የህወሓት አንድ ዓመት ያስቆጠረው ሚስጢራዊ ሰነድ ምን ይላል?
~ ሰነዱ “ጠላት” የሚለውን የፌደራል መንግሥት በኃይል በመገርሰስ በህወሓት የሚመራ አሻንጉሊት የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ያለውን ራዕይ ያስቀምጣል፣
~ ህወሓት በጉልበት ወደማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ለመመለስ ያለውን ህልም ይገልፃል፣
(ልዩ ሪፖርታዥ ~ ድሬቲዩብ)
በፌደራል መንግሥት ፓርላማ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ልክ የዛሬ ዓመት ጦርነት ከመክፈቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ ያወጣው ባለ88 ገፅ “የትግል ልዩ ምዕራፍ ዕድገቶችና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ ስትራቴጂውን ይፋ አድርጓል።
ስትራቴጅው በጥቅሉ ህወሓት ቀደም ሲል ጀምሮ ከለውጡ ተቃራኒ በመሆን ጦርነት ለመግጠም ያደረገውን ሁለንተናዊ ዝግጅት ፍንትው አድርጎ የሚተነትን ነው። “ጠላት” በሚል አስቀድሞ የፈረጀውን የፌደራል መንግሥት በኃይል በማስወገድ አሻንጉሊት የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ያለውን ምኞትም በሰነዱ አንፀባርቋል።
ህወሓት አፈር ልሶም ቢሆን ወደማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን በጠመንጃ እገዛ የመመለስ ህልሙን ሰነዱ ፍንትው አድርጎ ያስቀምጣል።
ሰነዱ የፌደራል መንግሥትን በኃይል የማስወገድ ውሳኔ በ2012 ዓ.ም አጋማሽ ገደማ በህወሓት ውሳኔ ያገኘና ሲዘጋጁበት ስለመቆየታቸው ያትታል።
“…ከዛሬ 5 እና 6 ወራት በፊት ገደማ ሀገራዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የትግል ልዩ ምዕራፍ እና ቀጣይ አቅጣጫ ክስተቶች/ እድገቶች ጽሁፍን አስመልክቶ ሶስት እቅዶችን ለይተን በማስቀመጥ ተንቀሳቅሰናል፡፡ አሀዳዊውን እና አምባገነን ቡድንን ማስወገድ፣ የባለ አደራ መንግስት መፍጠር/ መመስረት …” በማለት ያስቀምጣል።
“የጠላት (የአብይ ቡድን) መሰናበትን ወይም መውደቅን ተከትሎ ወዴት እና እንዴት እንደሚሄድ በከፍተኛ ብቃት እና ጥንቃቄ በመመለስ ከወዲሁ (ተጀምሮም ስለቆየ) የኢትዮጵያ ህዝቦች – ሀይሎችን ማሰባሰብ በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ደግሞ በተለይ በድርጅት ውስጥ፣ መንግስት እና ህዝብ ሙሉ መግባባት ተፈጥሮ ግልጽ በሆነ አቅጣጫ ላይ ሆነን ከወዲሁ የዘላቂ ዋስትናችንን መሰረት በሚያረጋጥ ባቡር ላይ ተሳፍረን መጓዝ መጀመር አለብን።” በሚል ያስቀምጣል። አያይዞም ” ምን አይነት የሽግግር መርህ / አሰራር ?” እንደሚኖር ያትታል።
“በሀገራችን አሁን በተፈጠረው ቀውስ እና ከባድ ጥርጣሬ በአንድ በኩል፣ የተደራጁ የፖለቲካ ሰልፎች /ሰልፈኞች ግንባር ወይም ጥምረት/ በሀገር ደረጃ ያለመኖር እና የተበታተነ መሆን፣
እነዚህን ተከትሎ ተጠቃሚ የውጪ ዜጎች ሂደቱን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል እያደረጉት የሚገኘውን መረባረብ እና ጣልቃ ገብነት በሌላ መልኩ፣ እንዲህ አይነቱ መዝረክረክ የጅምላ እና ችርቻሮ እንካ – በእንካ ሰፊ እድል የሚከፍት ፖለቲካዊ ገበያ ገዢ በሆነበት ወቅት የሽግግሩ አሰራር / መርህ ወይም የጊዜያዊ መንግስት መቋቋም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ብቃት መታየት እንደሚገባው ያስገነዝበናል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ የጊዜያዊ መንግስት አሰራር መርህ ወይም መቋቋም የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆኑትን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በሚጠቅም የሚቋቋሙበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
ይህንን ጊዜያዊ መንግስት ለማቋቋም ቁልፍ መነሻው ይህንን ማድረግ እና በዚሁ መተግበር ለጊዜው ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር እንዴት እንቀጥል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አንድ ሁለት እርምጃ ወደ ፊት የሚወስደን ይሆናል፡…”
ህወሓቶች አስቀድመው ጦርነት አይቀሬ መሆኑን መደምደማቸውን ሰነዱ ያሳያል።”….ወታደራዊ ጦርነትም እንደማይቀር እና የጦርነቱ አይነት እና ይዘት፣ ይህንን አደጋ የምንመክትበትን እና የምናሸንፍበት መውጫ መንገዳችን እና የህዝባችን ወሳኙ ሚና ላይ በአግባቡ የተሟላ መግባባት/ ግንዛቤ እንዲፈጠር ሊሰራበት የሚገባ ነው።…ስለሆነም ህዝባችን የሞራል እና ወኔ ልዕልና፣ ጽናት እና ኩራት ያለው ሆኖ መቆም እንዲችል በሁሉም ረገድ አቅማችን የቻለውን ያህል ርብርብ ማካሄድ ይገባናል፡፡…”ሲል አስፍሯል።
ህወሓት በዚህ ሰነዱ የፌደራል መንግሥቱ መዳከሙንና ደጀን እንደሌለው የተሳሳተ ድምዳሜ አስቀምጧል። ይህም ድምዳሜ መነሻ አድርጎ መጓዙም ዛሬ ለደረሰበትና እየደረሰበት ላለው ኪሳራ እንደዳረገው ይታመናል። ሰነዱ እንዲህ ይላል።” …በዚህ ወቅት ጠላት ተንገዳግዷል፡፡ ይህ ነው የሚባል ደጀን የለውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ቁልቁል እየወረደ ጀምበር እንዳትጠልቅበት የሚያደርገው የቀቢፀ ተስፋ ቅዠት እና ጭፍን እና እውነታን ያላገናዘበ ሁሉን አቀፍ እርምጃዎችን እና መተናነቆች የሚያሳይበት ወቅት ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጊዜ በራሱ ለወገን ቁልፍ መመዘኛ መስፈርት ሆኖ እየወጣ ነው፡፡ በጠላት ላይ የሚወሰደው የማፈራረስ እርምጃ የወገን መረባረብ በተዘናጋ ቁጥር የመበታተን አደጋ ጥላውን እያጠላ ጠላት ተነፃፃሪ እና ጊዜያዊ ህይወት መዝራቱ የሚያስከፍለው አደጋ ሊመጣ ይችላል፡፡
ስለሆነም አሁን የተንገዳገደው ጠላትን አቅም በማሳጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጣል እና ለማሰናበት ወደ የጋራ ስትራቴጂያዊ ጥቃት የተሻገረበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ሰዓቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡…” ይላል።
የህወሓት ቡድን በዚህ የተሳሳተ ስትራቴጂ መሰረት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከለሊቱ 5:00 ሰዓት ገደማ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥት ሆኖ ከጎኑ አሰልፎት የነበረው የመከላከያ (የሰሜን እዝ) አባላት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ከባድ ክህደት በመፈፀም ጦርነቱን መጀመሩ የሚታወስ ነው። በጦርነት መካከል የተገደለው የህወሓት ቃልአቀባይ የነበረው አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው “መብረቃዊ” ያለውን ጥቃት ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ መፈጸሙን በይፋ ማረጋገጡም አይዘነጋም።