Connect with us

ከዳንኤል ክብረት ጎን ነኝ!!

ከዳንኤል ክብረት ጎን ነኝ!!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከዳንኤል ክብረት ጎን ነኝ!!

ከዳንኤል ክብረት ጎን ነኝ!!

(ጥበቡ በለጠ)

ዲያቆን ዳኒኤል ክብረትን ለረጅም አመታት አውቀዋለሁ። ማወቅ ብቻም አይደለም እሳሳለታለሁ። ኢትዮጵያ እንደ አንተ አይነት ልጆች ይበርክቱላት እያልኩ የምፀልየው ከዘመነ ወያኔ ፋሽታዊ አገዛዝ ጀምሮ ነበር። ወያኔ የኢትዮጵያን ታሪክ እያራከሰ በሚጥልበት ወቅት፣ በዚያ ከፋፋይ ዘመን እነሆ ዳኒኤል ድንቅ ስራ አከናውኗል። 

የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት ማንነትን እየዞረ እየዳበሳት እያያት፣ እያነበባት ለትውልድ ታላላቅ የታሪክ ሰነዶችን አኑሯል። ከ30 በላይ ድንቅዬ መጻሕፍትን አሳትሟል።

መጻሕፍቱ እነ ንጉስ ኢዛና አክሱም ላይ እንዳቆሟቸው ታላላቅ ሐውልቶች፣ መጻሕፍቱ እነ ቅዱስ ላሊበላ ላስታ ላሊበላ እንዳነጿቸው ተአምረኛ ኪነ-ሕንጻዎች፣ መጻሕፍቱ፣ እነ አጼ ፋሲል ጎንደር ላይ እንዳገማሸሯቸው ውብ ኪነ-ሕንጻዎች ሁሉ ለትውልድ በቅርስነት የሚተላለፉ ናቸው። ወያኔ ከኢትዮጵያ ላይ እያነሳ የጣለውን የታሪኳን ማንነት እንደገና እያነሳ ያቆመላት ዳኒኤል ክብረት ነው። የምትራከሰዋን ኢትዮጵያን ወደ መንበረ ክብሯ እየመለሰ የጻፈላት የኔ ዘመን ብርቅዬ ልጇ ነው።

ዳኒ የአደባባይ ተናጋሪ ነው። ንግግሮቹ ማዕከል የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ነው። ኢትዮጵያን በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የማኖር ትልቅ ፕሮጀክት አከናውኗል። ዳኒ ከአፋቸው ማር ጠብ ይላል ከሚባሉት የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች አንዱ ነው። ትውልድን በተረቱም፣ በብሂሉም ሲመክር፣ ሲገስፅ፣ ሲያስታውስ፣ ሲያቃና የኖረ የዘመኔ ፈርጥ ነው።

ዳኒኤል ክብረት፣ በወያኔ ፋሽታዊ አገዛዝ ተማረው ከሐገራቸው ወጥተው እንደ ጨው ዘር የተበተኑብንን ዜጎቻችንን በያሉበት ሐገር እየዞረ ጠያቂያቸው ነው። በዚያ በስደት ሕይወታቸው ውስጥ ገብቶ የሚያስተምራቸው፣ ተስፋ የሚሰጣቸው፣ በመንፈስም በስጋም እንዳይወድቁ የሚያቃናቸው የጨለማው ዘመን ብርሐን ነበር። ዳኒ የባዕድ ሐገር ስደተኞች አለኝታ ሆኖ ትውልድን ወደ ተስፋ ያሻገረ መንፈሳው ወንድም ነው።

ዳኒኤል ክብረት መምህር ነው። ሐይማኖትን፣ ስነ-ምግባርን፣ ኢትዮጵያዊነትን፣ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ማንነትን በኢትዮጵያዊያን ስነ ልቡና ውስጥ ሲገነባ የኖረ ነው። ኢትዮጵያን በሰው ልጅ አእምሮ ውስጥ መንፈሳዊ ጸጋ አድርጎ እየሳላት የኖረ የኔ ዘመን ብርቅዬ ልጇ ነው።

ዳኒኤል ክብረት፣ አማካሪ ነው። ብዙ ትዳሮችን ከመበተን ያዳነ ነው። ቤትን፣ ትዳርን፣ ልጆችን፣ ትውልድን በጎ የሕይወት ጎዳና እንድይዙ ያበረከተው አስተዋፅኦ መቼ ገና ተነገረለት?

ዳኒኤል ክብረት፣ ቆራጥ ነው። ጀግናም ነው። ለኢትዮጵያ እና ለሕዝብዋ ይጠቅማል ብሎ ያሰበውን ነገር ከመተግበር ወደ ኋላ የሚያስቀረው ነገር የለም። መንፈሳዊ ልዕልናው ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ የእርሱ መለያ ቀለሙ ነው።

ዳኒኤል ክብረት ዘረኝነትን፣ ፅንፈኝነትን፣ አግላይነትን የሚፀየፍ ወንድማችን ነው። እርሱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ወዳጅ ነው። የጓደኞቹና የወዳጆቹ ስብጥር በራሱ አስገራሚ ነው። አጅግ ብዙ ሰው የዳኒ ጓደኛ፣ ተመካሪ፣ ተከታይ፣ አድናቂ ነው።

ዳኒኤል  ክብረት፣ ለኢትዮጵያ በጎ የሰሩትን አስታዋሽ ያጡትን ባለውለተኞች እያስታወሰ የሚሸልም ተቋምም የመሰረተ የዚህ ዘመን ባለውለተኛ ነው። ትውልድን በሚገነባ አስተሳሰብ ውስጥ የዳኒ አሻራ ደማቅ ነው።

ዳኒኤል ክብረት፣ ይህን ለዘመናት የካበተ ኢትዮጵያዊ ሰብዕናውን እና ፈጣሪም የሰጠውን ፀጋ ተጠቅሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የራሱን በጎ አሻራ ሊያሳርፍ ቆርጦ ተነስቷል። ይህ ሁኔታ ጠቀሜታው ከፍተኛ ስለሆነ እኛም ወዳጆቹ፣ አድናቂዎቹ ከጎኑ ቆመን ተመርጦልናል።

ኢትዮጵያ ከውጭም ከውስጥም ጠላቶች ተነስተውባታል። የተነሱባት ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ከወደቀበት መጥፎ የታሪክ ክስተት ውስጥ ጎልቶ እየወጣ ባለበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያዊነትን ሲያራክስ የኖረው ያ ወያኔ፣ ግብአተ መሬቱ እየተፋጠነ ሲሄድ ጫጫታዎች በዝተዋል። ከፋፋዩ ወያኔ ፈፅሞ ላይመለስ ሄዷል። እየተንፈራፈረ ጉዳት ቢያደርስም እስትንፋሱ ትቆማለች። ግን የወያኔ መውደቂያ ዋናው መሳሪያ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው። 

የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው። ወያኔ ላይመለስ የሚሄደው የኢትዮጵያዊያን አንድነት በመጠንከሩ ነው። ያ የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ ሕብረት እና ፍቅር የመጣው እንደ ዳኒኤል ክብረት አይነት ሰው ለአመታት ትውልድ ላይ ስለሰራ ነው። እናም ዳኒ አገር ሆኗል። ኢትዮጵያን ሆኗል። ዳኒን መንካት ኢትዮጵያን መንካት ሆኗል። ዳኒ ላይ የሚወጡ መግለጫዎች የፀረ – ኢትዮጵያ መገለጫዎች ናቸው። ምክንያቱም ዳኒ ኢትዮጵያን ስለሆነ ነውና።

ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር በቅድሚያ ያደረገችው፣ ኢትዮጵያዊነትን በትውልድ ውስጥ ሲገነቡ የኖሩትን ሊቃውንትን ማደን፣ ማጥፋት ነበር። ከነዚያ በፋሽስቶ እና በባንዳዎች አሰሳ ውስጥ ገብተው ከነበሩት ብርቅዬ ኢትዮጵያዊያን መካከል ተመስገን ገብሬ ዋነኛው ነበር። በዘመኑ ደራሲው እና አርበኛው ተመስገን ገብሬ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ትልቅ መምህር ስለነበር የፋሽስቶች እና የባንዳዎች ትኩረት ነበር። 

ዛሬም ዳኒኤል ክበረት የኢትዮጵያ ጠላቶች እና ባንዳዎች የትኩረት ኢላማ ሆኗል። ይሄን የጠላት ሐይል እፋለማለሁ! ኢትዮጵያዊነት ላይ የሚመጣን አደጋ የማስተናግድበት መንፈስ የለኝም። በዲያቆን ዳኒኤል ክብረት ላይ  የሚሰነዘሩት ጫናዎች ኢትዮጵያዊነትን ለመምታት የተቃጡ በትሮች ናቸው። እናም ከዳኒኤል ክብረት ጎን ነኝ!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top