Connect with us

ሙሼ ሰሙ እንደፃፈው!..

ዛሬና ትናንት የብዙ ሰዎችና የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት የሳበ ጉዳይ በመሆኑ የግል ምልከታዩ እነሆ:-
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ሙሼ ሰሙ እንደፃፈው!..

ሙሼ ሰሙ እንደፃፈው!..

በመጀመርያ ሰራዊታችን ከክልል ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ላጎናጸፈን ድል አክብሮቴን እገልጻለሁ። 

ጦርነትን በስኬት ለማጠናቀቅ ኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ነው፡፡  በጥንቃቄ የማይታቀድና በአግባቡ የማይመራ ኢኮኖሚ  ጦርነቱን በማራዘም እጥረትና የደጀን መሰላቸት አስከትሎ ጦርነቱንና ውጠቱን ፈታኝ ስለሚያደርገው ጦርነቱን ለማሸነፍ ኢኮኖሚውን ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።

ማንኛውም ጦርነት ፋይናንስ የሚደረገው በሶስት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛው ከዜጎች በሚሰበሰብ ግብር  ነው፡፡ ሁለተኛው በብድር ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ግሽበት (Inflation Financing) ነው፡፡ ጦርነቱን በብድር፣ በከፍተኛ የግብር ጫናና “መዋጮ”ብቻ ፋይናንስ የሚደረግ ከሆነ ጫናው ሲበዛ ልማቱና እድገቱን በማኮማተር ኢኮኖሚውን ሊያናጋው ይችላል፡፡ 

ኢኮኖሚያዊ መናጋቱም ማህበራዊ ቀውስን በመፍጠር ሰላማዊ ሕይወትን መምራትም ሆነ ጦርነቱን ማካሄድን ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ኢኮኖሚ ሁለተኛው የጦር ግንባር ነው የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡   

የጦርነት ኢኮኖሚ እንደ ሃይማኖት ቀኖና የለውም፤ የትርፍ ሰዓት ስራም አይደለም፡፡ ከጦርነቱ እኩል ልዩ ትኩረትን ይሻል፡፡ ጦርነቱን ለማሸነፍም ሆነ የጦርነትን ዘለቄታዊ ጠባሳን ለመጠገን አቅምህን አስተባብረህ፣ አሟጦ ከመጠቀም ባሻገር የርዕየተ ዓለምህን የረድፍ አሰላለፍ ማስተካከል ግድ ሊልህ ይችላል፡፡ አሜሪካ የምታወግዘውንና የምታሳድደውን “ሶሻሊዝም” በ1940ዎቹ በ2ኛው የዓለም  ጦርነት፣ በ1950ዎቹ በኮርያ ጦርነት ወቅት ለመቀበል ተገዳ ነበር፡፡

አሜሪካ በ2ኛው የዓለም ጦርነት 2.2 ቋሚና 34 ሚሊየን በጎ ፈቃደኛ ወታደሮችን መልምላለች፡፡ ይህን ሃይል ለማደረጀት ለማስታጠቅና ለማዝመት መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግርን ጠይቋታል፡፡ ስንቅና ትጥቆችን ለማምረት ነባር ኢንዱስትሪዎችን ወደ ጦር መሳርያ ማምረቻነት መለወጥ፣ አዳዲስ የጦር መሳርያ ማምረቻ ፋብሪካዎችን መትክል፣ ለሲቪል የፍጆታ አጠቃቀም ስርዓትን ማበጀት፣ አላስፈላጊ የቅንጦት እቃዎችን ከምርት ሰንሰለት ማስወገድና ከውጭ ማስመጣትንም አግዳ ነበር፡፡

ደጀኑ (Home Front) እንደ “ቪክትሪ ጋርደን” ባሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች አማካኝነት በጓሮውና በይዞታው ላይ የራሱን ምርት በማምረት መደበኛውን ምርት እንዲያግዛና ቁጠበን ባህል እንዲያደርግ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡ ውሳኔዎቹ እስከ 20 ሚሊየን ( 10 ሚሊየኑ ሴቶች ናቸው) የሚደርሱ የስራ እድሎችን ከመፍጠራቸውም በላይ ከጦርነቱ በኃላ ኢኮኖሚው ከደረሰበት ጉዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ አንሰራርቶና ጠንክሮ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ከእኛስ ምን ይጠበቃል፡፡ ለጊዜው ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ብቻ ላንሳ። አንደኛው ከመንግስት በኩል የሚጠበቅ ነው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ላይ ሆነን በተለመደ መንገድ ( Business as usual) ስራን መከወን አይቻልም፡፡ በእለት ከእለት ስራ በተጠመዱ የሚኒስትር መስርያ ቤቶች አማካኝት ስራን መከወን ውጤቱ እዘጭ እንገጭ ከመሆን አይዘልም፡፡ የእለት ከእለት ስራቸው የሚያንገዳግዳቸው ተቋማትን የሚያግዙ አዳዲስ አደረጃጀቶችንና አወቃቀሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት አሜሪካ ( Office of Price Administration, Office of Economic Warfare, Office of War Mobilization and Reconversion) የመሳሰሉ ተቀማት አቋቁማ ነበር፡፡

ሌላው መንግስት ተቋሞቹ በጥብቅ የቁጠባ ዲሲፕሊንና ፖሊሲን እንዲመሩ፣ ኃላፊዎቹም በሀገሪቱ አቅም ልክ ቢሮዎቻቸውን እንዳመሩ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ የስራ ሰዓትን ማክበር፣ መስተንግዶን ማቀላጠፍና ዘመቻ ባህል እንዳይሆን ተጠንቅቆ ጦርነቱ የሚነጥቀንን የጊዜ፣ የሰው ኃይልና የሀብት ብክንትን ለመሻማት፤ በተጨማሪ የስራ ሰዓት አማካኝነት በጎ ፈቃደኞች ያለ ክፍያ በዘመቻ የሚያግዙበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በምርት አቅርቦትና ግብይት መካከል ያለውን የተዛባና የተራዘመ ሰንሰለት በመበጣጠስ የዋጋ ንረትና እጥረት መቋቋም አለበት።

ሁለተኛው ከሕዝብ የሚጠበቅው ነው ( Home Front)፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የሚያባክነውና የሚያድፋፋው ሀገራዊ ሀብት ኮሮና፣ ጦርነትና የተፈጥሮ ችግር በተፈተነው ኢኮኖሚ ላይ የሚጥለው ተጨማሪ ጠባሳ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ እንደ ብክንት፣ ዝርክርክነት፣ ስግብግብነትና አለመቆጠብ ያሉ ኃላ ቀር ባህሎች በኢኮኖሚው ላይ የሚስከትሉት መዘዝ ዘላቂና ተቀጣጣይነት ያለው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። 

ኃላፊነት መሰማትና ተቆርቋሪነትን ባህል መሆን አለብት፡፡ ገንዘብ ስላለን ብቻ ያላመረትነውንና ያሻንን ትርኪ ምሪኪ ሁላ በውጭ ምንዛሪ እየሸመትን ያለገደብ መቀራመትን ጋብ እናድርግ፡፡ ለእጥረትና ለንረት መንግስትን ብቻ ማመረር መፍትሔ አይደለም፡፡

መብራት፣ ውሃ፣ የነዳጅ ውጤቶችን፣ ስፔር ፓርቶችን፣ ጎማና ሌሎች ወሳኝ የፍጆታ አቅርቦቶችን እንቆጥብ ከሚያስፈልገን በላይ በመግዛትም (Horde) ሆነ በመጠቀም (Wastage) ኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ ከመፍጠር እንቆጠብ፡፡ ሀገር በጦርነት ላይ ነች፡፡ የሀገራችን ልጆች በባዶ ሆድ፣ በሀሩርና በጥም እየተቃጠሉ መስዋእትነት እየከፈሉ ነው፡፡ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ዋጋ በመጫንም ሆነ ፍጆታ በመሰወር የምናደርገው ሕገ ወጥ የስግብግበነት ተግባር በዘማች ቤተሰቦችና ወገኖች ላይ የሚሰራ የግፍ ግፍ መሆኑን አንርሳ፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top