“ባንዳዎች ሁሌም ተሸናፊዎች ናቸው”
~ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ኢትዮጵያን ሸጠው ለማትረፍ የሚጥሩ ባንዳዎች ሁሌም ተሸናፊዎች ናቸው፤ የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በቆራጥ ልጆቿ ተከብሮ ለዘልአለም ይኖራል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ።
አሸባሪው ሕወሃት ሲፈጠርም ኢትዮጵያዊነትን በማክሰም የተበታተነች አገር በመፍጠር ሃብቷን የመቀራመት እቅድ ይዞ ነበር የተነሳው።
በ1968 ዓ.ም እውን ባደረገው ማንፌስቶው ትግራይን የኢትዮጵያ አካል ባለማድረግ ህዝብን ጠላት አድርጎ በመፈረጅ ባንዳነቱን ያረጋገጠ ሃይል መሆኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን በተቆጣጠረባቸው ዓመታት ኢትዮጵያ የምትባል አገር አንዳትኖር አሸባሪው ህወሃት ብዙ ሰርቷል ።
አሸባሪው ህወሃት በ27 ዓመታት ፖለቲካውን በበላይነት ተቆጣጥሮ በኢትዮጵያ ያልፈፀመው በደል፣ ያልዘረፈው ንብረትና ያልፈፀመው ሴራ አልነበረም።
በደሉና ግፉ የበዛበት የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ ያሽቀነጠረው የጥፋት ስብስብ “ባልበላውም በመጫር ላፍስሰው” ብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውስጥ ባንዳ ሆኖ ከውጭም ጋብዞ ለጥፋት እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና የአሸባሪውን ህወሃት እኩይ ዓላማ በሚመለከት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዲህ ያብራሩታል።
በታሪክ አጋጣሚ ሁሉ የኢትዮጵያ የውጭ ጣላቶች በውስጥ ባንዳዎችን በመመራት ያደረጉት ጥረት ሁሉ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን አስታውሰው አሁንም ይሁን ወደፊት ኢትዮጵያ በባንዳዎች አትሸነፍም ሲሉ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን ሸጠው ለማትረፍ ከሚሹ የውስጥ ባንዳዎች ጋር ኢትዮጵያዊያን እየተፋለሙ አሸንፈውና አሳፍርው እየመለሱ ክብሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቀው ኖረዋል አሁንም የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በቆራጥ ልጆቿ ተከብሮ ለዘልአለም ይኖራል ብለዋል።
“አሸባሪው ህወሓት የተደራጀ ባንዳ ነው” የሚሉት ዲያቆን ዳንኤል፤ ከመነሻውም ባንዳነትን ይዞ የስውር መዋቅር ዘርግቶ ሲሰራ ኖሮ አሁን ላይ ደግሞ ግልጽ አገር የመሸጥ አጀንዳውን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ምዕራባውያኑ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን በማንበርከክ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ መሆኗ እንዲቀር እየሰሩ ይገኛሉም ነው ያሉት።
የአፍሪካ ፅኑ መሰረት የሆነችውን ኢትዮጵያ በማንበርከክ አህጉሩን የማተራመስ ዓላማ ይዘው መምጣታቸውንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ የመሪዎች መዝመት አዲስ አለመሆኑን ጠቅሰው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በግንባር በመገኘት ሰራዊቱን መምራት የዘመኑ ሌላ ታሪክ ሲሆን ለቀጣይ መሪዎች ደግሞ በአርያነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን መሪ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ዳያቆን ዳንኤል ገልጸዋል። (ኢዜአ)