እንኳን በመጋዘኗ በሲኖዲዮሷ ጣልቃ እየተገባ፣ ፓትረያሪኳ ተሰዶ 27 አመት በመከራ ያሳለፈችና የትህነግ ስውር ደባ ያሰቃያት ቤተ ክርስቲያን እኮ ናት!
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ደሬቲዩብ)
ከሀገረ ስብከቱ መጋዘን 1800 ጥይቶች ተገኙ የሚለው ዜና ትልቅ ጉዳይ መሆኑ ገርሞኛል፡፡ ምክንያቱም ጥይቱ በቤተ ክርስቲያኗ መጋዘን መኖሩ በካርታ እንኳን ካሰላነው ስድሳ ካርታ ጥይት ነው፡፡ ምናልባት ምን ያህል ክላሽ ለጸጥታ ስራ ትጠቀማለች የሚለውን ብናስብ የጥይቱ ቁጥር ላይጋነን ሁሉ ይችላል፡፡ ከዚያ ይልቅ ግን እንዴት ብሎ የሚጠይቅ ሞኝ እንዴት ይረሳል ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሃያ ሰባት አመት ያየችው ስቃይ መች ተቆጥሮ ያልቃል? እንደው ወያኔ መጋዘኗን አኑሮበት ቢሆን እንኳን ምን ብርቅ ነው? ታጋዮች እንደ ካህን በመዋቅሯ ተጠቅጥቀው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊጠረንፏት መከራቸውን ሲያዩ አይደለም እንዴ ያሳለፉት?!
ይህቺ ቤተ ክርስቲያን እኮ ዋናው መሪዋ ከሀገር ተሰዶ ፖለቲካ እጁን ከትቶባት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሳይቀር ጣልቃ እየተገባበት፣ ጳጳሳት በማረፊያ ቤታቸው እየተደበደቡ፣ በአደባባይ መነኩሴ በጥይት እየተመታባት ያሳለፈች አይደለችም እንዴ?
በፖለቲካ መሪዎቹ ኦርቶዶክስና አማራን አንገት አስደፍተናል እየተባለ ሲነገር መች ምስጢር ነው አደባባይ ላይ አልነበረም እንዴ ሲታወጅ የሰማነው?
በየሀገረ ስብከቱ ከትግል የተረፈ ማሃይም አይደል እንዴ ሊቃውንቱን ካልመራሁ ብሎ ሲያሰቃይ የኖረው? በመጋዘኗ እንኳን ጥይት መድፍ ቢደበቅ እንኳን ምን ይገርማል? እንደ ቤተ መንግስቱ ሁሉ ቤተ ክህነቱም ኢትዮጵያን ያለ ሲያሳድድ፣ በዘር ፖለቲካ ተለክፎ በስውር የጌታቸው አሰፋ መዋቅር ሲታመስ መኖሩ አንድም ቀን ምስጢር ሆኖ አያውቅም፡፡
አንዳንድ ጉዳዮች ትናንትን እረስተን ዛሬ ስንገረም ያስገርማሉ፤ እውነት ለመናገር በደንብ ከተፈተሸ እና ጉዳዮ ከተመረመረ ይሄ ተገኘ የተባለው ጥይት ተሰውሮ የተቀመጠ እንደማይሆን እገምታለሁ ምክንያቱም ያን ማድረግ ከፈለጉ ቁጥሩ ከዚህ የሚበልጥ በርካታ ነገር መደበቅም ይችላሉና፤
በራሳቸው ገዳም ከባድ መሳሪያ ገጥመው የሚዋደቁ እንዲሁም ቄሱን ታጋይ አድርገው የሚያሰልፉ ቅርስ ሸጠው ክላሽ የሚገዙ ቡድኖች የቤተ ክህነትን መጋዘን ቢደፍሩት አልያም ቢጠቀሙበት ወይም በመዋቅራቸው ለክፉ ቀን ቢያስቀምጡት ምኑ ገርሞ ነው?
ይልቁንም ሁሉም ቦታ እጃቸው ስለነበረ የፖለቲካ ቁማርተኞች እያወራን እንዴት እዚህ ቦታ በሚል አንዘናጋ የትም እና ሁሉም ቦታ በጥንቃቄ ክትትል አድርጎ ስውር ዓላማቸውን ማፍረሱ ውጤት ያመጣል፡፡ ኢትዮጵያን የጠላ ሃይል ሴራዎችን የትም ማምከን ከቻልን ኢትዮጵያን እንታደጋለን፡፡