Connect with us

የደሴዋ እብድ እና አሜሪካ

Social media

ነፃ ሃሳብ

የደሴዋ እብድ እና አሜሪካ

የደሴዋ እብድ እና አሜሪካ
(አብዱራህማን አህመዲን- የቀድሞ ፓርላማ አባል)

በዱሮ ጊዜ በደሴ ከተማ ውስጥ የምትኖር አንዲት እብድ ነበረች፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን በጧት ተነሳችና “እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል፣ እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል…”በማለት እየዞረች ስትለፈልፍ ዋለች አሉ፡፡ እብድ ስለሆነች እሷ የምትለውን ልብ ብሎ የሰማት፣ ነገሬ ብሎ ያዳመጣት ሰው አልነበረም፡፡ ከእብድ ፍሬ ያለው ነገር ይነገራል ብሎ ከቁብ የቆጠራት አልነበረም፡፡

በዚያው እለት ምሽት ላይ በደሴ ከተማ በአንዱ ሰፈር የእሳት ቃጠሎ ተነሳ፡፡ ብዙ ቤቶች ተቃጠሉ፡፡ በርካታ ንብረት ወደመ…ያቺው የደሴዋ እብድ በማግስቱ ጧት ተነሳችና በየሰፈሩ መዞር ጀመረች፡፡

በየሄደቺበት ቦታ ሁሉም ሰው የሚያወራው የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ቤት ስለመቃጠሉ፣ ንብረት ስለመውደሙ ነው፡፡ ገረማትና “የሚሰማኝ ጠፍቶ ነው እንጂ እኔ ተናግሬ ነበር፡፡ እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል ብዬ ነበር…” አለች አሉ፡፡

የሚገርመው ነገር ቤቱን ያቃጠለቺው እሷ ራሷ ነበረች፡፡ “እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል፣ እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል…”ስትል ያረፈደቺው እሷ ራሷ ማታ ቤት እንደምታቃጥል እቅድ ይዛ ስለነበር ነው…

አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ያለቺው ተግባር ከደሴዋ እብድ ጋር ተመሳሰለብኝ፡፡ አሜሪካ፤ “ወያኔ አዲስ አበባ ይገባል፡፡ እነሱ ሲገቡ በከተማዋ ችግር ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ዜጎቼን ቶሎ ከአዲስ አበባ ውጡ…” በማለት በአደባባይ መናገር ከጀመረች ሰነበተች፡፡ እንዲህ ያለው ራእይ፣ እንዲህ ያለው ነብይነት ለአሜሪካ ብቻ እንዴት ሊገለጥላት ቻለ? አሜሪካ ለብቻዋ የምታውቀው ነገር ይኖር ይሆን?

ወያኔ አዲስ አበባ መግባቷ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በ1983 ደርግን ጥለው አዲስ አበባን ተቆጣጥረዋል፡፡ በከተማዋ ግን ምንም የተፈጠረ ተዓምር አልነበረም፡፡ ሰላማዊ ህዝብ ላይ ትኩረት ያደረገ የተቃጠለ ቤት አልነበረም፡፡ የወደመ ንብረት አልነበረም፡፡

ዜጎች እርስ በርስ አልተጨፋጨፉም፡፡ ያኔ የአሜሪካም የአውሮፓም ኤምባሲዎች በአዲስ አበባ ነበሩ፡፡ እነዚህን ኤምባሲዎች ማንም አልነካቸውም፡፡ አንድም የውጭ ሀገር ዜጋ ጥቃት አልደረሰበትም፤ የተገደለ ፈረንጅም አልነበረም፡፡

ዛሬ ምን የተለየ ነገር ተፈጥሮ ነው አሜሪካኖቹ እንዲህ ጭንቅ ጥብብ ያሉት? አሜሪካኖቹ የሚያውቁት ነገርማ አለ! ያ ነገር እነርሱ ራሳቸው ለአዲስ አበባ ከተማችን ያጠመዱላት ወጥመድ ይሆን? እና እንደ ደሴዋ እብድ የሚያደርጉትን ወይም በወያኔ አማካይነት የሚያስደርጉትን እየነገሩን ይሆን? ደግሞስ ወያኔዎቹ የአሜሪካ የቁርጥ ቀን ወዳጆች ናቸው፡፡

ዜጎቻቸውን በማስወጣት ስራ ተጠምደው ከሚባዝኑ ወዳጆቻቸውን ወያኔዎች “ተው ዜጎቼን አትንኩ” አይሏቸውም እንዴ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እንችል ዘንድ ወደ ኋላ መለስ ብለን የአሜሪካንን እና የወያኔን ወዳጅነት እንመልከት… ህወሓት ከደርግ መንግስት ጋር ሲያደርግ በነበረው የትጥቅ ትግል ወቅት በርካታ ፈረንጅ ወዳጆችን እንዳፈራ ይታወቃል፡፡

ከነዚህ ውስጥ አንዱ ካናዳዊው ፕሮፌሰር ጆን ያንግ ነው፡፡ ጆን ያንግ በዚያ ወቅት ለBBC በጋዜጠኛነት ይሰራ ነበር፡፡

እናም ለዘገባ በሱዳን በኩል ወደ ትግራይ ገባ፡፡ ጋዜጠኛው
ጆን ያንግ ዘገባውን ሰርቶ አልተመለሰም፡፡ የወያኔዎቹ “አድቬንቸር” (ጀብድ) ብቻ ሳይሆን እነ መለስ ዜናዊ ጤፍ በሚቆላው ምላሳቸው ሰውየውን አንዳች አዚም ጫኑበት፡
፡ ለዓመታት አብሯቸው እዚያው ቆየ፡፡ እየዘገበም፣ አብሯቸው እየታገለም፣ ታሪካቸውን እየመዘገበም አብሯቸው ቆየና በ1983 አብሯቸው አዲስ አበባ ገባ፡፡

እንደገባም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ከእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ያስተምር ጀመር፡፡ በዚያው ወቅት በእንግሊዝኛ “Peasant Revolution in Ethiopia: Tigray People Liberation Front 1975 – 1991” (ማለትም፤ “የገበሬ አብዮት በኢትዮጵያ፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከ1967–1983”) በሚል ርእስ የህወሃትን የትግል ሂደት የሚያወሳ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ጆን ያንግ እስከ አሁን ድረስ ከህወሓት ጎን ነው፡፡

የዛሬ ዓመት “The looming long civil war that could break Ethiopia” ማለትም “ኢትዮጵያን ሊሰብር የሚችል ረጅም የእርስ በርስ ጦርነት” በሚል ርእስ የወያኔ አጋርነቱን የሚያሳይ መጣጥፍ በመጻፍ ጓዳዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 71ኛው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አንቶኒ ብሊንከን የመለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡ የብሊንከነረ ባለቤት ልጅ ስትወልድ መለስ ዜናዊ “አራስ ለመጠየቅ” ወደ አንቶኒ ብሊንከን ቤት አሜሪካ አቅንቶ እንደነበር ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

ዛሬ አንቶኒ ብሊንከንን የህወሓት ነገር እንቅልፍ የነሳቸው ከወያኔ መሪዎች እና ከህወሓት ጋር ያላቸው የተለየ ግለሰባዊ ወዳጅነት ነው፡፡

ምስክርነትም የሚጸድቀው ሦስት ሲሆን ነው፡፡ አንድ የወያኔ ወዳጅ ልጨምርላችሁ፡፡ከአንቶኒ ብሊንከን የቅርብ ረዳቶች ውስጥ አንዷ ጄል ስሚዝ ትባላለች፡፡ ጄል ስሚዝ ለህወሃት አመራር ቅርብ ናቸው፡፡ እኚህ ሴት ላለፉት 40 ዓመታት ከህወሓት ጋር ዝምድና አላቸው ተብሏል፡፡

ጄል ስሚዝ በመለስ ዜናዊ የአስተዳደር ዘመን የህወሓት እና የአሜሪካ የስለላ ድርጅት – CIA አገናኝ ነበሩ ይባላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ጄል ስሚዝ የትግራይ የረድኤት ድርጅት በሆነው በኤፈርት ውስጥ ለሦስት ዓመታት በኃላፊነት ሰርተዋል፡፡

በወቅቱ የኤፈርት መሪ የነበረው ተክለወይኒ አሰፋ ይህንኑ ተናግሯል ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት “ጄል ስሚዝ ለህወሓት ከሞንጀሪኖ እኩል ናት” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡

እንግዲህ እነዚህ ዝምድናዎች ናቸው ህወሓትንና አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናትን በማይበጠስ ክር ያስተሳሰራቸውና በ“ፍቅር እስከ መቃብር” መርህ ያቆራኛቸው፡፡ ለዚህም ነው የአሜሪካ መንግስት ለአሸባሪው ቡድን ከወታደራዊ የሳተላይት መረጃ ማቀበል እስከ አማካሪነት እያገለገለች ያለቺው፡፡

እዚህ ላይ “አሜሪካ እና የደሴዋን እብድ የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ የደሴዋ እብድ ምሽት ላይ ቤት የማቃጠል እቅድ ስለነበራት ጧት ላይ “እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል፣ እዚህ ከተማ ቤት ይቃጠላል…” ስትል ዋለች፡፡

አሜሪካም ኢትዮጵያን የሚያምሱትን፣ አዲስ አበባን በደም አበላ ለማጥለቅለቅ የተዘጋጁትን ህወሓትንና ሼኔን ለሽብርና ለጭፍጨፋ ማሰማራቷን ስለምታውቅ፣ እነዚህ የሽብር ኃይሎች በአዲስ አበባ ከተማ የዘረጉትን የጥፋት መዋቅር ስለምታውቅ፣ ህወሓትና ሸኔ በአዲስ አበባ ሁከትና ብትብጥ በማነሳሳት ህዝቡን እርስ በርስ ለማጫረስ እቅድ ማውጣታቸውን ስለምታውቅ፣ በአዲስ አበባ ያሉ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የታጠቁትን መሳሪያ የህወሓት አማካሪ የሆነቺው አሜሪካ በደንብ ስለምታውቅ፣… እንደደሴዋ እብድ “ህወሓት ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በአዲስ አበባ ሽብርና እልቂት ስለሚኖር ዜጎቼ በአስቸኳይ ውጡ…” የሚል ውትወታ፣ ጩኸትና ማስፈራራት እያሰማች ነው፡፡

በርግጥ አሜሪካ ዜጎቿን ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ማድረጓ መብቷ ነው፡፡ ከፈለገች ኤምባሲዋንም መዝጋት ትችላለች፡፡ የህወሓትና የሸኔ ስፖንሰር መሆን ግን በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ላይ ወረራ መፈጸም መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገራችን ፈርሳ፣ ህዝባችን ተጨፍጭፎ እያየን እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ እንደማይሆንም ግንዛቤ መውሰዱ ጠቃሚ ነው፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top