Connect with us

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ለትግራይ ወጣቶች እና ሚሊሻ የቀረበ ጥሪ ።

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ለትግራይ ወጣቶች እና ሚሊሻ የቀረበ ጥሪ ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

ዜና

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ለትግራይ ወጣቶች እና ሚሊሻ የቀረበ ጥሪ ።

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ለትግራይ ወጣቶች እና ሚሊሻ የቀረበ ጥሪ ።

የህወሓት ሽብርተኛ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሣሪያ ያደረጋቸው የትግራይ ወጣቶች እና ሚሊሻ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥሪ ያደርጋል።

የአሸባሪው ጥቂት መሪዎች ባላቸው ስግብግብ የሥልጣን ፍላጎት እና ከሕግ ተጠያቂነት ለመዳን ሲሉ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት በመማገድ ከንቱ መሥዋዕትነት እያስከፈሉት ይገኛሉ።

ከአጎራባች ክልሎች እና በአጠቃላይ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋርም በጠላትነት እንዲሰለፍ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን አደናግረው እና አስገድደው ወደ አስከፊ ጥፋት እየከቱት ነው።

ይህ የሽብርተኛው የጥፋት መንገድ በእጅጉ ያሳሰበው እና የትግራይ ሕዝብን እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የሚመለከተው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሆደ ሰፊነት ለትግራይ ሕዝብ በተለይም ወጣቶች እና ሚሊሻ አባላት የሚከተለውን ጥሪ ያስተላልፋል።

ዕድሜ ዘመኑን ” ሥልጣንን ዘላለማዊ ርስቴ ካላደረግኩ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ፤ አሊያም አጥፍቼ እጠፋለሁ” የሚል አስተሳሰብ የተጠናወተው ሽብርተኛው ፤ ለሕዝብ እልቂት እና እንግልት ደንታ ስለሌለው ትግራይ ክልል ከገባ ማግስት ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያልተገቡ እሰጥ-አገባዎችን ከመፍጠር ጎን ለጎን በከፍተኛ ቁጥር ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ሲያሰለጥን እና ወደ መንግሥታዊ ሥልጣኑ በኃይል ለመመለስ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ሀገር የማፍረስ ተግባሩን የትግራይ ሕዝብን ለዓመታት ሲያገለግል የቆየውን የሰሜን ዕዝን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ከጀርባ ማጥቃት ጀመረ።

የህወሓት የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን በመራባቸው ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በሆነው የሥልጣን ጊዜው በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ላይ ለመስማት እጅግ የሚሰቀጥጡ እና ለማመን የሚያዳግቱ ዘግናኝ ግፎችን ፈፅሟል።

ይህንንም በእስር ቤቶች በማጎር፣ ቶርች በማድረግ፣ ጥፍር በመንቀል፣ በማኮላሸት፣ ከአደገኛ አውሬዎች ጋር በማሰር እና በማስበላት መንግሥታዊ ሽብርተኝነት የፈፀመ መሆኑን መላው ሕዝብ እና የጥቃቱ ሰለባዎች የመሰከሩት ሐቅ ነው።

የሽብር ቡድኑ የወንጀሎች ቁንጮ አመራሮች በትግራይ ሕዝብ በተቋቋሙ የተራድዖ ድርጅቶች ስም የቤተሰብ ኔትወርክ በመዘርጋት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን ሀብት ዘርፈው በልጽገውበታል፤ የትግራይ ሕዝብ ከግማሽ በላዩ በምግብ ለሥራ መርሐ-ግብር ኑሮውን እየገፋ እነርሱ ግን ቤተሰቦቻቸውን በአውሮፓ እና በአሜሪካ የቅንጦት ቤት እና መኪና ገዝተው የተንደላቀቀ ሕይወት እንዲመሩ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሽብርተኛውን ወንጀለኞች ከዳር እስከ ዳር የጠላቸው እና ሊፋለማቸው ቆርጦ የተነሣው በፈፀሙበት ግፍ፣ ባካሄዱበት ዘረፋ ከአብራኩ በወጣው ሠራዊት ላይ የግፍ ጥቃት ስለፈፀሙ እና “ኢትዮጵያን እናፈርሳለን” ብለው በአደባባይ ስለፎከሩ ነው።

እናንተም ለሚያደርጉት እኩይ ተግባራቸው ተባባሪ አትሁኑ።  ዓላማቸው እንድትሞቱላቸው በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ቀስቅሰው በማሰለፍ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችሁ ጋር በጠላትነት እንድትፋለሙ እና ትርጉም የሌለው መሥዋዕትነት እንድትከፍሉ ማድረግ ነው።

ስትሞቱ እና አካላችሁ ሲጎድል ወላጆቻችሁ ወይም ሚስት እና ልጆቻችሁ ጡረታ ወይም የደም ካሣ አያገኙም። ደማችሁ ደመ-ከልብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ሙሉ ድጋፉን የሰጣቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የየክልሉ ልዩ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች አንድነታቸውን አጠናክረው እያደረጉት ያለውን ሀገራቸውን ከመፍረስ የመታደግ ውጊያ በአሸናፊነት መወጣታቸው እይቀርም።

የአሸባሪው ህወሓት ጁንታዎችም በቅርቡ ለሽንፈት ይዳረጋሉ። ታዲያ ለምን በሽንፈት መደምደሙ ለማይቀር ከንቱ ዓላማ ሕይወታችሁን እና አካላችሁን ትከፍላላችሁ? ቤተሰቦቻችሁንም ለምን ያለረዳት ታስቀራላችሁ?

በአሁኑ ሰዓት እናንተን ወደ ጦር ሜዳ የሚማግዱ የሕወሓት አመራሮች ወንጀለኞቹ ጥቂት ሲሆኑ፣ ሕዝቡን ሞቢላይዝ በማድረግ የተሰለፋችሁ ሁሉ ወንጀለኞች ናቸሁ ተብሎ አይታሰብም።

የሽብርተኛው መሪዎች እነርሱ በወንጀለኝነታቸው ለሕግ እንዳይቀርቡ ትታዳጓቸው ዘንድ የትግራይን ወጣቶች፣ ሚሊሻዎች፣ ወንድ እና ሴት ሕፃናትን ያለበቂ ሥልጠና ወደ ጦርነት ይልኳቸዋል። ይህ ድርጊታቸው ትግራይን ያለወጣት፣ አረጋውያንን ያለ ጧሪ የሚያስቀር የጭካኔ ድርጊት ነው።

የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ክብር ሲል የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም ሽበርተኛው ግን “ኢትዮጵያን ሳላፈርስ ውጊያ አላቆምም” ብሎ በጦርነቱ ገፍቶበታል።

ጎረቤት ክልሎችንም በመውረር ያሰማራቸውን በርካታ የትግራይ ልጆች ለሞት እና ለአካል ጉዳት ዳርጓል።

ሕይወታቸውን ለማዳን ወደ ኋላ በሚሄዱት ላይም በማሰር እና በመረሸን የጭካኔ እርምጃ እንደሚወስድባቸው ከራስህ በላይ ማስረጃ የለም።

ርኅራሔ ያልፈጠረባቸው የሽብርተኛው መሪዎች በጦር ሜዳ የቆሰሉ እና መንቀሳቀስ የማይችሉትን ወንድሞቻችሁን ከውጊያ አፈግፍጋችኋል በማለት ከፊታችሁ ሲረሽኑ እንደነበር ከእናንተ በላይ አስረጂ የለም።

ሽብርተኛው በርካቶችን ለከንቱ ዓላማ ለሚያካሂደው ጦርነት ገብሮ እና ወላጆችን የወላድ መኻን አድርጎ አሁንም ተጨማሪ የግዳጅ ምልመላዎችን እያካሄደ ነው።

እታገልለታለሁ ለሚለው ሕዝብም ቅንጣት ርኅራሔ የሌለው የጁንታው ወንጀለኛ ስብስብ “በሕዝብ ማዕበል ጦርነትን አሸንፌ ዕድሜዬን አራዝማለሁ” በሚል ኃላፊነት የጎደለው ራስ ወዳድ ውሳኔ ዕድሜ እና ፆታ ሳይለይ ከሕፃን እስከ አዛውንት በጦርነት በመማገድ ለአስከፊ እልቂት እየዳረገ ይገኛል።

አሁንም በርካቶችን ለአላስፈላጊ መሥዋዕትነት ከዳረገ በኋላ “ልጅህን ለዘመቻ የማትልክ ከሆነ ዕርዳታ አይሰጥህም” በማለት ሕዝቡን እያሰቃየው መሆኑ በገሃድ የምታየው እውነት ነው።

ስለሆነም የትግራይ ወጣቶች እና ሚሊሻዎች ሆይ፣ ዓላማ ለሌለው ጦርነት መሥዋዕት መሆናችሁ ይብቃ!

በሽንፈት መደምደሙ ለማይቀር የሽብር ቡድን መራሹ ጦርነት በከንቱ ማለቃችሁን ለማቆም ቆም ብላችሁ አስቡ።

በየግንባሩ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እጃችሁን በሰላም ብትሰጡ ሠራዊቱ ተቀብሎ በእንክብካቤ እንደሚይዛችሁ፣ ከቆሰላችሁም እንደሚያሳክማችሁ እና ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ሰላማዊ ሕይወት እንድትመሩ እንደሚመቻችላችሁ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይህንን ጥሪ የሚያቀርበው ካለው ሕዝባዊ ባህሪ እና ለትግራይ ሕዝብም ካለው ወገናዊነት መሆኑን እየገለጸ፣ እጃችሁን ለመከላከያ ሠራዊት ብትሰጡ ለሕይወታችሁ ዋስትና እንደሚሰጣችሁ በማስገንዘብ ዕድሉን ትጠቀሙ ዘንድ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ አኩሪ መሥዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት።

መስከረም 5/2014

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top