Connect with us

ምዕራባውያኑ በእጅ አዙር ቃታ ስበውብናል፡፡

ነፃ ሃሳብ

ምዕራባውያኑ በእጅ አዙር ቃታ ስበውብናል፡፡

ምዕራባውያኑ በእጅ አዙር ቃታ ስበውብናል፡፡ ዓለምን ገጥመናል፡፡ እግዜር ይስጠው ዓለም ዳግም እንደ አድዋ አንድ አድርጎናል!!

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ምን እንደፈለጉ እንኳን እኛ እነሱም የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ ግን ተጋግዘውብናል፡፡ የቻሉትን አድርገዋል፡፡ በእርዳታ ስም ባቀመሷቸው ገንዘብ ጨርቅ ጎዳናዎቻቸው ላይ ለመሸጥ እንኳን ሰላም የሌለባቸው ሀገር ወርቅ በመስታወት ከምትሸጠው ከተማ ለደህንነታችን ብለው እንዲወጡ አፍሪቃውያንን ጭምር ሊያሳድሙብን ሞክረዋል፡፡

አልበደልናቸውም፡፡ ትናንትም ቢሆን መጡ ቀመሱ ሄዱ፡፡ አድዋን ጥቁር ነጥብ አድርገው በዚህ ዘመን እድላቸውን ሊሞክሩ ከሆኑ የሞከሩት ያሳከው አንዲትን የብሔር ፖለቲካ ቁማር ያተራመሳት ሀገር ዳግም አንድ ማድረግ ሆኗል፡፡

በሚዲያዎቻቸው የመጨረሻውንና ነውረኛውን ቅሌት አሳይተውናል፡፡ በዲፕሎማሲ መርህ መጩው ትውልድ የሚያፍርበት ስራ ሰርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ዛሬም አንዲት ነጻና ኩሩ ሀገር እንድትሸማቀቅ ተባብረውብናል፡፡ እየሆነ ያለው ነገር ምናልባትም እኛን ምክንያት አድርጎ የዓለምን ታሪክ ሁሉ ይቀይር ይሆናል፡፡

በዚህ ደረጃ ለራሳችን ቦታ አለን፡፡ እኛን ምክንያት አድርጎ ዓለም የጥቁርን ክንድ ያየበትን የታሪክ ምዕራፍ አስዝግበናል፡፡ ለወንድሞቻችን የነጻነት ምልክቶች ሆነን ተገልጸናል፡፡ አድዋ ድል ያደረግነው ትናንትን ብቻ አይደለም ነገንም ነው፡፡

አሜሪካ ትናንት በውሎ አበል ሱማሌ አስገብታ እንዳላወጋችን እስክትረሳው በገዛ ሀገርና ግዛታችን ኢትዮጵያን ለማዳን የምንሄድበትን ርቀት ፈተና ለመሆን ሞክራለች፡፡ እጅ እግር የሌላቸው መግለጫዎቿ በየቀኑ ይጎርፋሉ፡፡ ከአልቃይዳ ቁጭ ብላ ያልመከረችው አሜሪካ ምክር የማይሻው መላ እያመጣች ክንዷን ለማሳየት ሞክራለች፡፡

አሜሪካንን መልካም አድርጎ የሳለልን የምዕራብ ሚዲያ እርቃኑን አይተነዋል፡፡ ሰብዓዊ መብት ተጣሰ በሚል ዜማ ሥራ አጥ ሴቶች ሥራ እድል ያገኙበት የንግድ ስምምነት ላይ ማዕቀብ ጣለች፡፡ አንዱ ሀሳቧ ከሌላው እንደሚጋጭ አየን፡፡

ለወትሮው አምንስቲ ይሄን አለ ሲባል እስኪሰለቸን የሚቀባበሉት የምዕራብ ሚዲያዎች አሁን ከሆንው አሳንሶ ቢናገር ዓይናቸውን ጨፍነው ፊታቸውን አዙረው የነውራቸውን መጠን እና ግዝፈት አሳይተውናል፡፡ እኛን ከጎናቸው እንቆም ዘንድ በሰሩበት ሚዲያ ከጎናቸው የምንርቅበትን ምክንያትና ሀቅ አሳዩን፡፡

በየሚዲያው እያሉት ያለውን ስንመለከት ከጉዳታችን ይልቅ ጀግንነታችንን መሰከረልን፡፡ ዓለም ጣቱን ቀስሮ እኛን ባገኘው ዘዴ እየገጠመ ነው፡፡ ዓለም በእኛ ላይ መነሳቱ አንዳችን በሌላችን እንነሳ ዘንድ የተሰራብንን ሴራና ቁማር በጣጥሰን አብረን እንድንቆም አድርጎናል፡፡

አባቶቻችን ተወረው ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ጦርነት ተልኮባቸው ጦር መሳሪያ እንዳይገዙ ደባ ተሰርቶባቸዋል፡፡ ይሄም ትውልድ ይሄን ያልፋል፡፡ የማያልፈውና በየዘመናቱ ለአፍሪካ ህልውና ስጋት ሆኖ የሚቀጥለው የምዕራባውያን ደባም እንደሁኔታው ወደ መቃብር እየወረደ ይመስላል፡፡ ማን ያውቃል ነገ የዓለም ታሪክ ይቀየር ይሆናል?

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top