የኃያላኑ አዲሱ የፍልሚያ ግንባር ….
(እስክንድር ከበደ – ድሬ ቲዩብ )
በአንድ ወቅት አውሮፓውያን ” ጭለማዋ አህጉር ” የሚሏት አህጉር ናት፡፡ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ዘመን ባብዛኛው ብሪታኒያና ፈረንሳይ ተቃርጠው በዛብዘዋታል፡፡ሁለቱ ኃያላን ለጥሬ እቃዎችን፣ለባሪያ ንግድና ጂኦፖለቲካዊ ተጽኖ የሚፎካከሩባት አህጉር ነበረች፡፡ዓለም ለአንድ ክፍለዘመን ያህል ዘንግቷት ቆይቷል፡፡
አሁን በ21ኛው ክፍለዘመን ከቅኝ ግዛት ጋር ባብዛኛው የሚመሳሰል የኃያላን ፉክክር እያስተናገደች ይመስላል፡፡ አሜሪካ ፣ቻይና ፣ህንድ ፣ ጃፓን ፣ከናዳ፣እስራኤልና የአውሮፓ ህብረት ሀገራት አህጉሪቱን ለመቆጣጠር ሩጫ ጀምረዋል፡፡አንድ ሀገር አሸናፊ እየሆነች መጥታለች፡፡
ይህቺ አህጉር አፍሪካ ናት፡፡ የ53 ሉኡላዊ ሀገራት አህጉር ነች፡፡ የከዓለም ህዝብ ቁጥር 17 በመቶ ህዝብ ይኖርባታል፡፡ 9 ነጥብ 6 በመቶ የዓለምን የነዳጅ ዘይት ምርት ድርሻ ይዛለች፡፡ከፕላቲኒየም ማአድን አቅርቦት 90 በመቶ ትሸፍናለች፡፡ በዓለም 90 በመቶ የኮባልት ማአድን አምራች ነች፡፡ የዓለም የወርቅ ማአድን ሀብት ውስጥ ገሚሱን የምትሸፍን አህጉር ናት፡፡ የዓለም ሁለት ሶስተኛውን ማንጋኒዝ ማአድን መጠን አቅራቢ ነች፡፡
35 በመቶ የዓለማችን የዩራኒም ድርሻ በአፍሪካ ይገኛል፡፡ 75 በመቶ የዓለም ኮልተን ማአድን ድርሻ ትይዛለች፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ 54 ድምጾች አሏት፡፡ እነዚህ አፍሪካን ለዓለም ኃያላን የፍልሚያ ሜዳ እንድትሆን የሚዳርጉ ናቸው፡፡
የአውሮፓ ህብረት እ.ኤ.አ በ2020 ለአፍሪካ ሀገራት ”ዘላቂ ልማት ” 54 ቢሊዮን ዶላር የኢቨስትመንት እንደሚመድብ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ የ1.3 ቢሊየን ህዝብ አህጉር በሆነችው፤ የአፍሪካ ገበያ ለመቆጠጠር ፍላጎት ነው፡፡ ህብረቱ ከ40 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ነጻ ገበያ ስምምነት ድርድር አደረገ፡፡ ይህ ግን የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥን የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡
በአፍሪካ ረዥሙን ኢትጵያና ጂቡቲን የሚያገናኘውን የባቡር ሀዲድ ጨምሮ 6ሺህ 200 ኪሎሜትር የሚረዝም የባቡር ሀዲድ ገንብታለች፡፡ ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በ33 የአፍሪካ ሀገራት 50 የኮንፊሸየስ ኢንስቲትዩት አቋቁማለች፡፡ በርካታየአፍሪካ ሀገራት የቻይናን ገንዘብ ምንዛሬ ይጠቀማሉ፡፡
ቻይና በውጭ ሀገር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው የወታደራዊ ምድብ አግኝታለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የጦር ሰፈር በአፍሪካ ቀንድ በጂቡቲ ከፍታለች፡፡ ጂቡቲ ህንድ ውቅያኖስን ከሜዴትራኒያ ባህርን ከህንድ ውቅያኖስ ጋር በሲዊዝ ቦይ አማካኝነት የምታገናኝ ስትራቴጂክ ስፍራ ላይ ትገኛለች፡፡ የጦር ሰፈሩ 10 ሺህ ወታደሮችን የማስፈር አቅም አለው፡፡ ቻይና ሸቀጣሸቀጦቿን የምታራግፍበት ገበያ አግኝታለች፡፡
ቻይና ትልቋ የአፍሪካ የንግድ አጋር ናት፡፡ባለፈው አንድ አስርት አመት ቻይና በአፍሪካ የንግድ መጠን 40 በመቶ እጥፍ እድገት ማሳየቱ ይነገራል፡፡ እንደ ሜካንዚ ጥናት ከሆነ 10ሺህ የቻይና ኩባንያዎች በመላ አፍሪካ በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት፡፡ ቻይና ደግሞ የገበያ ተደራሽነትን ትይዛለች፡፡ቻይና በአፍሪካ በ3ኛ ደረጃ በማአድን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ያላት ተሳትፎ ነው፡፡
በአፍሪካ ትልቁ ኢንቨስትመንት የቻይና ብቻ አይደለም፡፡ የአሜሪካም ድርሻ ትልቅ ነው፡፡አሜሪካ ከአፍሪካ ያላት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ድርሻ 54 ቢሊየን ዶላር ደርሷል፡፡በደቡብ አፍሪካ ብቻ 600 የአሜሪካ ኩባንያዎች አሉ፡፡ በግብጽ ከ1ሺህ የሚልቁ የአሜሪካ ኩባንያዎች እንዳሉ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መናገራቸው ይታወሳል፡፡አፍሪካ የዋሽንግተንና የቤጂንግ አዲስ አውደ ግንባር እየሆነች መምጣቷ ምልክቶች እየታዩ ናቸው፡፡ ለአያሌ አመታት አፍሪካ ለዋሽንግተን ከጦርነት ቀጠናነት ያለፈ ፋይዳ አልነበራትም፡፡
አሜሪካ 7ሺህ ወታደሮች በ13 የአፍሪካ ሀገራት አሏት፡፡ ዋሽንግተን ወታደሮቿን በጸረ ሽብር ዘመቻ ስም ቡኪናፋሶ ፣ካሜሮን፣ማአከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ቻድ ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፣ኬኒያ፣ሊቢያ፣ማሊ ፣ሞሪታኒያ፣ኒጀር ፣ደቡብ ሱዳን፣ሶማሊያና ቱኒዚያ አስገብታለች፡፡ አሁን አሜሪካና ቻይና አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ የርዕዮተአለም ሳይሆን ፤የአፍሪካን ንግድና ኢንቨስትመንት በበላይነት የመቆጣጠር ፉክክር ይዘዋል፡፡
እንደ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ የሰፈረ መጣጥፍ ከሆነ ፤”አፍሪካ የመጪ ጊዜ አህጉር ስለሆነች አቅሟን ልንጠቀም ይገባል፡፡ እ.ኤ.አ በ2050 አመተ ምህረት የህዝብ ቁጥሯ ከእጥፍ የሚያድግ ሲሆን ፤ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን የሚደርስና 60 በመቶው ከ25 አመት በታች ይሆናል፡፡”
አሜሪካ በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ እያደረገች ያለችው ጫና መልከ ብዙ ሲሆኑ፤ የውጥረቱ አንድ ክር የዋሽንግተንና የቤጂንግ የአህጉሪቱን የተፈጥሮ ሀብቶች እንደ ቅኝ ግዛት ዘመን በአዲስ መልክ የመቀራመትና የጂኦፖለቲካዊ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ፍልሚያ ነው፡፡