Connect with us

በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ሙከራ በእጥፍ ጨመረ

ኢመደኤ

ሳይንስና ቴክኖሎጂ

በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ሙከራ በእጥፍ ጨመረ

በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ሙከራ በእጥፍ ጨመረ

በ2013 በጀት አመት በኢትዮጵያ የሳይበር ምህዳር ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መጠን በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ፡፡

ከእነዚህም የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ውስጥ 75 ነጥብ 25 በመቶ ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ምላሽ እየተሰጣባቸው ያሉ መሆናቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንት ኤጀንሲ ብሄራዊ የሳይበር ጥቃት የአደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዢን (ኢትዩ ሰርት) ሀላፊ አቶ ሰብለወይን ጸጋዬ እንደገለጹት በ2013 በጀት አመት ከ2 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተሰንዝረዋል።

ይህም በ2012 ዓ.ም ከተሞከረዉ 1 ሺህ 80 አካባቢ ጥቃቶች ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን ያመላክታል ብለዋል።

በ2013 በጀት አመት ለተመዘገበው የሳይበር ጥቃቶች መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ሀላፊው ጠቅሰዋል ለዚህም ፤ተቋማት አሰራራቸውን ቀደም ሲል ከነበረው ተለምዶአዊ አጠቃቀም የኦንላይን አማራጮችን በስፋት መጠቀም መጀመራቸዉ ፣ከሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በሳይበር አማካኝነት ጫናዎች መፈጠራቸው እና በበርካታ ተቋማት ዘንድ ያለው ሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ክፍተት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ሰብለወይን ተናግረዋል፡፡

የጥቃት ኢላማ ከሆኑት ተቋማት መካከልም የፋይናንስ፣ የህክምና ፣ ሚዲያ እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች በሃገሪቱ ያሉ ወሳኝ መሰረተ-ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ያስታወሱት ሀላፊው ከተሰነዘሩት የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መካከልም በቀዳሚነት በድረ-ገፅ ላይ 33 ነጥብ 26 በመቶ የጥቃት ሙከራዎች ሲሰነዘሩ፣ በአጥፊ ሶፍትዌሮች (ማልዌር) አማካኝነት 29 ነጥብ 43 በመቶ በመሠረተ ልማት ቅኝቶች 18 ነጥብ 7 በመቶ ፣ እንዲሁም ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ መግባት 16 ነጥብ 15 በመቶ እና የሳይበር መሠረተ-ልማቶችን ሥራ ማቋረጥ ደግሞ 1 ነጥብ 8 በመቶ ጥቃቶች መከሰታቸውን ሃላፊዉ ገልፀዋል፡፡

ከእነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ውስጥ ምላሽ የተሰጠባቸው 75 ነጥብ 25 በመቶ ሲሆኑ 24 ነጥብ 75 በመቶ ደግሞ ምላሽ እየተሰጠባቸው ያሉ ጥቃቶች ናቸዉ። እነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢደርሱ ኖሮ በተቋማት እና በሀገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የስነ ልቦና ጫና ከፍተኛ እንደነበረም አቶ ሰብለወይን ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያለን ተጠቃሚነት እና ተደራሽነት ማደግ እና የህዳሴው ግድብ ሊኖረው የሚገባው ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ጉዳይ በቀጠናው ካሉ ሀገራት ጋር የፈጠረው ውዝግብ እንዲሁም ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጉዳዮች አለምአቀፍ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከመሆንዋ ጋር ተያይዞ ለሳይበር አጥቂዎች ኢላማ እንድትሆን አድርጓታል ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእነዚህ ጥቃቶች መነሻ ከተለያዩ የአለም ሀገራት በሚገኙ የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች የተሰነዘሩ እንደነበሩ ታውቋል።

በኤጀንሲው ውስጥ ያለው ብሄራዊ የሳይበር ጥቃት የአደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ማዕከል (Ethio-CERT) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ የሳይበር መሰረተ-ልማቶችን እና የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ የሚያጋጥማቸውን የሳይበር ጥቃቶች የመከታተል እና ለሚፈጠሩ ጥቃቶች ምላሽ የመስጠት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም በሀገራችን የሚገኙ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ራሳቸውን ከመሰል የሳይበር ጥቃቶች ለመከላከል በሶስት መሰረታዊ የሳይበር ደህንነት ጉዳዮች ላይ መስራት አለባቸው ያሉት ሀላፊው እነርሱም የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የአሰራር ስርአት መዘርጋት ፣ የሰው ሃይላቸውን በዘርፉ የሰለጠነ እና ብቁ ማድረግ እንዲሁም ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዋናነት የሀገሪቱን የኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማት ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሄራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ ሀገራዊ ሀላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው፡፡(ኢመደኤ)

Continue Reading
Click to comment

More in ሳይንስና ቴክኖሎጂ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top