እንኳን አደረሳችኹ!
የወላይታ ህዝብ የ2014 የዘመን መለወጫ የግፋታ በዓል የአብሮነት ዕሴቶች ተምሳሌትነቱ ጉልህ ስፍራ እንደሚሰጠው የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ አስታወቁ፡፡
ዋና አስተዳዳሪው የወላይታ ህዝብ የ2014 ዘመን መለወጫ ግፋታ በዓል አስመልክተው ለህዝቡ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው ዶክተር እንድርያስ ጌታ አዲሱ ዓመትለመላው ህዝባችን የጤና፣የብልጽግና እና የስኬትዓመት እንዲሆን ተመኝተው ለስኬታማነቱ መንግስት ከመላው ህዝብ ጋር በትጋት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግፋታ የወላይታ ባህል አዋቂዎችና ጥበበኞች የጨረቃን ዑደት ስሌት መሰረት በማድረግ ማህበረሰቡ ከክረምት ወደ በጋ፣ ከጭጋጋማ ድባብ ወደ ብርሀናማ አውድ፣ ከአሮጌ ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት ሽግግር የሚያበስሩበት፣ ፈጣሪን ላለፈው ዓመት ስኬት የሚያመሰግኑበት ክብረ-በዓል መሆኑን አመላክተው አዲሱ ዓመት ዕቅዳቸውና ጥረታቸው ስኬታማ እንዲሳካ አምላክን የሚማጸኑበት የተስፋ ተምሳሌት በመሆኑ ለክብረ-በዓሉ ታላቅ ክብርና ሞጎስ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡
የዘንድሮ የግፋታ በዓል ሽብርተኛው የሕወሀት ቡድን የተዳከመች ኢትዮጵያን ለማየት ከሚቃዡ የውጭ ሀይሎች ጋር በማበርየሀገራችንን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን አንድነት ለማፍረስ የጠነሰሰውን ወረራ ለመቀልበስ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንና የጸጥታ ሀይሎቻችንአንጸባራቂና ውጤታማ ተጋድሎ በማድረግ ለድል ብስራት በተቃረብንበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል ፡፡
አያይዘውም በዓሉ የሉዓላዊነታችን መገለጫ የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የ2 ዙር የውሀ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በተጠናቀቀበት የድል ብስራት ማግስት የሚከበር መሆኑ ለበዓሉ የላቀ ድምቀት እንደሚሰጥ አስረድተው የዞኑ ህዝብና አስተዳደር ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ግፋታ ተጣልተው፣ ተኮራርፈውና ተራርቀው የሰነበቱ የትዳር አጋሮች፣ ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ ጎረቤቶችና የተለያዩ የማህበረሰቡ አባላት ጥላቻቸውን በማራቅ ፍቅራቸውንና ወጅነታቸወን ዳግም እንዲያድሱ ዕድል የሚፈጥር የዕርቅና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር እንድርያስ ለተረጋጋና ለሰላማዊ ማህበረሰብና ሀገር ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን አመላክተው ዕሴቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ ቀጣይነት ያለው ጥረት ማድረግይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ዕሴቱ ስንፍናን የሚኮንን፣ ጥንካሬንና ትጋትን የሚያበረታታ፣ ተስፋንና ብርታትን የሰነቀ በመሆኑ ከአርአያነቱ ብዙ እንደሚቀስም የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የበዓሉ ቅድመ-ዝግጅትና አከባበሩ ቀልብን፣ ገንዘብን፣ ጉልበትንና ጊዜን በማስተባበርና በማቀናጀት የሚከወን መሆኑን አብራርተው ዕሴቱን ለትውልድ ለማሸጋገር እንዲቻል ለግንዛቤ ስራ ቀጣይነት ያለው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለበዓሉ አከባበር ድምቀት የሚሰጡ ግብአቶች አቅርቦት በማህበረሰቡ የቁጠባ ገንዘብ የሚደራጁ መሆናቸውን የተናገሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ከልምዱ ቁጠባን የማዳበር ባህላችንን በቀጣይነት በይበልጥ ማጎልበት እንዳለብን አስገንዝበው የግፋታ በዓልን ጨምሮ ሌሎች የሚዳስሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ይበልጥ እንዲጠኑ፣ እንዲታወቁና እንዲለሙ ከቱሪስት ፍሰት የላቀ ገቢ እንዲያስገኙ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት በተነሳሽነት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡(የወላይታ ዞን መንግስት ኮምኒኬሽን)
የዞኑ አስተዳደር የግፋታን በዓል ጨምሮ የብሄሩ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህልና ቅርሶች በላቀ ደረጃ እንዲለሙ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
—