ውድነህ ክፍሌ እንደጻፈው !…
“ቢሰድቡኝም ምንም አይመስለኝም። የዘር ፓለቲካ ያስጠላኛል!” ትላለች ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊት ሄርሜላ አረጋዊ።
ባችለር ዲግሪዋን በኢመርሰን ኮሌጅ በጋዜጠኝነ አግኝታለች፤በሐገረ አሜሪካ። ትውልዷ አዲስ አበባ ነው። በ7 ዓመቷ ወላጅ እናቷ ለትምህርት ወደ አሜሪካ፤ሚሲሲፒ ሲሄዱ አብራቸው ተጓዘች።
“ከብዙ ሰው ጋር ነው የኖርኩት” የምትለው ሔርሜላ ዘረኝነትን አጥብቃ እንደምትጠላ ትናገራለች፦”የዘር ፖለቲካን አላምንበትም!…እንዲህ ያለው የትም አይወስደንም” ትላለች።
ስለ አሜሪካው መገናኛ ብዙሀን ስለ CNN፣ዋሽንግተን ፖስት እና የእንግሊዙ BBC ስትናገርም፦ “ጦርነቱ ሲጀመር የእውነት ስራ የሚሰሩ መስሎኝ ዜናውን እያመንኩ ነበር።…የእውነት ስራ የሚሰሩ መስሎኝ ነበር። እናቴም ትግራይ ነበረች። ስለዚህ በጣም እከታተል ነበር”
ቆይታ ስትረዳ ግን የተዛባ መረጃ ማቅረባቸውን ተረዳች። “በኋላ ስረዳ ነው ሃሳቤን የለወጥኩት፤ እውነቱን ቆይቼ ነው የተረዳሁት”
ጋዜጠኛም ነችና በራሷ መመዘኛ ያመነችበትን ማቅረቡን ተያያዘችው። ይሄኔ የእኛ ዘር ነች ከሚሉ ወገን ቁጣና ስድብ ጎረፈላት፤”ባንዳ” የሚል ቅጽል ስምም ወጣላት። ከሌላ ወገን ደግሞ “ጀግኒት” የሚል ሙገሳ ዘነበላት።
ሄርሜላ የቆምኩት ከእውነት ጎን ነው ትላለች፦ “እኔ ለፖለቲካ ብዬ ሳይሆን ለሰው ብዬ ነው የምሰራው!” ስትል ትናገራለች። እንደበረዶ የሚወርድባትን ስድብ አስመልክታም “ለአንድ ወገን አልሰራም! አክቲቪስት አይደለሁም። ከሃቅ ጎን ነው የምቆመው…ስድቡ ምንም አይመስለኝም!” ስትል አቋሟን አስረግጣለች ትናገራለች።
ባንዳ በተባለችበት ቡድን ግን ነገሮች እየከረሩ መጡና ከምትሰራበት ተቋም CBS እንድትባረር ፊርማ ማሰባሰብ ተጀመረ። ሌላኛው ወገን ደግሞ የሄርሜላን ጀግንነት እያሞካሸ ማንም ከስራዋ እንዳይነቀንቃት ድጋፉን አጠናከረ። የድጋፍ ፊርማም ተሰባሰበ። “ብዙ የማይወዱኝ አሉ።ከአስር አመት በላይ ቲቪ ላይ ስለሰራሁ ደንዳና ትከሻ አለኝ።…ከስራ እንድባረር ፊርማ ተሰባስቦ ነበር። በሌላ ፊርማ ነው ወደስራ ገበታዬ የተመለስኩት!” ትላለች ሄርሜላ።
ፍልቅልቋና ሜትር ከሰባ ሶስት አካባቢ ቁመት ያላት ሄርሜላ አረጋዊ ጋዜጠኝነት የልጅነት ህልሟ ነበር። በዜና አንባቢነት፣ በሪፖርተርነትና በዘጋቢነት አልጀዚራን ጨምሮ ታላላቅ መገናኛ ብዙሐን ላይ ሙያዊ አገልግሎቷን ሰጥታለች፤እየሰጠችም ነው።
በምትወደው የጋዜጠኝነት ሙያም ተፈላጊነቷ እየጨመረ ነው። እንደ ፊመስ ፒፕል ድረ ገፅ መረጃ ከሆነ አመታዊ የተጣራ ገቢዋ 2 ሚሊየን ዶላር ይደርሳል ይለናል። ሔርሜላ ግን ክፍያው ሳይሆን በምትወደው ሙያ ከእውነት ጎን ቆማ የምታገኘው እርካታ ከምንም በላይ ዋጋው ከፍ ያለ እንደሆነ ታምናለች። ለዚህም ነው ደግማ ደጋግማ “ለሰው ብዬ ነው የምሰራው!” የምትለን።
“ኢትዬጵያ ተስፋ አላት።….አማራ ትግሬ መባባል አይጠቅምም።… ስለጎሳ፣ስለጦርነት ማውራት ማቆም አለብን!” ትለናለች።
እንደሄርሜላ ያሉ ሚዛናዊ ሰዎችን ያብዛልን። ሰላም ለሀገሬ!!! ሁሉም ከኢትዮጵያ በታች ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!።