Connect with us

የመቅደላ ቅርሶች ወደ እናት ሀገራቸው መልስ፤

ሄኖክ ስዩም

ነፃ ሃሳብ

የመቅደላ ቅርሶች ወደ እናት ሀገራቸው መልስ፤

የመቅደላ ቅርሶች ወደ እናት ሀገራቸው መልስ፤
እንግሊዞች ገቡና ዘረፉ እንጂ ኢትዮጵያን አልገዙም!!

(ሄኖክ ስዩም~ በድሬ ቲዩብ )
መቅደላ ኢትዮጵያን መዝረፍ እንጂ መግዛት፣ ኢትዮጵያን መውጋት እንጂ መማረክ የማይቻል መሆኑን ችላ ያሳየች የታሪክ አውድ ናት፡፡ የናፒዬር ጦር ያለውን ሁሉ ይዞ ወደ አቢሲኒያ መጣ፡፡ ያለንን ዘርፎ ተመለሰ፡፡ ታሪክ ኢትዮጵያውያን በመቅደላ ጦርነት ተዘረፉ አለ እንጂ በመቅደላ ጦርነት ሳቢያ ለቅኝ ግዛት ተዳረጉ ብሎ አላጠለሸንም፡፡ ከዚያ በፊት ነጻ ህዝቦች እንደነበርን ዛሬም ነጻ ህዝቦች ነን፡፡

ዘመን አልፎ ከመቅደላ የተወሰዱ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ የሚነሳው ጥያቄ የዘራፊ ወገኖች ላይ በረታ፡፡ ባህር ተሻግሮ መቅደላ የደረሰው የናፒዬር ጦር ገና ሲነሳ ያሰበው እንዳለ ለማሰብ እውቀት አይፈልግም፡፡ ያ የጦር መልእክተኛ ሪቻርድ ሆምስ የተባለውን የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ አብሮ ይዞ መጥቷል፡፡ ለዘረፋው የነበረው እቅድ ድንገታዊ እንዳልሆነም መረዳት ይቻላል፡፡

እጄን አልሰጥም ካሉት አፍሪቃዊ ንጉሥ ሬሳ ላይ የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው ወሰዱ፡፡

በ15 ዝሆኖችንና 200 በቅሎዎች የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ እንግሊዝ ተጋዙ፡፡ የተዘረፉት ቅርሶች ውሎ አድሮ የባለቤቶቹን ጥያቄ አስከትለዋል፡፡ ከመቅደላ ከተዘረፉት ቅርሶች መካከል የተወሰኑት እንደ አውሮፓውያኑ በ1868 የተካሄደው የመቅደላ ጦርነት አመታዊ በአል ሲዘከር ለእይታ መቅረባቸው ጥያቄውን አፈጠነው፡፡ የአክሱም ሐውልትን ያስመለሰው ኮሚቴ የመቅደላስ ቅርሶች? ማለት ጀመረ፡፡
የመቅደላ ቅርሶች የገጠማቸው ሙግት ተከታታይና መታከት የሌለበት ሆነ፡፡ ይሄ ሲበረታ ነው የእንግሊዙ ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ከ150 ዓመታት በፊት በነበረው የመቅደላ ውጊያ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው የተወሰዱ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ዘውድ፣ የሰርግ ቀሚስና የወርቅ ዋንጫዎችን በውሰት ልስጣችሁ እስከማለት የደረሰው፡፡

የመቅደላን ቅርሶች በማስመለስ በኩል በእንግሊዝ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲና የኢምባሲው ቤተሰቦች ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በልተቋረጠው ጥረትም ዲያስፖራውን ባሳተፈ እንቅስቃሴ ከNational Army Museum ጋር ባደረገው ጠንካራ ሙግትና ዲፕሎማሲ የአፄ ቴዎድሮስን ፀጉር ሚሲዮኑ ወደ ሀገሩ ማስመለስ ችሏል፡፡

እስከአሁን በነበረው ጥረትም የመቅደላን ቅርሶች በመለየት የተዘረፉት ላይ ብዙ ጥናት ሰርተው ቁጭት ከፈጠሩት እንደ አቶ ግርማ ኪዳኔ ያሉ ምሁራንን ጨምሮ ቃል ለማይገልጸው ውለታቸው የፓንክረስት ቤተሰቦች፣ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ መቅደላ 150 አመትን በመዘከር ዳግም የቅርሶቹን ጉዳይ ነፍስ የዘራበት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የሀገረ እንግሊዝ ወገን የቅርስ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች፣ በተለያየ ዘመን በሥራ ሃላፊነት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን የመሩ ሚኒስትሮችና የቅርስ ተቆርቋሪዎች እንዲህ ላለው ስኬታማ ተግባር የሚመሰገኑ ናቸው፡፡

ህዳር 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የገቡት የአንገት ጌጥ፣ በነሀስ የተለበጠ ጋሻ፣ ትልቅ የብር መስቀል፣ በቆዳ ተደጉሶ በእጅ የተፃፈ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ፣ አነስተኛ መጠን ያለው የብር መስቀል፣ ፅዋ ይወሰድበት የነበረ ዋንጫ እና ማንኪያ፣ የጳጳሳት እና የካህናት አክሊል፣ ሦስት ከቀንድ የተሰሩና በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎች፣ ክታብ እና የገበታ ስዕል የሚገኙበት 13 የኢትዮጵያ ቅርሶችም ለሀገራቸው ይበቁ ዘንድ የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ፣ በእንግሊዝ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ሼሄራ ዛድ ፋውንዴሽን ላደረጉት ጥረት ከልብ እናመሰግናለን፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top