Connect with us

ከአፍሪካ ግርጌ እስከ ነጩ ቤተ መንግሥት ደጃፍ

Social media

ነፃ ሃሳብ

ከአፍሪካ ግርጌ እስከ ነጩ ቤተ መንግሥት ደጃፍ

ከአፍሪካ ግርጌ እስከ ነጩ ቤተ መንግሥት ደጃፍ፤
ለዓለም እውነት የማሳወቅ ታሪካዊ ገድል!

(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ኢትዮጵያውያን ዓለም ፊት አብረው ቆመዋል፡፡ በመላው ዓለም የተደረገው ሰልፍ ደማቅ እና በየሀገሩ ብዙሺህዎች የተካፈሉበት ነበር፡፡ ትናንት የዓለም አደባባዮች የኢትዮጵያን የፍትሕ ጥያቄ አድምጠዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪቃ ጀምሮ አውሮጳን በማዳረስ እስከ አሜሪካ በደረሰው የ”ተውን” ጩኸት ዓለም አልሰማሁም ነበር እንዳይል አድርገነዋል፡፡
ይህ ሰፍል ነጻዋ ሀገር በውስጥ ጉዳይዋ ሰብአዊ መብትና ሰላም በሚል ድራማ ጣልቃ ተገብቶ ክብሯም ሉዓላዊነቷም እንዲራከስ የተወጠነውን ሴራ ያጋለጠ ነው፡፡ የአሜሪካ ጠምዛዥ እጆች በመጨረሻም ፈውስ ሳይሆኑ ጥፋትና መከራ መሆናቸውን አሳስቦ ህግና ሉዓላዊነት እንዲከበር ያደረገ ነው፡፡

በ27 የዓለም ከተሞች የተደረገው ሰልፍ መልእክቱም ሀሳቡም አንድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን እጅ መጠምዘዙ በቃ ብለዋል፡፡ የለንደን ጎዳናዎች ጉልበት አለኝ ብሎ በአፍሪካ ነጻ ጉዳይ ጫና ፈጥሮ መፈትፈትን በሚኮንኑ ጀግና አፍሪካውያን ድምጽ ተናውጠዋል፡፡

አሜሪካ እጇን ታነሳ ዘንድ በሚጠይቀው በዚህ ሰልፍ ኢትዮጵያና ኤርትራውያን በሀገራቸው ጉዳይ እየተፈጸመ ያለውን ጫና ለምን ብለው ሞግተው በቃ ብለው ጠይቀዋል፡፡ ይህ የፍትሕ ድምጽ መሆኑን ጫና አሳዳሪዎችም ዓለምም በይፋ አይቷል፡፡

ምን እንደፈለገ የማይታወቀውና ፍላጎቱ ዘመኑን የማይመጥነውን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲና ስውር እጃቸውን ዘርግተው በሀሰት መረጃ እውነት እያዛቡ ሀገር ለመበተን የቋመጡትን የምዕራብ ሚዲያዎች በአደባባይ ያጋላጠው ይህ ሰልፍ በሁለት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ህብረት ደምቆ ተካሂዷል፡፡ ማን ያውቃል ነገ አፍሪካውያን በዚህ ጉዳይ በአንድ ላይ አብረው ይቆሙ ይሆናል፡፡ እንደ ኤርትራና እንደ ኢትዮጵያም አፍሪካ በቃ የምትልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

በሎንደን ጎዳናዎች፣ በእስራኤል አደባባዮች፣ በነጩ ቤተ መንግሥት በራፍ፣ እንግሊዞች እንዳሻቸው በሚሆኑበት የደቡብ አፍሪካ ጎዳና፣ በካናዳ፣ ራስ ተፈሪያኑ የቃል ኪዳን ሀገራችን ላይ እየሆነ ያለው ነገር በቃ ብለው አብረው ከኢትዮጵያና ከኤርትራውያኑ ጎን ቆመዋል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዴንቨር ኮሎራዶ፣ በቦስተን፣ በሜኒሶታ፣ በአሪዞና፣ ቺካጎ፣ ቴክሳስ፣ አትላንታ፣ ዳላስ፣ በካናዳ ኦቶዋ፣ ቶሮንቶ፣ ሞንትሪያል ብቻ የትም ሁሉም ጋር በቃ ብለው የወጡ መፈክሮች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ጉዳይ እየተፈጸመ ያለውን ሴራ አጋልጠዋል፡፡

ይሄ ሰልፍ ከዚህ ቀደም ውጪ ያለው ሀገር ወዳድ በወታደሩና በህዝባዊ ሰራዊት ተጋድሎ ሲቀና የኖረውን ያህል በሀገር ውስጥ ያለው ወገን ደግሞ ምነው እዚያ መሃል ባደረገኝ እስኪል የሚያስቀና የነጻነት ተጋድሎ ነው፡፡

ዓለም እውነቱን በአደባባዮች ሰምቷል፡፡ ሚዲያዎቹ ያደረጉት ጫና፣ የውጪ ፖሊሲውን ደባ፣ የጣልቃ ገብነቱን መጠንና ሽብርተኛን የመደገፉን ስውር ሴራ በይፋ የተቃወሙት ኢትዮጵያና ኤርትራውያኑ እጅግ ብዙ ህዝብ በተሳተፈባቸው ብዙ ከተሞች ሆ ብለው ወጥተው ሁሉንም አጋልጠው፣ ይብቃ በሚል መሪ ቃል እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ እንዲበቃ ጠይቀዋል፡፡

ህዝብ የመረጠውን መንግስት በእጅ አዙር ለመጣል መፈለግ በምርጫ ከሚያምንና ነጻ ምርጫ ካላደረጋችሁ እያለ ማዕቀብ ከሚጥል መንግስት በነጻ ምርጫ ስልጣን የያዘን ሃይል ለማስወገድ ከአማጺ ጎን መቆም ምን ዓይነት እጅ እግር የሌለው መርህ እንደሆነ አሳይተውናል፡፡ እንዲህ አብረን ከቆምን ግን ምኞታቸው ይመክናል፡፡ እናሸንፋለን፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top