እንደ ሮል ሞዴል ሲቆጠሩ ፥ እንደ ትሕነግ ገል ሆነው ስለተሰበሩ ሰዎች…
(አሳዬ ደርቤ – ለድሬ ቲዩብ)
ባሁኑ ሰዓት በመላው ኢትዮጵያዊያን እይታ ግዙፍ ወንጀለኛ የሚባለው ‹‹ትሕነግ›› ሲሆን፣ ትልቁ ወንጀል ደግሞ ‹‹ከትሕነግ ጋር መተባበር›› ነው፡፡ ይህ ሕዝባዊ ድምዳሜ ታዲያ ከሚዲያዎች ዘገባ ወይም ደግሞ ከታሪክ ድርሳናት የተገኘ ሳይሆን በዐይናችን እና በዘመናችን ካየነው ምግባርና ተግባር የሚቀዳ በመሆኑ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሥም ገንቢ ፕሮፖጋንዳም ይሄን አስተሳሰብ ማለዘብ አልተቻለውም፡፡
ሴት ልጅን አስገድዶ ሲያረክስ፣ የንጹሐንን ደም እንደ መስኖ ውሃ ሲያፈስስ፣ አገር ሲያፈርስ፣ ሰላምና መረጋጋትን አጥፍቶ ሽብርን ሲያነግስ፣ ሲዘርፍና ሲጨፈጭፍ ብሎም በዚህ ምድር ላይ ያሉትን ወንጀሎች ሁሉ አንድ በአንድ ሲፈጽም ዐይተን የደረስንበት ድምዳሜ ነው፡፡
ስለሆነም ከህወሓት ጋር መተባበር ማለት ሴት ልጅን በመንጋ መድፈር ማለት ነው፡፡ ከትሕነግ ጋር አብሮ መሥራት ማለት እነዚያን ሁሉ የድርጅቱን ወንጀሎች መጋራት ማለት ነው፡፡ አሸባሪውን ለማዳን መሞከር ማለት አስገድዶ ደፋሪን፣ አገር አፍራሽን፣ በቃኝን የማያውቅ ዘራፊን፣ ምህረት የለሽ ጨፍጫፊን… ከእስር ቤትና ከመቃብር ቤት አውጥቶ ወደ ቤተ-መንግሥት እንደማስገባት የሚቆጠር ነው፡፡
ማንኛውም ሰው ከህውሓት ጋር ሲዶልት ተያዘ ማለት የ120 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችን አገር ሲያፈርስ፣ የጋሊኮማና የአጋምሳ ሕጻናትን ደም ሲያፈስስ፣ የሴትን ልጅ ክብረ ንጽሕና ሲገረስስ፣ የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ ክህደት ሲፈጽም፣ ብሎም የአማራና የአፋር ከተሞችን ሲያወድም… በቁጥጥር ስር ዋለ ማለት ነው፡፡
ሐቁ ታዲያ ይሄ ቢሆንም የዚህን አረመኔ ቡድን አረማዊ ተግባር ሊያወግዙ የሚገባቸው ታዋቂና አዋቂ ሰዎች የመርከስ ተግባሩ ውስጥ ተዘፍቀው ለህውሓት ሲያግዙ እየተገኙ ነው፡፡ ፕሮፌሰርና ዶክተር በሚል ማዕረግ የተጋረዱ በርካታ ሰዎች ከአሸባሪው ጋር ግንኙነት መስርተው የእርኩሰት ድርጊቱን በመቋደስ ላይ ሳሉ እርቃናቸውን ‹‹እጅ ከ ዙም›› እየተያዙ ነው፡፡
በኑሮ ደረጃቸው ባለጸጋ የሆኑ፣ በትምህርት ደረጃቸው እስከ ሦስተኛ ድግሪ የጫኑ፣ በዝናቸው የገነኑ፣ በርካታ ታላላቅ ሰዎች ለአገራችን ችግር የመፍትሔ አካል ይሆናሉ ተብለው ሲጠበቁ የእልቂቱና የውድመቱ ምንጭ ሆነው ሲተውኑ እጅ ከፍንጅ (ከፈንጅም ጭምር) እየተያዙ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ትዝ አለኝ መሠላችሁ?
አንዱ ሥራ ፈላጊ በሆነ የቅጥር ማስታወቂያ ተወዳድሮ የጽሑፍ ፈተናውን ያልፍና ለቃል ፈተና ይቀርባል፡፡ ለኢንተርቪው ከገባ በኋላም ‹‹ቢሮው ወንበር ላይ ቁጭ ባለበት ብቻውን ሞቶ የተገኘ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ማን ይባላል›› የሚል ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡
ወጣቱም ዐይኑን ኮርኒስ ላይ ሰቅሎ ‹‹ቢሮው ውስጥ ሳለ ብቻውን የሞተ›› የሚለውን ሐረግ እያነበነበ ሲያስብ ከቆየ በኋላ መልሱን እንደማያውቀው ሲረዳ ምን ብሏቸው ቢወጣ ጥሩ ነው?
‹‹ምን ብቻውን ይሞታል እኔንም ይዞኝ ሞተ እንጂ››ልክ እንደዚሁ ሁሉ ህወሓት የተባለው ሙታን ድርጅትም ‹‹ብቻዬን ከምሞት›› ብሎ በርካታ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ይዞ እየሞተ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩም፡-
በትምህርት የላቁ- በሃብት የከበሩ
አርአያ ሆነው- ሲጠሩ የኖሩ
ስንትና ስንት ጋሼ- እልፍ አእላፍ አንቱ
በዘመን ተጋልጠው- በአገር ሲዶልቱ
ከስኬት ጫፍ ወርደው- እንደ ገል ሲነኩቱ›› እያየናቸው ነው፡፡
ጠቅለል ስናደርገው…
በባለፉት ዘመናት የመድረክና የሚዲያ ጌጥ የነበሩና እጅግ የተከበሩ ታላላቅ ግለሰቦች በቀሪው ዘመናቸው በቴሌቪዥን ቀርቶ በሰው ዐይን ለመታየት በሚያሸማቅቅና በጸጸት አለንጋ በሚለመጥጥ ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀው በቁማቸው ሲሞቱ ማየት ያስገርማል፡፡ በዚህ የፈተና ወቅት አፈርና ጠጠር መስለው የኖሩ እውነተኛ ወርቆችን ማግኘት እንደቻልነው ሁሉ ታላቋን አገራችንን ከክብሯ ላያወርዷት ነገር ታላቅነታቸውን የሚያንኮታኩቱ፣ የሞተውን ድርጅት ከሞት ላያስነሱትና ከወንጀሉ ላያነጹት ነገር ሕይወታቸውንና ክብራቸውን የሚሰው ወርቅ መሰል እብቆችንም ማየት ችለናል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳለው ሕብስት በሚል ሥም ሲጠሩ ከኖሩት መሃከል ዋነኞቹ ዳንቴላቸው ሲገለጥ ሊጥ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የባሕል አልባሳታቸው ሲገለጥም ባንዳ የሚል ንቅሳትና የህውሓት ባንድራ ከጉያቸው እየተገኘ ነው፡፡
እናም ከጸጸት የሚገላግል ሞት መጥቶ እስኪወስዳቸው ድረስ እነዚህ ሰዎች በቀጣይ ዘመናቸው ‹‹ደደቢት ተወልዶ አፋርና አማራ መሬት ላይ የሞተው ድርጅት ማን ይባላል›› ተብለው ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ይመስለናል፡፡
‹‹እኛን በቁም የገደለን ነዋ!››