“ኦሮሞ ሆነህ መቀሌ ሄደህ ከወያኔ ጋር ለመስራት ማሰብ ቅሌት ነው!” ~ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ጉዳዩ የዘር ብቻ አይደለም ፤ እንዲያ ቢሆንማ ለመለስ ዜናዊ ከሺህ አድዋ አንዱ በረከት ስምዖን ባልበለጠ ነበር፡፡ እኩይ ዓላማን ግብ የማድረስ ጉዳይ ስለሆነ ብሔር ሳይመርጥ ጁንታው የኔ ያለውን ቅጥረኛ ኢትዮጵያ ላይ ያሰማራል፡፡
አንድ ሰሞን ገና መቀሌ እንደገቡና ጥጋቡ ለመብረድ ፈተና ገጥሞት እንካ ሰላንቲያው እንደ ከረረ ከአማራ እነ አቶ ልደቱ አያሌ ከኦሮሞ ደግሞ በርካታ ያኮረፉ ፖለቲከኞች መቀሌን የውሃ መንገድ አድርገዋት ነበር፡፡
የለውጥ ሃይሉ ቅር አሰኝቶናል አልያም በሚፈለገው መጠን ለውጥ አልመጣም ማለት ሌላ ሆኖ ሳለ ወጣቱ በስናይፐር ታጭዶ ያመጣውን ለውጥ መቃብር የሚከት ፍቅር ውስጥ መግባት ብዙዎቹን አስገርሟል፡፡
እዚህ መንደር “በሬ ያኮላሸውን ይወዳል!” እስኪባል ትናንት ሃይላንድ አንጠለጠሉብኝ ብሎ ወጣቱን በቁጭት ያስነሳ አብዮተኛ ስልጣን ሲያጣ ደግሞ ከእነሱ ጋር ልሞክር ብሎ ሲባትል ታይቷል፡፡ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ አንድ ቃለ መጠይቁ ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጠው ምላሽ ድርጊቱን እንዴት እንዳፈረበት ከሚኮንንበት መንገድ መረዳት ይቻላል፡፡
ሀጫሉ የፖለቲካ ታጋይ ነን የሚሉ ሰዎች እየሆኑ ያሉትን ነገር ተመለከተና እንዲህ አለ፤
“ምንም ያህል ስለ ፖለቲካ ልታውቅና ምሁር ልትሆን ትችላለህ፡፡ ነገር ግን መቀሌ ሄደህ ከወያኔ ጋር ለመስራት ማሰብ ቅሌት ነው፡፡”
ይሄንን ቅሌት ዛሬም እየደገሙ ያሉ ሰዎች አይተናል፡፡ ያሬድ ጥበቡ የህወሃትን ክፋት ልክ በሌለው መንፈስ የአማራ ወጣት ላይ አስተጋብቶ አሁን ደግሞ መቀሌ ሄዷል፡፡ መቀሌ የሚሄዱ ሰዎች ስልታቸው ብዙ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጦርነት ሀገር ያፈርሳል ይሉና ይመክራሉ፤ ምክራቸውን የሚያቆሙት ህወሃት ድል አድርጌ ከተማ አስለቀቅሁ ሲል ነው፡፡
ሌሎቹ ደግሞ መንደር ለመንደር የህወሃትን ታላቅ ጦረኛነት እያንሾካሾኩ የህብረተሰቡን ስነ ልቦና ለመስረቅ ይጥራሉ፤ መቀሌ በመንፈስ የሚሄዱና ከትህነግ ጋር የሚሰሩ ሰዎች ብዙዎቹ የራሳቸው ቋንቋ ተናጋሪዎች ቢኖሩም እንደ ሀገር በየቋንቋው በገንዘብ የገዙት ሀገር ሻጭ አለ፡፡
እርግጥ ነው፤ ነገሩን ጠልቆ ለመረመረ ከእነሱም የሀገር ወዳዱና የአንደርታው ሚና እንደ አድዋው አይደለም፡፡ የሚያምኑት በጣም የሰፈራቸውን ልጅ ነው። ለዚህም ነው ትህነግ በአንድ መንደር ልጆች አልፎም ቤተሰብ አባላት ስተነዳ የኖረችው፡፡ ተው ባይ በጠፋበት ሀገር መቀመቅ የከተተችውም ለዚህ ነው፡፡
ግን ዛሬም ሀጫሉን ያልሰማ ጅል በልቡ መቀሌ ሄዷል፡፡ እኛ ደግመን ደጋግመን የምንነግረው ግን መቀሌ መሄዱ ቅሌት መሆኑና ውርደቱ የእሱና የልጆቹ እንጂ ኢትዮጵያ እንደማትዋረድ ነው፡፡
ድል ለታላቋ እናት ሀገር፤ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ!!