Connect with us

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት  አካላት ለውይይት የቀረበ  ሰነድ

ይኸ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት አካላት ለውይይት የቀረበ ሰነድ ከምንጫችን ያገኘነው ነው።

ነፃ ሃሳብ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት  አካላት ለውይይት የቀረበ  ሰነድ

ይኸ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት  አካላት ለውይይት የቀረበ  ሰነድ ከምንጫችን  ያገኘነው  ነው። ሰነዱ የህወሓትን የክህደት ጦርነት አነሳስና አካሄድ እንዲሁም ቀጣዩን የኢትዮጵያ ሁኔታ በሚገባ የዳሰሰ ነው። ፅሁፉ ረዥም በመሆኑ በትግእስት እንዲያነቡት  እንጋብዛለን።

መልካም  ንባብ!!

***

የሕወሐት የክህደት ጦርነት፣ ከጽንሰት እስከ እርጅና

(ለውይይት የቀረበ ሰነድ)

ሰላምሁን አየለ

የነገሩ መነሻ -፩  

ሕወሐት ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በበላይነት ሲዘውር ነበር፡፡ በዚህ ዘመኑም አልፎ አልፎ የኢኮኖሚ ዕድገትና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ታይቷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኢፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል፣ የአንድ አካባቢ ሰዎች የበላይነት፣ የዴሞክራሲ መቀጨጭ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የኢትዮጵያን አንድነት የማዳከም ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱ በኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገ ትግል እና በሕዝባዊ ተቃውሞ የሕወሐት የበላይነት ዘመን አክትሟል፡፡ የሕወሐትም ዕጣ ፈንታ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በውድድር ብቻ የሚወሰን ሆኗል፡፡ 

ማንም የበላይ ወይም የበታች ሆኖ የሚኖርበት የፖለቲካ ምኅዳርም ተዘግቷል፡፡ ‹የበላይ ሆኖ የኖረ እኩልነት ውርደት ይመስለዋል› እንደሚባለው ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በእኩል ሜዳ መወዳደርን ሕወሐት ለመቀበል አልወደደም፡፡ በዚህም የተነሣ ወደ ቀደመ የሽፍትነት ጠባዩ ተመለሰ፡፡ የሕወሐት መዛግብት እንደሚያሳዩት በቀደመው የሽፍትነት ዘመኑ የገዛ ጓዶቹን መግደል፤ ሕዝብን በጠላትነት መፈረጅ፣ ንኡስ የገዥ መደብን በፓርቲ ውስጥ መፍጠር፤ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግርን ለፖለቲካ ስሕበት መጠቀም ዋነኛ የትግል መንገዶቹ ነበሩ፡፡

የነገሩ መነሻ – ፪

ሕወሐት በዘመኑ የነበረውን የዓለም የፖለቲካ ለውጥ ተጠቅሞ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በሁለት እግሩ እያነከሰ ነበር፡፡ በአንድ እግሩ ኢትዮጵያን ለመግዛት፣ በሌላ እግሩ ደግሞ በትግራይ ውስጥ ያለውን አካባቢያዊ ገዥነት ላለመልቀቅ ይታገል ነበር፡፡ ነገ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገዥነቱን ባይቀበለው ወደ ደደቢት ተመልሶ በሽፍትነቱ ለማሰብ ዐቅዶ ነው የመጣው፡፡ ልክ ሲያገቡ ስለ ፍቺው እንደሚነጋገሩት ሰዎች፡፡ በዚህ ዕቅዱ የተነሣ በትግራይ ውስጥ በፖለቲካ የበላይነት በቆየባቸው 40 ዓመታት በትግራይ ገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ለክፉ ቀን ይሆነኛል ያለው ዝግጅት በግልጽና በሥውር ሲያከናውን ነው የኖረው፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ለአንድ ፓርቲ ብቻ የሚታዘዝ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መዋቅር ሲያዘጋጅ፤ በየዋሻውና በየገደሉ መሣሪያና  እህል ሲቀብር፤ የወታደር ማሠልጠኛ ዋሻዎችንና ገደሎችን ሲያዘጋጅ፤ ምሽግ ሲቆፍር ኖሯል፡፡  

ትግራይ ውስጥ ተቃዋሚ ሐሳብ ያለው ቡድንና ግለሰብ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ነጻ ጋዜጦችና መጽሔቶችን አግዶ ኖሯል፡፡ ማኅበራ ጉዳዮችን(ለምሳሌ የሴቶችን መደፈር) የተመለከቱ ሰልፎችን እንኳን ሲከለክል ነበር፡፡ ከአጠቃላዩ የትግራይ ሕዝብ አንድ አምስተኛውን ካድሬ አድርጎታል፡፡ በሴፍቲኔት የሚሰጡ ርዳታዎችን ለማግኘት ካድ መሆን ወይም የካድሬ ቤተሰብ መሆን የግድ ነበር፡፡ በየሠፈሩ 20 ነዋሪዎችን የሚጠረንፍ ጠርናፊ አዘጋጅቶ የእያንዳንዱን የመንደሩን ነዋሪ ግላዊ ሕይወት ሳይር ይቆጣጠራል፡፡ ያለ ጠርናፊው ፈቃድ ሠርግ ማድረግ፣ እንግዳ መቀበል፣ ለልቅሶ መቀመጥ፤ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ፣ አይፈቀድም፡፡

ሰዎቹን በርዳታ ድርጅቶች፣ በዓለም አቀፍ ተቋማትና በኤምባሲዎች ሆን ብሎ በማስቀጠር ለፕሮፓጋንዳና ለዲፕሎማሲ ሥራው ሲዘጋጅ ነበር፡፡ አንዳንዶቹንም የኤርትራ ስደተኞች ናቸው እያለ ወደ ምዕራቡ ዓለም በማሻገር ለገንዘብ ስብሰባና ለውጭ አደረጃጀት ሲያመቻቻቸው ቆይቷል፡፡ በሀገር ውስጥም በጽዋ ማኅበራትና በልማት ማኅበራት ስም የራሱን ወገኖች በድብቅ ሲያደራጅ ነበር፡፡ ከ3000 በላይ ይሄንን መሰል አደረጃጀቶች በለውጡ ጊዜ ፈርሰውበታል፡፡ የዚህ ሁሉ ዝግጅት ግብ ‹ኢትዮጵያን መግዛት ካቆምኩ ኢትዮጵያን ማፍረስ እጀምራለሁ› የሚል ነው፡፡ አቶ በረከት ስምዖን በአንድ ስብሰባ ላይ እንዳሉት ‹ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተገነባችው በኢሕአዴግ ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ካለ ትኖራለች፤ ኢሕአዴግ ከፈረሰ ትፈርሳለች፡፡›

 

የነገሩ መነሻ  – ፫

ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የገነባችው ሠራዊት በ1983 ዓም እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ ይህ ሠራዊት ዘመናዊ ሠራዊት በኢትዮጵያ ከተመሠረተ ጀምሮ በሰው ኃይል፣ በሥልጠና፣ በመሣሪያና በአደረጃጀት የተከማቸ ሀብት የነበረው ነው፡፡ በምዕራብም በምሥራቅም ሀገሮች የሠለጠነ ነው፡፡ ሕወሐት ግን ‹የደርግ ወታደር› ብሎ አፈረሰው፡፡ ኢትዮጵያም ዘመናዊ ጦር የሌላት በሽቅ ተዋጊዎች ስብስብ የምትጠበቅ ሀገር ሆነች፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲከሠት ኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል የሚመጥናት ሠራዊት አልነበራትም፡፡ በወቅቱ ኤርትራ የተሻለ አደረጃጀት፣ ሥልጠናና ብዛት የነበረው ሠራዊት ነበራት፡፡ ጦርነቱ ከተለኮሰበት ጊዜ ወሳኙ ጦርነት እስከተደረገበት ጊዜ ጦርነቱን ያዘገየውም ዋናው ምክንያት ይህ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ሠራዊት መገንባት ነበረባት፡፡ መንግሥት ያደረገውን ጥሪ የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ብለው ባይነሡ ኖሮ የኢትዮጵያ ታሪክ በአሳዛኝ መልኩ ይቀየር ነበር፡፡ የተወሰኑ የቀድሞ ጦር አባላት በአሠልጣኝነትና በዘማችነት፤ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ደግሞ በደጀንነትና በዘማችነት በመሠለፋቸው ጦርነቱን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ በዚያው አጋጣሚም ኢትዮጵያ የፈረሰውን ሠራዊቷን ለመገንባት አስችሏታል፡፡

ሕወሐት የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ለሁለት ፖለቲካዊ ዓላማዎች አውሎታል፡፡ የመጀመሪያው ‹በጦርነት የተጎዳ አካባቢ ነው› በማለት ለትግራይ የተለየ በጀት እንዲመደብ ለማድረግ ተጠቅሞበታል፡፡ የዚህ ዋና ዓላማም የትግራይን ሕዝብ በተለየ መንገድ ለመጥቀም አይደለም፡፡ ቀደም ብሎ ያቅደው እንደነበረው፣ ከሥልጣን ከተወገደ ትግራይን ለመገንጠል እንዲያመቸው ለመዘጋጀት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ‹ከኤርትራ በኩል የጦርነት ሥጋት አለብኝ› በማለት ዋናውን የኢትዮጵያ ጦርና የጦር መሣሪያ ትግራይ ውስጥ ለማከማቸት ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ምክንያት 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ጦር በሰሜን ዕዝ ሥር ሆኖ ትግራይ ውስጥ ነበር፡፡ ሕወሐት ከኤርትራ ጋር የነበረው ውዝግብ እንዳይፈታ ይፈልግ የነበረው ጉዳዩን ለፖለቲካ ሽፋን ለመጠቀም እንዲያመቸው ነው፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ሥጋቱን ለፖለቲካ ዓላማ አውሎታል፡፡ ከ2008 ዓም በኋላ ደግሞ ወጣቶችን በብዛት መመልመል፣ በመከላከያ ጄኔራሎች አማካኝነት ለወጣቶች ሥልጠና መስጠት፣ ሚሊሻውን ማጠናከር፣ ከትጥቅ ትግል በኋላ ጡረታ የወጡትን መልሶ መጥራት፤ የመከላከያ አባላትን ማስከዳት በዕቅድ ይዞ ሠርቶበታል፡፡  

ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ አየር ኃይል፣ የወታደራዊ መገናኛ መሣሪያዎች፣ አብዛኛው ተተኳሽ፣ ስትራቴጂያዊ የጦር መሣሪያዎች፣ በብዛት የነበሩት ትግራይ ውስጥ ነበር፡፡ በሂደትም መከላከያን የመሰለ ዕዝ፣ የአሠራር፣ የመገናኛ መንገድ እና አደረጃጀት በመፍጠር ዋናው የሀገሪቱ ጦር እንዲዳከም ተደርጎ ነበር፡፡ የዚህ ዋናው ዓላማ መከላከያን በአካልም በዕዝም በሕወሐት ሥር ማድረግ ነው፡፡ በአካል ትግራይ ውስጥ እንዲሆን፤ በዕዝ ደግሞ በሕወሐት ጄኔራሎች እንዲመራ ተደርጓል፡፡

የጥቅምት 24 /2013 ዓም ዋዜማ

በችግር ጊዜ የተገነባውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሕወሐት ፖለቲካዊ ሤራ ሠርቶበታል፡፡ ኢትዮጵያ እስከ 2010 ዓም አካባቢ የነበራት ጦር ወደ 100ሺ የሚጠጋ ነበር፡፡ ይሄም ከሀገሪቱ ሕዝብ አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በብዙ ሀገሮች የሕዝባቸውን 1 በመቶ ያህል ወታደር ይገነባሉ፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ ወደ አንድ ሚልዮን የሚደርስ ጦር ሊኖራት ይገባ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ግን ሆን ተብሎ ሳይገነባ ቀርቷል፡፡ እንዲያውም መከላከያን በመንደሮች ውስጥ የፖሊስ ሥራ እንዲሠራ በማድረግ ሕዝብና መከላከያ በጠላትነት እንዲተያዩ ተደርጓል፡፡ የዚህም ውጤት ወደ መከላከያ የሚገባው ምልምል እንዲቀንስ ሆኗል፡፡ ይህም መከላከያን የማዳከሚያው አንዱ ስትራቴጂ ነበር፡፡ በትግራይ የልዩ ኃይልና ሚሊሻ ቁጥር መጨመር፤ የመከላከያን ቁጥር ደግሞ መቀነስ፡፡

ከዚሁ 100ሺ ጦር መካከል 40 በመቶው ስታፍ ነበር፡፡ ከቀሪው 60ሺ ጦርም 25ሺው የሕወሐት ጦር እንደሆነ ራሱን የሚያስብ የአንድ አካባቢ ሰው ነው፡፡ ጦሩን ከሚመሩት አመራሮች መካከል 85 በመቶው የሕወሐት የጦር አመራሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ የሕወሐት ከፍተኛ የጦር አመራሮች ሀገርንና መከላከያን በመካድ፤ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ለመከላከያ ተገዳዳሪ የሆነ ሠራዊት በትግራይ ምድር እየገነቡ ነበር፡፡ 

ሕወሐት በጥቅምት 2014 ዋዜማ በአራት መልኩ ይታይ ነበር፡፡

 1.     አብዛኞቹን አመራሮቹን ከሀገር ቤትና ከውጭ ሀገር ቀስ በቀስ በመሳብ መቀሌ ውስጥ እያከማቸ ነበር፡፡
 2.     በተለያዩ ዙሮች ወታደሮችን እያሠለጠነ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከ163ሺ በላይ በመደበኛ ወታደር ደረጃ የሠለጠነ ኃይል አከማችቶ ነበር፡፡ ይሄንንም ኃይል በ9 ክፍለ ጦሮች፣ በ1 ኮማንዶና በ1 ልዩ ኃይል አደራጅቶት ነበር፡፡
 3.     በተለያዩ አካባቢዎች ኮንክሪት ምሽጎች ይገነባ ነበር፡፡
 4.     በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ተግባራትን በራሱና በወኪሎቹ በኩል ያካሂድ ነበር፡፡ ይህም የፌዴራል ኃይሎች ብሎ ሊያስተባብራቸው የሞከራቸው ኃይሎች በሚፈልገው ዐቅምና ፍጥነት አልሄድለት በማለታቸው የተከተለው ዕቅድ ነው፡፡ በአፋር(የአፋር ታጣቂዎች)፣ በአማራ(ቅማንትና የአገው ሸንጎ) በኦሮምያ(ሸኔ)፣ በቤኒሻንጉል(የጉምዝ ታጣቂ)፣ በሶማሌ(በሥልጣን ያኮረፉ የሶማሌ ታጣቂዎች)፣ለዚህ የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ በተለይም ደግሞ በሱዳን በኩል የሚገቡ የሕወሐት ሰዎች ለእነዚህ በድንበር አካባቢ ሥልጠናና መሣሪያ ይሰጧቸው ነበር፡፡ የደኅንነት ሪፖርት እንደሚያሳው ከ35 ጊዜ በላይ የደኅንነት ኃይሉ ከፌዴራል ፖሊ ጋር ተቀናጅቶ ወደ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት እንዲኮላሹ አድጓቸዋል፡፡  

ሕወሐት ጥቅምት 24 ቀን በሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ጥቃት ሲሠነዝር ሁለት ነገሮችን በመተማማን ነበር፡፡

 1.     ለዘመናት ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በየዋሻው ያከማቻቸውን መሣሪያዎችና ትጥቆች
 2.     በሰሜን ዕዝ አማካኝነት በትግራይ መሬት እንዲከማቹ የተደረጉትን መሣሪያዎች

 

ከእነዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከሕዝብ በኩል ሊደርስበት ለሚችለው የአጽፋ ምላሽ ሁለት ነገሮችን አስቀድሞ እንደሠራ ያምን ነበር፡፡ ይሄንንም በሰነዶቹ ላይ አመላክቷቸዋል፡፡  

 1.     ሕወሐት ለዘመናት በሠራው ሤራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከፋፍሏል፡፡ በተለይም በአማራና በኦሮሞ መካከል ጠላትነት ሰፍኗል፡፡ ስለዚህ አንድ ሆነው አይወጉኝም፡፡
 2.     ሕዝቡ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እንዳይተማመን አድርጌዋለሁ፡፡ ስለዚህም የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ በሕወሐት ላይ አይዘምትም ብሎ አምኗል፡፡ የሕወሐት ሰነዶች እንደሚያሳዩት በተለያዩ ስሞች የተከፈቱ ከ2ሺ በላይ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን ሕዝብ ለማጋጨት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ እነዚህም ቀስ በቀስ እየታወቁ እንዲጠፉ በመደረጉ መቀመጫቸውን ካይሮ፣ ካርቱም፣ አሜሪካና ጀርመን ያደረጉት ብቻ ቀጥለዋል፡፡

የጥቅምቱ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ሲጀመር፣ የሕወሐት አስተሳሰብ የተሳሳተ እንደነበር በገሐድ ታይቷል፡፡ ሊያፈርሰው የሞከረው ሰሜን ዕዝ ከጊዜያዊ መደናገጥ ወጥቶና ራሱን አደራጅቶ በመዋጋት የቻለውን ያህል ትጥቁንና መሣሪያውን ይዞ ወጥቷል፡፡ ሊያወጣቸው ያልቻላቸውንም መሣሪያዎችና መጋዝኖች ጥቅም እንዳይሰጡ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል በግንባርና በደጀን ተሰልፎ ሕወሐትን ወደ ለመደው ዋሻ ሸኝቶታል፡፡ የሕወሐት አመራሮች ራሳቸው ባደረጉት ግምገማ ከሰሜን ዕዝ የሚፈልጉትን ያህል መሣሪያና ትጥቅ እንዳላገኙ አምነዋል፡፡ 163ሺ ጦር ሕወሐት ሲያሠለጥን በብዛት የታጠቀው ቀላል መሣሪያዎችን ነበር፡፡ የተማመነው የሰሜን ዕዝን መሣሪያ ለመውሰድ ነበር፡፡ ግን አልተሳካም፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከጥቅምት 24 በኋላ የሕወሐትን ጦር ሲገጥም አምስት ፈተናዎችን አልፎ ነበር፡፡

 1.     የሕወሐት አባላት የሆኑ አዛዦች ከድተውታል፡፡ በውስጡ የነበሩትም አስመትተውታል፡፡ አብዛኞቹ የጦር መሪዎች እነርሱ ነበሩ፡፡ እነርሱ ደግሞ ጦሩን አስመቱ፣ ክደው ሸሹ፤ በመሐል ሀገር የነበሩትም ትእዛዝ በመጠበቅ ላይ ነበሩ፡፡
 2.     የመገናኛ መሣሪያዎቹ በራሱ አዛዦች እንዳይሠራ ተደርጓል፡፡ ለአንድ ወታደራዊ ሥርዓት ወሳኙ የመገናኛ መሥመር ነው፡፡ የመገናኛ መሥመር የሌለው ጦር ተቀናጅቶና ዕዝ ጠብቆ ሊዋጋ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው የመገናኛ መሣሪያዎቹ እንዳይሠሩና ኮዳቸው እንዲቀየር የተደረገው፡፡
 3.     ሰሜን ዕዝ ሲጠቃ የተያዙ አባላት፣ የተወሰዱ መሣሪያዎች፣ ጥቅም እንዳይሰጡ የተደረጉ መሣሪያዎች ነበሩት፡፡ እነዚህ ሁሉ በኢትዮጵያ ገንዘብ የተገዙ የሀገር ሀብቶች ናቸው፡፡
 4.     ከመነሻው ከአንድ ብሔር ውጭ ያሉ የሠራዊቱ አባላት ቁጥራቸው እንዲቀንስና ቁልፍ ቦታዎች እንዳይይዙ ተደርገው ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ የሕወሐት መኮንኖች ሲከዱና አንዋጋም ብለው ጥለው ሲቀመጡ የአመራር ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ እንደነ ጄኔራል ባጫና ጄኔራል አበባው ያሉ ከፍተኛ መኮንኖች ወደ ሠራዊቱ ባይቀላቀሉ ኖሮ ደግሞ ክፍተቱ የማይጠገን በሆነ ነበር፡፡
 5.     ከትግራይ ውጭ የነበሩ ከሕወሐት ጋር የሚሠሩ የጦር አመራሮችና ወታደሮች ከሕወሐት አባላት ጋር እየፈጠሩት በነበረው ያልተገባ ግንኙነት የተነሣ ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህም የሠራዊቱን ዐቅም አዳክሞት ነበር፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የሕወሐትን ጦር የገጠመው እነዚህን ሁሉ መሰናክሎች አልፎ ነው፡፡ ትልቁ የማሸነፊያ ኃይሉ ኢትዮጵያዊ ወኔው ነበረ፡፡ በዚህ ወኔ ሞተርነት በ21 ቀናት ውስጥ ሕወሐትን ከስሕበት ማዕከሉ ለመንቀል ችሏል፡፡ የጥቅምት 24ቱ ሕግ የማስከበር ዘመቻ የተከናወነው በአንድ በኩል ተመትቶ በአንድ በኩል በርትቶ በሀገር ፍቅር ወኔ በዘመተ ኢትዮጵያዊ ሠራዊት ነው፡፡ የአማራና የአፋር ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ተደምረው የፈጠሩት ዐቅም ነበር ድሉን ያመጣው፡፡ ሠራዊቱ ድሉን ያስገኘው ሁሉም ነገር ተሟልቶለት፤ ችግሩ ሁሉ ተቃልሎለት፤ ጉድለቱ ሁሉ ተሞልቶለት አልነበረም፡፡ የጎደለውን ሁሉ የሞላው ለሀገሩ ባለው ፍቅር ነው፡፡

የጥቅምቱ ሕግ የማስከበር ዘመቻ አራት ዓላማዎች ነበሩት፡፡

 1.     የተወሰዱትን ትጥቆች ማስመለስ
 2.     የተያዙትን የሠራዊት አባላት ማስለቀቅ
 3.     ሕወሐት የዘረጋውን የፖለቲካና የጦር ተቋም ማፍረስ
 4.     ወንጀለኞችን አድኖ ለፍርድ ማቅረብ

አራቱን ዓላማዎች በማሳካት ረገድ ዘመቻው ውጤታማ ነበር፡፡ በጦርነቱ ጊዜ ከጥቅ ውጭ ከነበሩት በስተቀር ብዙዎቹ መሣሪያዎች ተመልሰዋል፡፡ ከ2ሺ በላይ የተያዙ የሠራዊት አባላት እንዲለቀቁ ተድርጓል፡፡ ሕወሐት የዘረጋውን የፖለቲካና የወታደራዊ መዋቅር ለማፍረስ ተችሏል፡፡ ጥቂት ያልተያዙ ወንጀለኞች ከመኖራቸው በቀር ዋናዎቹ አመራሮች ወይ ተገድለዋል አለያም ለሕግ ቀርበዋል፡፡ ሕወሐትም ቀድሞ ተዘጋጅቶበት ወደነበረው የተንቤን በረሃ ገብቷል፡፡

 

ከጥቅምት 24 /2013 ዓም ማግሥት

መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ውስጥ ለ8 ወራት ያህል ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜም ወንጀለኞችን በማደን፤ ሕዝቡን በማረጋጋት፤ ለሕዝቡ ርዳታ እንዲደርሰው በማድረግ፣ ሕዝቡ ሊተዳደርበት የሚችለውን መዋቅር እንዲዘረጋ በማገዝ እና ሕግና ሥርዓት በማስከበር ተልዕኮውን ፈጽሟል፡፡ ይህ የ8 ወራት ቆይታው በምልዓት እንዳይሳካ ያደረጉት አምስት ምክንያቶች ነበሩ፡፡

 1.     በአንዳንድ አካላት የተፈጸሙ ያልተገቡ ተግባራት፡- ሕወሐት ወደ በረሐ ከገባ በኋላ በተዘረጋው መዋቅር ውስጥ የነበሩ አንዳንድ አካላት የፈጸሙት ያልተገባ ተግባር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳይተማመን አድርጎታል፡፡ እነዚህ የተፈጸሙት ተግባራትና ፈጻሚዎቻቸው እዚህ ግባ የማይባሉ ቢሆኑም በምሳሌነት እየተጠቀሰ የሕዝብ ልብ ለማሸበር ግን በቂዎች ነበሩ፡፡ መንግሥት እነዚህን አካላት አጣርቶ ወታደራዊና ሲቪል ርምጃዎችን ወስዷል፡፡
 2.     በጊዜያዊ አስተዳደር በኩል የተፈጸሙ ስሕተቶች፡- ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሲባል በተዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ብዙዎቹ አካላት ከሕወሐት ጋር የሚሠሩ፤ ለሕወሐት መረጃ የሚያቀብሉ፤ ጠጠሩን አጋንነው ተራራ የሚያሳክሉ፤ የኢትዮጵያን ክፉ ከሚመኙ የውጭ ኃይላት ጋር ተባብረው ሀገር የሚያደሙ፤ ሆን ብለው በሕዝቡ ውስጥ ቅሬታንና ብሶትን የሚቀሰቅሱ ነበሩ፡፡ የተመደቡበትን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ፌዴራል መንግሥትንና የአማራ ክልልን መውቀስ የዘወትር ሥራቸው ነበር፡፡ ሚዲያውን ከመቆጣጠርና ለገንቢ ዓላማ ከማዋል ይልቅ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ የሚነዛበት የሕወሐት ሚዲያ አድገውት ነበር፡፡ በየዞኑና በየወረዳው የተመደቡ፣ ሀገራቸውን ለማገልገል የቆረጡ የትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ እንዲፈጸምባቸው ሁኔታዎችን አመቻችተዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ከ35 በላይ የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ተገድለዋል፡፡ የሕወሐትን ዓላማ የሚወሙ የጊዜያዊ አስተዳደር ሰዎችም ከኃላፊነት እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡
 3.     ሕወሐት በሕዝቡ ውስጥ ባደራጃቸው የስለላና የቁጥጥር መዋቅሮች በኩል የተነዛው ፕሮፓጋንዳ፡- ሕወሐት ሁለት ባላ ተክሎ ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡ ካሸነፈና ከተሸነፈ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ ዝግጅቱ መካከል አንዱ ለዘመናት በሕዝቡ ውስጥ የገነባው ሥውር የስለላ መዋቅር ነው፡፡ ይህ መዋቅር ሕዝብን  አንድ ለ አምስት እየጠረነፈ፤ ከሕወሐት ትእዛዝ ውጭ እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ መዋቅር አማካኝነት የሚመጣውን ትእዛዝ ያልፈጸመ ማንኛውም ተጋሩ ሞት ይጠብቀዋል፡፡ ገዳዩን ግን አያውቀውም፡፡ ይህ አፋኝ መዋቅር ሕወሐት ወደ በረሐ ከገባም በኋላ በሥውር ሥራውን ቀጥሎ ነበር፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ይገናኛሉ፤ ይሠራሉ ያላቸውን ያስፈራራል፤ ይገድላል፡፡ ከበረሐ እስከ ከተማ መረብ ዘርግቶ መረጃ ያመላልሳል፡፡ ስንቅ ያቀብላል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ሽብር ይነዛል፤ ያልተደረገውን ፈጥሮ ሕዝብ እንዲነሣሣ ያደርጋል፡፡ የርዳታ እህሎችን በመቀማት ወደ በረሐ እንዲላክ ያደርጋል፡፡ ተፈጥረዋል የተባሉ ኢምንት ስሕተቶችን አጋንኖ የዘር ማጥፋት እንደተከናወነ አድርጎ ይከሣል፡፡ ይህ የስለላ መረብ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፣ በእምነት ተቋማት ውስጥ፣ በጤና ተቋማት ውስጥ፣ በርዳታ ድርጅቶች ውስጥ፣ በሚዲያ አካላት ውስጥ ተዘርግቶ ሲያውክ ኖሯል፡፡ ሆን ብሎ እያቀነባበረና ከሚዲያዎች ጋር እየተላላከ ተጎድተናል የሚሉ ሰዎችንም እያዘጋጀ ሠራዊቱን ይከሳል፡፡

አኩስም ከተማ ላይ ያን ሁሉ ጥፋት ያቀናበረው ይህ ቡድን መሆኑን የደኅንነት መረጃዎች አሳይተዋል፡፡ የአኩስም ጽዮን ከመከበሩ በፊት ጸጥታ ለማስከበር የሄዱ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ነበሩ፡፡ እነዚህ አባላት አኩስም ሲደርሱ ይህ የስለላ መዋቅር ‹ታቦተ ጽዮን ልትዘረፍ ነው› የሚል ቅስቀሳ ቀስቅሶ ወጣቶችን በአክሱም ጽዮን ዙሪያ ሰበሰባቸው፡፡ በዚያ ጊዜ ከ700 በላይ ወጣቶች በጸጥታ አካላት ላይ ርምጃ ለመውሰድ ዘምተው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ መሠዳሪያቸውን ደብቀው ወደ ሕዝብ የተቀላቀሉ ልዩ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ሁኔታው እየተካረረና የፖሊስ አባላቱ በቁጥራቸው ማነስ ምክንያት እየተጠቁ ሲመጡ ሌሎች ኃይሎች ሕግ ወደ ማስከበር ተስበው እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡

 1.     የተበተነው ሚሊሻና ልዩ ኃይል፡- ሕወሐት ከጦርነቱ በፊት ያሠለጠናቸው ከ163ሺ የሚበልጡ ሚሊሻዎችና ልዩ ኃይሎች ነበሩት፡፡ በጦርነቱ መሸነፋቸውን ሲመለከቱ መሣሪያቸውን ቀብረው ሰላማዊ ሕዝብ መስለው ተበተኑ፡፡ ቀስ በቀስም ‹ክብሪት› የሚባል አደረጃጀት በስለላ ተቋሙ አማካኝነት ፈጥረው የጦሩን እንቅስቃሴ ማወክ ጀመሩ፡፡ የመከላከያ ሠራዊት በተወሰነ መልኩ እነዚህን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የዚህም ዋነኛው ምክንያቱ በሕዝቡ መካከል ሠርገው በመግባታቸውና ሕዝቡንና ሚሊሻውን ለመለየት ባለመቻሉ ነው፡፡
 2.     ፖለቲካዊና ወታደራዊ አለመናበብ፡- የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተካሂዶ መቀሌ ከተያዘ በኋላ በወታደራዊ አመራና በፖለቲካ አመራሩ መካከል አለመናበብ ነበር፡፡ የትግራይ ክልል በኮማንድ ፖስት በወታደራዊ አመራር ሥር መዋል ነበረበት፡፡ አመራሩም በተወላጅነት ስም ለሕወሐት ለሚያደሉ አካላት መሰጠት አልነበረበትም፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ወኪሎችና የሚዲያ አካላት ወደ ትግራይ በሄዱ ጊዜ ያናገሯቸው ወታደራዊ ጄኔራል ሕወሐት የሚለው የሚደግሙ ዓይነት ነበሩ፡፡ ወታደሩ ደም ከፍሎ ያስገኘውን ድል የተመደቡት ሲቪል አመራሮች በዋዛ አስነጥቀውታል፡፡

ሕወሐት በበረሐ ሆኖ ምን ሠራ?

ሕወሐት በረሐ ሊገባ እንደሚችል አስቀድሞ ወስኖ ተዘጋጅቷል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ዝግጅቱ ከ40 ዓመታት በላይ የወሰደ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ዋናው የስበት ማዕከል ወደ መቀሌ መገሥገሡን ሲመለከት፣ ሕወሐት ዋና ከተማውን ለቅቆ ወደ ተንቤን በረሐ ገባ፡፡ የተንቤን በረሐ ለሽምቅ ውጊያ እንጂ ለተለምዷዊ ጦር የማይመች፤ በአውሮፕላን ለመምታት የሚያስቸግር አካባቢ ነው፡፡ ሕወሐት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ቦታውን ለማዘዣነትና ለማሠልጠኛነት ተጠቅሞበታል፡፡ ከትጥቅ ትግሉም በኋላ ልመለስ እችላለሁ ብሎ ሲጠብቀው የኖረ ነው፡፡

ሕወሐት በተንቤን በረሐ ሆኖ 3 ነገሮችን ሠርቷል፡፡

1.እንደገና መደራጀት፡- ከተለያዩ አካባቢዎች በስለላ መዋቅሩ አማካኝነት ተመልምለው የሚላኩትን ሰዎች በዋሻ ውስጥ ሲያሠለጥን ቆይቷል፡፡

 1. ሕዝቡ በአንድ ለአምስት የነበረውን አደረጃጀት እንዲያጠናክርና ከመከላከያ ጋር ሕዝባዊ ጦርነት እንዲገጥም አድርጓል፡፡
 2. ለፕሮፓጋንዳ ጦርነት የሚሆን አደረጃጀት ፈጥሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ ርዳታ በመስጠት ሰበብ የገቡ የውጭ ድርጅቶች ድጋፍ አድገውለታል፡፡ በአንድ በኩል የመገናኛ መሣሪያዎችን በማቅረብ፤ በሌላ በኩል ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኝ በማመቻቸት፤ ከዚያም ሲያልፍ የሕወሐትን የሐሰት ክስ በማስተጋባት የውጭ ድርጅት ሠራተኞች የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በራሳቸው ስም መድኃኒት ሊያደርሱላቸው ሲሉ ተይዘዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ለድርጅታቸው የተሰጣቸው መኪና የሕወሐት መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ ባንክ ባለመኖሩ መንግሥት ገንዘብ መፍቀድ አለበት ብለው ያስፈቀዱትን ገንዘብ ለሕወሐት የሚለግሱ ነበሩ፡፡ የሕወሐትን ሰዎች የርዳታ ድርጅት ተቀጣሪዎች አስመስለው ከፍተኛ ደመወዝ ይከፍሏቸው ነበር፡፡ መንግሥት የሠራተኞቻቸውን ቁጥር፣ ስምና አድራሻ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ብዙዎቹ ማቅረብ አልቻሉም፡፡

የሕወሐት የፕሮፓጋንዳ ሥራ አራት ዘርፎች ነበሩት፡፡

 1. ኤርትራን በተመለከተ ይነዙት የነበረው ፕሮፓጋንዳ፣
 2. የትግራይ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ጥላቻ እንዲያድርበት የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ፣
 3. በሠራዊቱ ውስጥ አሥርገው ባስገቧቸው ወኪሎች በኩል የሠራዊቱን ሞራል ለመንካትና ለመከፋፈል የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ፣
 4. ብሔሮችን በተመለተ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ(ይሄኛው ብሔር የኛ ወገን ነው፤ ያኛው ብሔር ጠላታችን ነው፡፡ ይሄኛውን ብሔር ማርኩ እንጂ አትግደሉ፤ ያኛውን ብሔር ካገኛችሁ ግደሉት፣ ወዘተ. የሚል)

መከላከያ ለምንና እንዴት ወጣ?

መከላከያ በትግራይ ምድር ውስጥ የቆየባቸው 8 ወራት በባዕድ ምድር እንደቆየባቸው ጊዜያት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ሕዝቡ ከሕወሐት አገዛዝ ለመላቀቅ አልፈለገም፡፡ በዚህም የተነሣ ባገኘው አጋጣሚ መከላከያን ይተናኮሳል፡፡ መንገድ ይዘጋል፤ ድንጋይ ይወረውራል፤ ጫካ ውስጥ ተቀድብቆ ተኩሶ ይሸሻል፡፡ መረጃ ይደብቃል፡፡ ራሱ የርዳታ ሥርጭቱን እያሰናከለ መንግሥትን ይወቅሳል፤ ይከሣል፡፡ ከ100 ቢልዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን ያፈርሳል፡፡ የምዕራቡ ሚዲያዎችም ትንሹን እያጋነኑ፤ የሌለውን እየፈጠሩ፣ ሕወሐት የሚሰጣቸውን እያስተጋቡ መከላከያንና ፌዴራል መንግሥትን መክሰስ የዕለት ጸሎታቸው አደረጉት፡፡ የእነርሱን ቅኝት የሚከተሉ አንዳንድ የምዕራብ ሀገሮች፣ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ክስ፣ ውግዘትና መግለጫ  በዛ፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በመከላከያ ላይ ክስ ማዝነብ ከሚሰጡት ርዳታ በላይ የሚሠሩት ሥራ ሆነ፡፡

ይህ ሁሉ ናዳ እየዘነበም ቢሆን መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ በተለየ፣ ለኢትዮጵያም ሕዝብ በአጠቃላይ የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ፍላጎት ብቻ ሊሳካ አልቻለም፡፡ እንዲያውም ድርቅ የሕወሐት የፖለቲካ መሣሪያ እየሆነ መምጣት ጀመረ፡፡ ገበሬውም የእርሻው ሥራ ደረሰበት፡፡ ወታደሩም ደጀን ባልሆነው ማኅበረሰብ መካከል ገብቶ ተፈተነ፡፡ የውጭ ጫናውም ጨመረ፡፡ ይሄን ሁኔታ በመመልከትም መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ሠራዊቱን ለማውጣት ወሰነ፡፡ ሕዝቡ የማሰላሰያ ጊዜ ተሰጥቶት የሚረባውን እስኪወስን መከላከያ እንዲወጣ ተደረገ፡፡

በሕወሐት ፕሮፓጋንዳ የተወናበደው ሕዝብ ማዕበል እየፈጠረ ወደ ሠራዊቱ በመትመም ለሠራዊቱ የኅሊና ፈተና ሆነው፡፡ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ወደ ሠራዊቱ በሺዎች ሆነው እየመጡ ወታደሩን ለጠብ ያነሣሡ ጀመር፡፡ ለምሳሌ በዐቢይ አዲ በሁለት ክፍለ ጦሮቻችን ላይ 40ሺ ሕዝብ ሆ ብሎ በመምጣት ወረራ አካሂዶበታል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ በዘመናዊ መልኩ የሠለጠነ በመሆኑ ሕጻናትንና ሴቶችን፣ በጠቅላላው ሲቪሎችን አልመታም ብሎ ዋጋ ከፍሏል፡፡

መከላከያ ከትግራይ ሲወጣ ሦስት ዓላማዎች ነበሩት፡፡

 1.     ሰብአዊ ሁኔታን ማቀላጠፍ፡– ገበሬው እርሻውን የሚከውንበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ሠራቱ የርዳታ ሥራውን ያውካል እያሉ ለሚከሡት የርዳታ ተቋማት ነጻ የሆነ የርዳታ ማዘዋወሪያ መንገድ ማመቻቸት፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት ለሚከስሱት በየጊዜው ምላሽ ከማዘጋጀት ይልቅ ከከሳሾቹ አካባቢ ራስን ነጻ ማድረግ፡፡
 2.     ደጀን ወደሚያገኝበት አካባቢ መሄድ፡- የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ የገባው የትግራይን ሕዝብ ከሕወሐት ጭቆና ለማላቀቅና እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጻነት እንዲኖር ለማድረግ ጭምር ነበር፡፡ ነገር ግን በተወሰኑ ኃይሎች ተወናብዶ ሕዝቡ የትግሉ አጋር ለመሆን አልቻለም፡፡ ሕዝቡ ነገሮችን ገምግሞ ራሱ የትግሉ አጋር እስኪሆን ድረስ  ከትግራይ ክልል በመውጣት ትግሉ ሙሉ ድጋፍ ወደሚያገኝበት የአፋርና የአማራ ክልል መንቀሳቀስና መቋቋም፡፡
 3.     ራሱን እንደገና ማደራጀት፡- አስቀድሞ እንደተገለጠው፣ መጀመሪያ በሕወሐት በተሠራው ሤራ፤ ቀጥሎ በከዱት የሠራዊት አባላትና አመራሮች፣ ሦስተኛ የሰሜን ዕዝ በመጠቃቱ፣ አራተኛ ለስምንት ወራት በትግራይ በረሐዎች በመንከራተቱ የተጎዳውን ሠራዊት እስከመጨረሻው እንዲጠናከር አድርጎ መልሶ ማቋቋም ይገባ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ አንጻራዊ ፋታ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ለማሳካት ሠራዊቱ በተጠናና አደጋ በሚቀንስ መልኩ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ገብቷል፡፡ ዕቅዱ ከ3 ወራት በፊት የተዘጋጀ ነበር፡፡ የመውጣቱም ሂደት በምሥጢርና በግልጽ የሚከናወኑ ምዕራፎች ነበሩት፡፡ እስከ ምርጫወው ድረስ በሥውር ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ከምርጫው በኋላ ደግሞ በግልጽ ከትግራይ ምድር ወጥቷል፡፡

ሕወሐት አስቀድሞም ዓላማው ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ደግሞ መከላከያን ማፍረስ ምሦሦውን መምታት ነው፡፡ አስቀድሞ በሠራቸው ሤራዎች መከላከያን ሲያዳክም የቆየውም ለዚህ ዓላማ ነበር፡፡ በኋላም ሰሜን ዕዝን የመታው ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ አብዛኞቹ የሕወሐት ሰዎች የሆኑት የጦሩ አመራሮችና ወታደሮች የከዱትም ይሄንኑ ዓላማ ለማሳካት የሚችሉ መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በታሰበው ልክ ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

ይህ እኩይ ዓላማው ያልተሳካለት ሕወሐት፣ መከላከያ ፋታ ከማግኘቱ በፊት እግር በእግር ተከታትሎ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች መጣ፡፡ ሕወሐት ይሄንን እንዲያደርግ ያበረታቱት የውጭ ሀገር ወዳጆቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ወዳጆቹ ሁለት ነገር ሊያደርጉለት ተስማምተው ነበር፡፡ እርሱ የሚያደርጋቸውን ጥፋቶች በዝምታ ለማለፍና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርጋቸው ከሆኑ ግን ለማውገዝ (እነዚህ ከደኅንነት የመረጃ ጠለፋዎች የተገኙ የስልክ ልውውጦች ናቸው)፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሳተላይት መረጃዎችን ጨምሮ ሌሎች የኢንተለጀንስ መረጃዎችን(የኢትዮጵያን መንግሥትና መከላከያን የተመለከቱ) ለመስጠት፡፡ 

ሕወሐት ይሄን ሲያደርግ በሦስት ዓይነት አደረጃጀት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

 1.     በግንባር የሚጋ ወደ 200ሺ ጦር አሠልፏል፡፡
 2.     ተተኪ ተዋጊ ከኋላ ወደ 300ሺ አሠልፏል፡፡ ይሄ ተዋጊ በቂ መሣሪያ የለውም፤ ነገር ግን በወረራ ይሳተፋል፤ ቁስለኛ ያነሣል፡፡ ይዘርፋል፡፡ ሀገር ያጠፋል፡፡ የፊተኛው ሲያልቅም ተተክቶ ይዋጋል፡፡ ሕወሐት በአሁኑ ወረራው እድሜያቸው ከ12-65 የሚደርሱትን ተጋሩዎች ሁሉ አዝምቷል፡፡ ከእነርሱም ጋር የኦነግ ሸኔ፣ የቅማንት ዐማጺ እና የአገው ሸንጎ ተዋጊዎች ተማርከዋል፡፡
 3.     በየሠፈሩ በአንድ ለአምስት የተደራጀ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ኃይል አለ፡፡ የዘመተው ሠራዊት ሲቀንስ ከመካከል ያዘምታል፡፡ ወጣቶችን ይመለምላል፤ ወጣት ሲያልቅ የተገኘውን ሁሉ ያሰልፋል፡፡ በዚህ ምልመላ በገዳም የሚገኙ መነኮሳትና ቆሎ ተማሪዎች፣ ቄሶችና ዲያቆኖች ሳይቀሩ ተሰልፈዋል፡፡ ይህ ኃይል ‹ከአማራ ክልል ለአንድ ዓመት የሚሆን ምግብ ሰብስበህ፣ ንብረት ዘርፈህ ትመለሳለህ› ተብሎ የሚመጣ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ‹አዲስ አበባ ቅርብ ነው፤ እዚያ ከደረሳችሁ ሀብታም ትሆናላችሁ› ተብለው የመጡ ናቸው፡፡ እነዚህኞቹ ከተማ ባዩ ቁጥር ‹አዲስ አበባ ያ ነው?› እያሉ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

 

ሕወሐት ከፊል የአማራ አካባቢዎችን ይዞ ለመቆየት እንዴት ቻለ?

ሕወሐት ውጊያ የከፈተው ፡-

 1.     በአፋር በኩል የኢትዮ ጂቡቲን መሥመር ለመቆጣጠር፣
 2.     በምዕራብ በኩል የወልቃይትን ኮሪደር አስከፍቶ ከሱዳን ጋር ለመገናኘት፣
 3.     በማይ ጸብሪ በኩል አርማጭሆን በመቁረጥ ከቅማንት ዐማጺ ጋር ተገናኝቶ ጎንደርን ለማያዝና የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት፣
 4.     በራያ በኩል የወሎን ሰሜንና ደቡብ ለመያዝ፣
 5.     በራያ በኩል ጨጨሆን ተሻግሮ ደብረ ታቦርንና ባሕርዳርን ለመያዝ ነበር፡፡

በአፋር በኩል የተወሰነ ቢገፋም ከክልሉ አብዛኞቹ ቦታዎች ተሸንፎ ወጥቷል፡፡ የወልቃይትን ኮሪደር ከትግራይና ከሱዳን በኩል ለመውረር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራም ከሽፏል፡፡ በማይጸብሪ በኩል የመጣው ወራሪም እስከ ደባርቅ አካባቢ ቢደርስም አሳፋሪ ሽንፈት ተከናንቦ ዛሬማን ተሻግሯል፡፡ በመቄትና በጨጨሆ በኩል የመጣው ወራሪም ደብረ ታቦር አቅራቢያ ደርሶ በሕዝቡና በመከላከያ የጋራ ትግል ወደ ጋሸና ተመልሷል፡፡ ቆቦን፣ ወልድያንና መርሳን ይዞ ወደ ወገል ጤና የመጣው ወራሪ እና ዋግ ሕምራንና ላስታን የያዘው ወራሪ ግን ከሁለት ወራት በላይ እዚያው ይገኛል፡፡ ለምን?

 1.     የወሎ ግንባር ሰፊ ነው፡፡ ከፍላቂት እስከ ጭፍራ ይደርሳል፡፡ ይሄን ሁሉ በወታደር ብቻ መዝጋት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ወደ ደባርቅ የመጣው የሕወሐት ጦር በሦስት አካላት ነው የተደመሰሰው፡፡ መከላከያ ዋናውን ስትራቴጂያዊ ውጊያ ተዋጋ፤ በግራና በቀኝ ያለው መሥመር የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ዘጋ፡፡ በየሸጡ የተቆራረጠውን ጉድባና ገደላ ገደል የአካባቢ ሕዝብ ተደራጅቶ ዘግቶ ተዋጋ፡፡ በመካከል መከላከያ አጋጥሞት የነበረውን ፈተናም በጋራ ለማለፍ ተቻለ፡፡
 2.     ሕዝቡ ከጦርነት ጋር ያለው ባህል እንደሌሎች አካባቢዎች ባለመሆኑ
 3.     በሠራዊቱ ውስጥ ሕወሐት አሥርጎ ባስገባቸው ሰዎች በሚነዛ ወሬ እና በሚሠራ ሤራ ሠራዊቱ በተደጋጋሚ በመፍረሱ
 4.     የወረዳና የዞን አመራሩ ሕዝቡን ከማስተባበር ይልቅ በሐሰት ወሬ ተነድቶ አካባቢው ጥሎ በመጥፋቱ፡፡ ሕወሐት ወደ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ከመጣ ጀምሮ አካባቢያቸውን ነቅተው ታጥቀው ያዋጉ አካላት ነበሩ፡፡ በቀታራኒ ደግሞ 85 በላይ የወረዳና የዞን አመራሮች አካባቢያቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ተረጋግጧል፡፡
 5.     በገንዘብ ተገዝተው ከሕወሐት ጋር የሚያብሩ አካላት መኖራቸው፤ እስከ 40 ሺ ብር ተከፍሏቸው መረጃ የሚሰልሉ ነዋሪዎች ተይዘዋል፡፡
 6.     ወጣቱ ክፍል ራሱን ለውጊያ ከማዘጋጀትና አካባቢውን ከመጠበቅ ይልቅ ሽሽትን መምረጡ፤ የሕወሐት ወራሪ ወደ ወሎ በመጣ ጊዜ በመሣሪያ ዐቅሙ ከምሥራቅ አማራ አካባቢ ሕዝብ የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ልዩነቱ የአደረጃጀት ነበር፡፡ የትግራይ ወራሪ ከሀገሩ ነቅሎ 400ሺና 500ሺ ሆኖ ለዝርፊያ ይመጣል፡፡ ያለቀው አልቆ የተረፈው ወደፊት ይሄዳል፡፡ ጉዞው እንደ አንበጣ ነው፡፡ የምሥራቅ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ግን ሕዝብን በሕዝብ ለመመከት ዝግጅትም ፍላጎት፣ አላሳዩም፡፡
 7.     በአማራ ልዩ ኃይል ውስጥ ሠርገው ለጠላት ሲሠሩ በነበሩ ኃይሎች የተነሣ የጠፋ ጊዜና ኃይል አለ፡፡ አሁን ያሉት አመራሮች ተተክተው ቀዳዳውን እስኪደፍኑት ድረስ በውስጥ ሠርገው ገብተው ልዩ ኃይሉን ያስመቱት፤ በኋላም እንደ ምግበ ያሉ አካላት አጋፍጠው ጥለውት ጠፍተው ነበር፡፡

የሕወሐት ወታደራዊ ሰነድ እንደሚያሳየው ዋና የጦርነቱ ዒላማ ወሎ አልነበረም፡፡ ዒላማው ሁለት ቦታዎች ናቸው፡፡ የአፋርና የወልቃይት ኮሪደር፡፡ በአፋር በኩል የኢትዮ ጂቡቲ መሥመርን ለመቁረጥና በኢኮኖሚው ላይ ከባድ ጫና ለማሳደር፤ በወልቃይት በኩል ደግሞ ከሱዳን ለመገናኘትና መሣሪያና ወታደር ለማግኘት ነበር፡፡ ሰነዱ እንደሚለው ሌሎቹ ግንባሮች ኃይል የመበተኛ ግንባሮች ነበሩ፡፡ መከላከያም በዕቅዱ ላይ ትኩረት የሰጠው ለሁለቱ ግንባሮች ነው፡፡ ሁለቱ ግንባሮች በሚገባ ባይጠበቁ ኖሮ ሕወሐት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰው ጫና ከዚህ የከፋ ይሆን ነበር፡፡ ሕወሐት በወሎ በኩል የጦር ጫና የሚፈጥረው አካባቢውን ፈልጎት አይደለም፡፡ በዚያ በኩል ጫና ሲፈጥር የሕዝቡን ቁጣ በመቀስቀስና በመንግሥት ላይ ጫና በማሳደር፣ ከአፋርና ከወልቃይት ግንባር ጦር እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ነው፡፡ ከአፋርና ከወልቃይት ግንባር ጦር ሲቀነስ ደግሞ ዒላማውን ለመምታት ዕድል ያገኛል፡፡  

 ሕወሐት የሚዋጋበትን መሣሪያ ከየት አገኘው?

ሕወሐት አሁን የሚዋጋበትን መሣሪያ ያገኘው ከአራት ምንጮች ነው፡፡ የመጀመሪያው ቀደም ብለን እንደገለጥነው በምሥጢር ለብዙ ዘመናት ደብቆት ያቆየው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የመከላከያ የሎጀስቲክስና የደኅንነት ኃላፊዎች በጥንቃቄ የሚመረጡ የሕወሐት የቁርጥ ቀን ሰዎች እንዲሆኑ ተደርገው ነበር፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የመሣሪያዎችን ግዥ፣ ሥርጭትና ክምችት ምሥጢራዊ የሕወሐት ኦፕሬሽን አካል ለማድረግ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጉዳዩ ከመጠን ማለፉን ዐውቆ መከላከያ ኦዲት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ በወቅቱ ሕወሐትን ከልክ በላይ አስቆጥቶታል፡፡ ሜቴክ ከተቋቋመ በኋላ የተገዙ መሣሪያዎች በሕወሐት ድብቅ ግምጃ ቤቶች ትግራይ ውስጥ እንዲከማቹ ተደርገው ነበር፡፡ ብዙዎቹ ለረዥም ጊዜ በመቀመጣቸውና ተኩስ ስላልተደረገባቸው በኋላ ከጥቅም ውጭ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የሕወሐት ወታደራዊ ሰነድ እንዳመለከተው ከደበቁት መሣሪያ 20 በመቶውን እንኳን በጤና ማግኘት አልቻሉም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ከ2008 ዓም ጀምሮ በኮንትሮባንድና በግልጽ ሲገዛ የነበረው ነው፡፡ ይሄ መሣሪያ በብዛት በሕግ ማስከበሩ ጊዜ እየተመታና እየተማረከ ከእጁ ወጥቷል፡፡ የተወሰነውን ግን ወደ ተንቤን ለማሸሽ ችሏል፡፡ ሦስተኛው ምንጩ በተለያዩ ስሕተቶች ምክንያት ከሠራዊቱ የተንጠባጠበለት መሣሪያ ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ በተለይ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን ከየደረሰበት ቦታ በግዥ እያሰባሰበ መውሰዱ ነው፡፡ የሕወሐት መሣሪያዎች ስትራቴጂያዊ ባለመሆናቸው የሚያገለግሉት በክረምት ብቻ መሆኑን ያውቃል፡፡ በዚህም የተነሣ ክረምቱ ከማለቁ በፊት የኢትዮጵያን መንግሥት አስጨንቆ ወደ ድርድር ለማምጣት የቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ክረምቱ ከወጣ የአየር የበላይነት ይወሰድብኛል ብሎ ፈርቷል፡፡

የሕወሐት አሁናዊ ሁኔታ

ሕወሐት አዲስ አበባ እገባለሁ ብሎ የጀመረው ዘመቻ ከወሎ ለማለፍ አልቻለም፡፡ አይሳኩም ብሎ ያቀዳቸው አምስት ነገሮች ተሳክተዋል፡፡ (1)ምርጫው ተሳክቷል፡፡ (2)የሕዳሴ ግድቡ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት ተሳክቷል፡፡ (3)አዲስ መንግሥት የመመሥረቱ ሂደት ተሳክቷል፡፡ (4)የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት እንደገና አጠናክሮ የመገንባት ሂደቱም ተሳክቷል፡፡ (5)ሕዝቡ ለመከላከያው ተመዝግቦ በመግባት፣ ገንዘብ በማዋጣት፣ ደም በመለገስ፣ በግንባር ተገኝቶ በማበረታታት፣ ስንቅ በማዘጋጀት፤ ያደረገው አስተዋጽዖ ተሳክቷል፡፡ አምስት የታቀዱ ጥፋቶች ደግሞ ከሽፈዋል፡፡ (1)ከኦነግ ሸኔ፣ ከቅማንት ዐማጺ፣ ከጉምዝ ታጣቂና ከሌሎችም ጋር ግንባር ፈጥሮ ለማተራመስ የታቀደው ሤራ በብዛት ከሽፏል፡፡ ሕወሐት በጠበቀው መልኩ እንዳልሄደለት በግምገማው አምኗል፡፡ (2)አንዳንድ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካላት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሸረቡት ተንኮል ከሽፏል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ኢትዮጵያን ከ10 ጊዜ በላይ አጀንዳ ያደረገው የጸጥታው ምክር ቤት የሚፈለገውን ውሳኔ ማሳለፍ አልቻለም፡፡ (3)ሕዝቡን በብሔር ለማጋጨት፣ በተለይም አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት የተሸረበው ሤራ ከሽፏል፡፡ (4) ‹ጠባችን ከብልጽግና እና ከዐቢይ ጋር ነው› በሚል ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን አታልሎ ለማለፍ የተወጠነው ሤራ ከሽፏል፡፡ (5)በተለያዩ ቦታዎችና ወቅቶች የሽብር ተግባር በማካሄድ ሕዝቡን ለማሸበርና ዓለም አቀፍ ጫናውን ለማባባሰስ የተሞከሩት ሙከራዎች በጸጥታ አካላት ቅንጅት ከሽፈዋል፡፡

እነዚህ እንዳሉ ሆነው፡-

 1.     ትግራይ ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት ማኅበራዊ ቀውሱ ተባብሷል፡- የመንግሥት ሥራ፣ እርሻ፣ ንግድ፣ በሕወሐት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ሁሉም ሰው እንዲዘምት ተደርጓል፡፡ መነኮሳትና ካህናት ሳይቀሩ በግዳጅ ይዘምታሉ፡፡ ከ3700 በላይ ካህናትና መነኮሳት እንደዘመቱ ከተገኙ መረጃዎች ተገምቷል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሲጠይቁ ዘምተህ ዘርፈህ ብላ ይባላሉ፡፡ መንግሥት ዘርህን ሊያጠፋው ነውና መዝመት ግዴታ ነው ተብሏል፡፡ ያልዘመተ ባንዳ ነው ተብሎ በአደባባይ ይረሸናል፡፡ ርዳታው ለሕዝብ ሳይሆን ለሕወሐት ሠራዊት ቀለብ እንዲውል ተደርጓል፡፡
 2.     በሕወሐት ሠራዊት ውስጥ ጥያቄ ተፈጥሯል፡፡ በየጊዜው ይፈርሳል፡፡ በየጊዜው ይበተናል፡፡ መሣሪያ ይሸጣል፡፡ የታሰበውን ያህል ገፍቶ አዲስ አበባ መግባት አልቻለም፡፡ አዛዦቻቸው እየቆሰሉና እየተገደሉ ነው፡፡ እስካሁን ከ34 በላይ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮቻቸው ተገድለዋል፡፡ የሕወሐት ጦር ከመሸሹ በፊት የተገደሉ ወይም በማይተርፍ ሁኔታ ቆሰሉ አዛዦቹን አንገት ይቆርጣል፡፡ እስካሁን 34 አዛዦች አንገታቸው ተቆርጦ ተገኝተዋል፡፡ ይሄም የታወቀው በየግንባሩ የትግራይ ሕዝብን መጀመሪያ በማነሣሣት ለማዝመት ይሞክራሉ፡፡ እምቢ ካለ ያስገድዳሉ፡፡ ወደኋላ እንዳይመለስ ይረሽናሉ፡፡ በቆየ ቁጥር በየአካባቢው ተቃውሞና ሽፍትነት እየተባባሰ መጥቶበታል፡፡ በተያዙ አካባቢዎች ሕዝብ እየሸፈተ ሲያስቸግራቸው መንደሮችን ማቃጠል፤ ሕዝቡን በመደዳ መጨፍጨፍ፤ እህሉን መዝረፍና ማቃጠል፤ ከብቱን መረሸን ጀምረዋል፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ በአራት መንገዶች አስፈራርተው ዝም ለማሰኘት ይሞክራሉ፡፡

ሀ/ በአካል፡- በመግደል፣ በመጨፍጨፍ

ለ/ በሞራል፡- በስድብ፣ በማንቋሸሽ፤ ቤቱን የሬሳ መቅበሪያ በማድረግ፣ በመድፈር(የተገደሉ የሕወሐት ጦር አስከሬኖች ሲፈተሹ በብዛት የሚገኘው ኮንዶምና ሐሺሽ ነው፡፡ ይህም ሴቶችን መድፈር የጦርነቱ ዕቅድ አካል መሆኑን ያሳያል)

ሐ/ በመንፈስ፡- የእምነት ተቋሙን በማርከስ፣ የእምነት ዕቃዎቹን በማራከስ፣ ካህናትና ሼሆችን በማዋረድ

መ/ በባህል፡- ከባህሉ የወጣ ነገር በማድረግና እንዲያደርግ በማስገደድ

 1.     የመሣሪያ ዐቅማቸው እየታደከመ መጥቷል፡፡ ያከማቹት እያለቀ፣ ተጨማሪ የሚያገኙበት መንገድ እየጠበበ መጥቷል፡፡ የመጨረሻ ዕቅድ ብለው በዚህ ረገድ ያስቀመጡት በሠራዊቱ ውስጥ ሽብር በመንዛት መሣሪያ ጥሎ እንዲሄድ ማድረግን ነው፡፡
 2.     ፀረ ሰላም ኃይሎች ያሰቡትን ያህል አላገዟቸውም
 3.     የመከላከያው ዝግጅት ካሰቡት በተቃራኒ ሆኗል
 4.     አስቀድሞ ሲያደርገው እንደነበረው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ይነዛል፡፡ የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን ለመንዛት የማኅበራዊ ሚዲያውን ይጠቀማል፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን ወደከተሞች በማሥረግ ወያኔ እዚህ ደረሰ እዚያ ደረሰ የሚል ወሬ ይነዛል፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ መስሎ ጦሩ ከዳን፤ ልዩ ኃይሉ ከዳን የሚል ወሬ ያሠራጫል፡፡

መጨረሻው ምንድን ነው?

ሕወሐት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ብልሽት ጥንተ አብሶ ነው፡፡ እሱ እስካልተወገደ ድረስ ሀገር ሰላም አታገኝም፡፡ የፈውን ፈጅቶ የወሰደውን ወስዶ ሕወሐት መወገድ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ባለ ሦስት ማዕዘን መፍትሔ መሰጠት አለበት፡፤ የሕዝብ፣ የፖለቲካ አመራሩና የሠራዊቱ የማይነጣጠል አንድነት ወሳኝ ነው፡፡ በዐድዋ ዘመቻ ጊዜ ጦርነቱ የተደረገው በትግራይ ምድር ነው፡፡ ጦርነቱ ግን የትግራይ ጦርነት አልነበረም፡፡ ዚያድባሬ በወረረን ጊዜ የጦር ዐውደ ውጊያው በሶማሌ ክልል ላይ ነበር፡፡ ያ ማለት ግን ጦርነቱ የሶማሌ ጦርነት አይደለም፡፡ ከሕወሐት ጋር የምንዋጋው ጦርነትም በአማራና በአፋር ክልል ላይ ነው፡፡

ጦርነቱ ግን የአፋርና የአማራ ጦርነት አይደለም፡፡ የዚያድባሬም ሆነ የሕወሐት ጦርነት ዓላማቸው ሀገር ማፍረስ ነው፡፡ ልዩነታቸው ከውጭና ከውስጥ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እንኳን ለጦርነት የተሰለፈ ሕዝብ ለእግር ኳስ የተሰለፈ ቡድን እንኳን እየተዘናጋ፣ እየተዋቀሰና እየተካሰሰ ድል ማድረግ አይችልም፡፡ ሳይናበቡና ሳይግባቡ የሚመጣ ድል የለም፡፡ ሲዖል ከገቡ በኋላ እንዲህ ማድረግ ነበረብን ማለት ከሲዖል አያድንም፡፡ ችግር ከመጣ በኋላ እንዲህ መደረግ ነበረበት ማለትም ችግሩን አይቀርፍም፡፡ ልብ ከሚያደክሙ፣ ክንድ ከሚያዝሉ ነገሮች ሁሉ ተቆጥበን  የጀመርነውን ትግል ከዳር እናድረስ፡፡ ከዚያ በኋላ ሂደታችን እንገመግመዋለን፡፡ የሥራ ጊዜ ዛሬ፣ የመወቃቀስ ጊዜ ደግሞ ነገ ነው፡፡

ሰው በሁለት መንገድ ለጠላቱ ይሠራል፡፡ አስቦና ባለማሰብ፡፡ አስበው የሚሠሩት የሕወሐት ጀሌዎች በመሆናቸው እንዋጋቸዋለን፡፡ ሳያስቡ የሚሠሩትን ግን ልንገሥጻቸው ይገባል፡፡ የጦሩን መረጃ፣ እንቅስቃሴና ዕቅድ በማውጣት፤ ፎቶዎችን በመልቀቅ፤ የወታደሩንና የደጀኑን ሞራል የሚነኩ ተግባራትን ሳያስቡ በማድረግ ለጠላት የሚሠሩትን ማረም ይገባል፡፡ ማንም በተለየ መልኩ ለዚህች ሀገር የመሞት ግዴታ ያለበት የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዐቅማችንንም፣ ልባችንንም፣ ጊዜያችንንም ሠውተን ጦርነቱን በአጭርና በጥቂት ኪሣራ የምናሸንፍበት ግንባር ላይ እንዝመት፡፡

(እነዚህን ነጥቦች ለመወያያ እንዲሆኑ አቅርቤያቸዋለሁ፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ሐሳብ ስጡባቸው፤መረጃም ጨምሩባቸው፤ አመሰግናለው)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top