያለው መሽዋለኪያ ይገኛል፡፡ ከዚህ መሽዋለኪያ አካባቢ አፄ ላሊበላ ለአሸንተ ማርያም በተክርስቲያን ግንባታ አስጀምሮት ነበር የሚባለለት አንድ ስፍራ አለ፡፡ የአሁኗ አሸተን ማርያም ከዚህ ስፍራ ጥቂት ከፍ ብላ ትገኛለች፡፡

በአሸተን ማርያም ረዥም ዘመን ያስቆጠሩ በጨርቅና በእንጨት ገበታ በውሃ ቀለም የተሳሉ ስዕሎች ይገኛሉ፡፡ ስዕሎቹ ባህላዊውን የቀለም ቅብ አሰራር የተከተሉ፣ በመስመሮችና በወዝ የተሰሩ ናቸው፡፡ /የብርናንና ጥላ አጣጣልን የሚያሳይ ስዕል በወዝ የተሰራ ይባላል፡፡/

ነአኩቶ ለአብ

የነአኩቶ ለአብ ገዳም በቡግና ወረዳ 024 ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ከላሊበላ ከተማ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከላሊበላ ከተማ ወደ ስፍራው የሚደርስ  የመኪና መንገድ አለ፡፡ ይህን መንግድ በመጠቀም ስፍራው ለመድረስ 45 ደቂቃ ይፈጀል፡፡ ገዳሙ ተፈጥሮአዊ በሆነ ዋሻ የተከበበና መግቢያው ላይ በጥርብ ድንጋይ የታነጸ ሲሆን ወደ ደጃፉ ለመድረስ የሚረዳ የድንጋይ ደረጃ አለው፡፡

በገዳሙ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ መጠን ያላቸው ተፈጥሮአዊ የድንጋይ ገበታዎች ከቤተመቅደሱ ጣሪያ ላይ በሚንጠባጠበ የጠበል ውሃ ዘወትር የተሞሉ ናቸው፡፡ ከጐን በሚኘው የዕቃ ቤት የተለያዩ ነገስታት የስጦታና የክብር ዕቃዎች፣ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ ”ስማጐንደር” በሚል መጠሪያ የሚታወቀውና አፄ ነአኩቶ ለአብ ከጦርነት መልስ ይዘውት እንደመጡ የሚገርለት ትልቅ ከበሮና ሌሎች ቅርሶች ይገኛሉ፡፡

በነአኩቶ ለአብ ገደም ውስጥ በዘመኑ የተሰሩ የጨርቅና የገበታ ላይ ስዕሎች አሉ፡፡ ስዕሎቹ የድንግል ማርያምን ምስልና የክርስቶስን ስቅለት የሚያሳዩ፣ የአፄ ነአኩቶለአብን ንግስና ገድል የሚዘክሩ ሆነው በወፍራም የውሀ ቀለም የተሳሉ የወዝ ስራዎች ናቸው፡፡

ነገተ ማርያም

ከላሊበላ ወልድያ መንገድ በመገንጠል 2 ኪ.ሜ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ከላሊበላ ከተማ 31 .ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው የገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን ከአንድ ቋጥኝ ተፈልፍሎ የተሰራ ውቅር ህንፃ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኑ በ1260ዎቹ በአፄ ይኩኖ አምላክ እንደተሰራ ይነገራል፡፡ በበጋ ጊዜ ወደ ደብሩ የሚያስጠጋ ጥርጊያ የመኪና መንገድ አለ፡፡

የገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን አሰራር አንዱ የላሊበላ አብያተክርስቲያናት የቤተ መድሃኒዓለምን ይመስላል፡፡ ህንፃው ከተፈለፈለበት ቋጥኝ ገደል ነፃ ሆኖ ለብቻው የቆመ ነው፡፡ በዙሪያው ያለው የተጠረበ ቋጥኝ እንደ አጥር የሚያገለግል ሲሆን በመግቢያው በር ግራና ቀኝ የመስቀል ቅርጽ ተሰርቶበታል፡፡ በአካባቢው ከተፈለፈሉና እስካሁን ከሚታወቁት ውቅር ህንፃዎች የገነተ ማርያም ደብር በዕድሜ አነስተኛ ነው፡፡

በህንፃው ውስጥ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ባህላዊ የስዕል አሳሳል የተከተሉ የግድግዳ ላይ የቀለም ቅብ፣ የጨርቅ ላይ ቀለም ቅብና የገበታ ላይ ስዕሎች ይገኛሉ፡፡

ብልባላ ጊዮርጊስ፣ ብልባላ ጨርቆስ ከገነተ ማርያምና ከላሊበላ አብያተክርስቲያናት ጋር በተጓዳኝ ወሎን የሚያስጠሩ ታሪካዊ ቅርሶች ናቸው፡፡

አቡነ አሮን

አቡነ አሮን ገዳም በመቄት ወረዳ ከክፍለ ቋት ከተማ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘውና አግሪት ከምትባለው ትንሽ መንደር በስተሰሜን የ1፡30 የእግር መንገድ ያስኬዳል፡፡ ገዳሙ የታነፀው በ1330ዎቹ፣ አቡነ አሮን በተባሉ የሃይማኖት አባት እንደሆነ አዛውንቶች ይናገራሉ፡፡ ደብሩ በዋሻ ውስጥ ተፈልፍሎ የተሰራ ሲሆን የተለያየ ስፋት ያላቸው አምስት ክፍሎች፣ አስራ አራት አምዶች፣ ሁለት በሮችና ሰባት መስኮቶች አሉት፡፡ የደብሩ መግቢያ በር ባለ ሁለት ተካፋች ሲሆን ከሰባቱ መስኮቶች አንዱ በጣሪያው ላይ ይገኛል፡፡ መስኮቱ መዝጊያ የሌለው በመሆኑ በፀሐይ ጊዜ  በተወሰነ ሰዓት ብርሃን ያስገባል፡፡ በዝናብ ጊዜ ግን ምንም ውሃ እንደማያስገባ የደብሩ ካህናት ይጋራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህን መስኮት ስቁረት በሚል መጠሪያ ይጠሩታል፡፡

አቡነ አሮን ቋጥኙን ፈልፍለው ገዳሙን ከመስራታቸው በፊት ትዕምርተ መስቀላቸውን ተክለው ፀልየውበታል በሚባለው ስፍራ ላይ ውሃ አለ፡፡ ዋሻውን ለመፈልፈል የተጠቀሙበት መጥረቢያም በማህደር ሆኖ ተቀምጧል፡፡ የገዳሙ ግብር የሚወቀጥባቸው ሁለት ሙቀጫዎች አሉ፡፡ የደብሩ ካህናት እንደሚሉት ከሙቀጫዎቹ አንዱ “ከእምባጮ” የተሰራ ነው፡፡

ከጥንታዊ ስዕሎችና የብራና መጻሕፍት በተጨማሪ የበርካታ አዛውነትና ህፃናት አጽም በገዳሙ ይገኛል፡፡ አጽሙ የነማን እንደሆነና ለምን እንደተቀመጠ በውል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከገዳሙ ቅድስት ውስጥ ካለው መንበር ስርም የአቡነ አሮን መካነ መቃብር ይገኛል፡፡

ዋግ ኸምራ

ዋግኸምራ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዞን መስተዳድሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በሰሜንና በምስራቅ ከትግራይ፣በደቡብ ከሰሜን ወሎ፣ በምዕራብ ከሰሜንና ደቡብ ጐንደር ጋር ይዋሰናለ፡፡ የዞኑ የቆዳ ስፋት 744500 ሄክታር ሲሆን 300ሺ ያህል ህዝብ እንደሚኖርበት ይገመታል፡፡ በዞኑ ውስጥ የሚገኙት ሦስቱ ወረዳዎች ሰቆጣ፣ዝቋላና ደሀና ይባላሉ፡፡ የዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ ስትሆን ታሪካዊና ረዥም ዕድሜ ካስቆጠሩት የኢትዮጵያ ከተሞች የምትፈረጅ ናት፡፡ ከወልድያ ከተማ 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የዋግ ኸምራ ዞን አማርኛና ትግርኛ ተናጋሪ በሆኑ ሕዝባች መሀል የሚገኝ በመሆኑ የህዝቡ የቋንቋና የባህል ገጽታ ከአማራውና ከትግሬው ቋንቋ ባህል ጋር በአብዛኛው የተወራረሰ ነው፡፡ በዞኑ በቀደምትነት ሲነገር የቆየው አንጡራ ቋንቋ ኻምጣኛ ወይንም ኸምጣኛ ይባላል፡፡ ኻምጣኛ የሚሉት ዝቋላና ሰቆጣ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙት ተናጋሪዎች ሲሆኑ ኸምጣኝን የሚሉት ደግሞ ከተከዜ በስተምዕራብ ያሉት መሆናቸውን ዴቪድ አፕልያርድ የተባሉ የቋንቋ ምሁር ይገልፃሉ፡፡ ኻምጣኛ ተናጋሪ ባልሆኑ አጐራባች ሕዝቦች ዘንድ ቋንቋው አገውኛ በመባል ይታወቃል፡፡ የቋንቋ ምሁራን ኻምጣኛን በኩሻዊ ቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የማዕከላዊ ኩሽ ንዑስ ቤተሰብ አባል አድርገው ይፈርጁታል፡፡ በዚህ ንዑስ ቤተሰብ ውስጥ የሚካተቱት የአገው ቋንቋዎች ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ኻምጣኛ፣ ብሌንኛ እና ቅማንትኛ ናቸው፡፡

በባህላዊ አሰራር በክብ ቅርጽ ከድንጋይ የሚሰሩት ባለአንድ ፎቅ የሳር ክዳን ቤቶች የጎብኝዎችን ቀልብ ይስባሉ፡፡ ከፊሎቹ የቆርቆሮ ክዳን የለበሱ ሲሆን በአካባቢው አጠራር “ህድሞ” ይባላሉ፡፡ በተመሳሳይ ቅርጽ በላሊበላ ከተሰሩት ጥንታዊ ቤቶች ጋር እጅግ ይመሳሰሉሉ፡፡

መስቀለ ክርስቶስ

የመስቀለ ክርስቶስ ውቅር ቤተክርስቲያን ከሰቆጣ ከተማ ደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ 5 ኪ.ሜ. ርቆ ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያኑ የሚገኝበት ስፍራ ልዩ ስሙ ”ውቅር አባ ዮሃንስ” ይባላል፡፡ የመስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በአፄ ካሌብ ዘመን መንግስት /495-525 ዓ.ም/ ከአንድ አለት ተፈልፍሎ እንደተሰራ ይነገራል፡፡ የተፈለፈለበት የድንጋይ ዓይነትና የአፈላፈሉ ዘዴ ከላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል፡፡ ቤተክርስቲያኑ በአራቱም ጐኖች ከተፈለፈለበት ቋጥኝ ተለይቶ የቆመ ሲሆን በምዕራብ በኩል ጣሪያው ከቋጥኙ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በዕድሜ ብዛትና በእንቅብካቤ ጉድለት ምክንያት በህንጻውና በውስጡ ይገኙ ነበበሩት ጥንታዊ ስዕሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከቀሩት ጥቂት የደብሩ ስዕሎች ለመረዳት እንደሚቻለው የአሳሳሉ ጥበብ ጥንታዊውን ዘዴ የተከተለ ሲሆን ስዕሎቹ የተሰሩት በጭቃ ሞርታር ግድግዳው ላይ በተለፈጠ ጨርቅና በውቅር ህንፃው ላይ በተቀባ የኖራ ቀለም  ላይ ነው፡፡ ስዕሎቹ የውሃ ቀለምና የቀለም ቅብ ስራዎች ናቸው፡፡ በመስመሮች የነገሮችንና የገጾችን ተምሳሌነት የሚያሳዩ የወዝ ሥራዎችም ይታይባቸዋል፡፡ በእነዚህ የአሳሳል ዘዴዎች የተሰሩት ስዕሎች በቤተክርስቲያኑ ደጀሰላም ግድግዳ ላይ በመግቢያው በርና በቋሚ ምሰሶዎች ላይ ይታያሉ፡፡

አስክሬንን አድርቆ በማስቀመጥ ጥበብ ተዘጋጅተው ለረዥም ዘመናት እንደተቀመጡ የሚነገርላቸው የበርካታ ሰዎች አካላት በቤተክርስቲያኑ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አስከሬኖቹ የተገነዙት በቆዳ ሆኖ ቆዳዎቹ በትናንሽ እንጨት መሰል ቁልፎች እንዲያያዙ ተደርጓል፡፡

ገታና የገታ አንበሣ

ከአዲስ አበባ 375 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ አካባቢ ታሪካዊነት ያላቸውን የተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ ከከተማዋ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው ዋና መንገድ 12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የጨቆርቲ መንደርን ያገኛሉ፡፡ ከዚች መንደር ወደግራ 4 ኪ.ሜ ገብተው ነው በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለውን የገታ ቅዱስ ቦታና ጥልቅ የታሪክ ፍተሻ የሚያስፈልገውን የገታ አንበሣን የሚያገኙት፡፡

ገታ መውሊድን ምክንያት በማድረግ በያመቱ ደማቅ ክብረበዐል የሚደረግበት ስፍራ ሲሆን በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና ከዓረቡ ዓለምም ሳይቀር ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ መጉረፍ የተለመደ ባህላዊ ትርዒት ነው፡፡ ገታን ያቀኑት ቀደምት የሃየማኖቱ መሪዎች አዕፅምት በአንድ ክፍል ውስጥ በክብር ተቀምጠው  ይገኛሉ፡፡

ከጋታ ግቢ ጥቂት ርቀት ላይ የሚገኘው ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራው የአንበሣ ምስል ሌላው ትኩረትን የሚስብ ቅርስ ነው፡፡ ይህ የአንበሣ ምስል በከፊል አየር ላይ የተንጠለጠለ ሲሆን አብዛኛው የሰውነት ክፍሉ ከዋናው አለት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ይህ ምስል መቼ ለምነና በማን እንደተቀረጸ በውል የሚታወቀ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ በአንበሳው ምስል ፊት ላይ የመስቀል ቅርጽ የሚገኝ ሲሆን ከጐኑ ደግሞ የሳባውያን ፊደላትን የሚመስሉ ቅርጾች ይገኙበታል፡፡ አንዳንድ አዛውንቶች ምስሉ በክርስትና እምነት ተከታዮች በጥንት ዘመን እንደተሰራ ይናገራሉ፡፡ ዛሬ በአካባቢው ያሉት ነዋሪዎች ሙስሊሞች ናቸው፡፡

አንዳንድ አባቶች እንደሚሉት የገታ አንበሣ በክርስትና እምነት ተከታዮች የተሰራ ሲሆን የመስቀሉ ምስልም የሚጠቁመው ይህንኑ መላምታዊ ግምት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዛሬ በአካባቢው ብዙ ሙስሊሞች የሚኖሩ ሲሆን በመንደሩ ውስጥ የሚገኘውና ታላቅ ክብር የሚቸረው የገታ መስጊድም የዕለት ተዕለት ስርዓቱን እየሠጠ ይገኛል፡፡

ከኮምበልቻ ከተማ 60 ኪ.ሜ. ርቀት ወደ አሰብ በሚወስደው አውራ ጐዳና ላይ ባቲ ትገኛለች፡፡ ዘወትር በዕለተ ቅዳሜ በተለየ ሁኔታ ደመቅ የሚለውና የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአርጐባና የአፋር ብሔረሰቦችን በአንድነት የሚያገናኘው የሜዳ የገጠር ገበያ በተፈጥሮ ደም ግባት የሚጐላውን የባህላዊ አለባበስና አጋጊያጥ ስብጥር የሚያሳይ ምቹ መድረክ ነው፡፡ ትዕይንቱ በማይረሳ ትዝታ መንፈስን ይመስጣል፡፡

ከጉዞ በፊትም ሆነ በኋላ አረፍ ብሎ ንፁህ አየር ለመሣብና አካባቢውን ለማድነቅ የኮምቦልቻ ከተማ የተመቸች ናት፡፡

ከኮምቦልቻ ከተማ በዋናው መንገድ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የደሴ ከተማ ትገኛለች፡፡ ከአዲስ አበባ ሰሜናዊ ምስራቅ አቅጣጫ 400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ደሴ በሰሜን ማዕከላዊ ከፍተኛ ቦታዎች ምስራቃዊ ጫፍ ላይ የምትገኝ ደመቅ ያለች ከተማ ናት፡፡ የመንገዱን ግራና ቀኝ ማራኪ የተፈጥሮ አቀማመጥ እያደነቁ ወደ ደሴ ለመጓዝ የየብስ ትራንስፖርት ይመረጣል፡፡ ለፍጥነትና ለተሻለ ምችት በአውሮኘላን እስከ ኮምቦልቻ ተጉዞ ቀሪውን 25 ኪ.ሜ በመኪና በመጓዝ ደሴ መድረስ ይቻላል፡፡ ከተማዋ በከፍተኛ ስፍራ ላይ የተቆረቆረች ብትሆንም ዙሪያዋን በጦሳ ተራራ የተከበበች ናት፡፡ የጦሳ ተራራ የደሴ ከተማን ከቅርብ ርቀት ከላይ ወደታች ለመመልከት እጅግ ተስማሚ ስፍራ ነው፡፡

ከተማዋ ደሴ ከመባልዋ በፊት ላኮመልዛ በሚል ስም ትታወቀ ነበር፡፡ የደሴ ከተማ መስራች የልጅ እያሱ አባት ንጉስ ሚካኤል አሊ ናቸው፡፡ ንጉሱና ተከታዮቻቸው ቋሚ መቀመጫቸውን ደሴ ላይ ካደረጉ በኋላ ከተማዋ ቀስ በቀስ እየለማችና እያደገች በመሄድ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ  ካሉት ጥቂት ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ደሴ አካባቢዋንና ውስጧን ለሚጐበኙ ቱሪስቶች አመቺ የመዝናኛና ታሪክን የማወቂያ ስፍራዎች አሏት፡፡ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት የአይጠየፍ አዳራሽ የደሴ ሙዚየምና የወሎ ባህል አምባ የየበኩላቸውን ታሪክና ቅርስ በመያዝ ለተመልካች ልዩ ስሜትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ናቸው፡፡

አይጠየፍ በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ ተንቀሣቃሽ ድንኳናቸውን ተክለውበት እንደነበር በሚነገረው ጀም በሚል መጠሪያ በሚታወቀው ኮረብታ ላይ የማገኝ በጣም ሰፊና ግርማ ሞገስ ያለው አዳራሽ ነው፡፡ የከተማዋን እድሜ የሚጋራው ይኸው አዳራሽ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ሚካኤል የተገነባ እንደሆነ የነገራል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ባላባቶች ሰውን ከሰው ሳይመርጡ ግብር የሚያበሉበት ስለነበር አይጠየፍ የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው ይባላል፡፡

ወሎ ባህል አምባ የከተማዋን የቀርብ ጊዜ ታሪክ ገሃድ የሚያደርግልን በፋሺስት ኢጣሊያ የአምስት ዓመት /1928-1933/ ቆይታወቅት የተሠራ አዳራሽ ነው፡፡ አዳራሹ የተሰራበት ቁሳቁስ ከጣሊያን በተለይም ከሚላኖ ከተማ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በዚህ ታላቅ የሲኒማ አዳራሸ አዝናኝ ሲኒማዎች ቲያትርና የሙዚቃ ትርዒቶች ይቀርቡበታል፡፡

የደሴ ሙዚየም በአገሪቱ በዞን ደረጃ ከሚገኙ ሙዚየሞች ቀዳሚው ነው፡፡ የተለያዩ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሦች በአካል የሚታዩበት በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙት ብርቅዬ የዱር እንስሣት መካከል የሰሜን ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ እንዲሁም የሌሎች እንሥሣት የውስጥ አካላቸው ወጥቶ ውጫዊ የተፈጥሮ ቀርጻቸው ሣይዛባ በታክሲደርሚ ጥበብ ደርቀው ለዕይታ የቀረቡበት በተጨማሪም የተለያዩ ገላጭ ፎቶግራፎች የሚገኙበት ሙዚየም ነው፡፡

ከደሴ በቅርብ ርቀት የጐብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ስፍራዎች ያሉ ሲሆን ቦሩ ሜዳ ግሸን መቅደላ አምባ ሐይቅ እስጢፋኖስ ውጫሌ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ቦሩ ሜዳ

በባላባታዊ ስርዓት የኢትዮጵያ ገዢዎች ጠባቂዎቻቸውን አማካሪዎቻቸውንና ባለሟሎቻቸውነ ይዘው ለእረፍትና ለሌሎች ጉዳዮች ወደተለያዩ አመቺ ስፍራዎች የመጓዝ ልምድ ነበራቸው፡፡ ከእነዚህ የነገስታቱን አይን ከማረኩት ቦታዎች አንዱ ቦሩ ሜዳ ነበር፡፡

አፄ ዮሀንስ በተገኙበት በጐጃሙ ንጉሥ ተ/ሃይማኖትና በሸዋው ንጉሥ ምኒሊክ መካከል የነበረውን የስልጣን ሽኩቻ ለማወስወገድ ውይይትና እርቅ የተካሄደው የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያነ ሥርዓትን በተመለከተ በነበረው ልዩነት ላይ ስምምነት የተደረሰው ከአፄ ዮሐንስ አረፍት በኋላ ንጉስ ምኒሊክ በእግራቸው መተካታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጁትና ነጋሪት ያስጐሸሙት ከደሴ ከተማ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ገደም በሚወስደው መንገድ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ቦሩ ሜዳ ላይ ነበር፡፡

ፍቅሬ ገና ነው፡፡ ወሎን አውርቼላት ተናግሬላት አልጨርስም ገና እንጓዛለን፡፡ ከደጋጎቹ አገር፡፡ እንዴትነሽ ሀገሬ….

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top