Connect with us

ጳጉሜን የበጎነት ወር

ጳጉሜን የበጎነት ወር
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ጳጉሜን የበጎነት ወር

ጳጉሜን የበጎነት ወር

(ክርስቲያን ታደለ)

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንኳን ለጳጉሜን ወር በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የራሳችን በራሳችን ከምንኮራባቸው ጉዳዮች አንደኛው የዘመን አቆጣጠራችን ነው። የኢትዮጵያ የዘመን መቁጠሪያ እጅግ አጭርና 13ኛ ወር የሆነው ጳጉሜን ያስገኜ ነው። ወሩ በመንግስታዊ የሕዝብ አገልግሎት ተቋም ደመወዝ የማይከፈልበት፤ የቤት ኪራይም የማይከፈልበት ነው። 

ጳጉሜን የሰው ልጅ ከፈጣሪው የሚነጋገርበትም ነው። የመንፃትና ኃይማኖታዊ መልካም ነገሮችን የመከወኛ ወርም ነው።  ይህም ወሩን የበጎ ሥራ በመስራት እንድናሳልፍ እርሾ ሆኖ የሚያገለግለን ነው።

የተወደዳችሁ ወገኖቼ፦

የ2013 ዓመት አገራችን በርካታ ጉዳዮችን ያሰተናገደችበት ነው። የሰሜን እዝ መጨፍጨፍ፣ የማይካድራ ዘር ፍጅት፣ የጉሊሶ ጭፍጨፋ፣ የትግራይ ወረራ፣ ምርጫ፣ የጋሊኮማ ፍጅት፣ የአጋምሳ ጭፍጨፋ፣ የመተከል ፍጅት፣…እያለ እያለ የዓባይ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሊት ጋር ያደርሰናል። በእሳት ተራምደው በኦሎምፒክ ያኮሩን ጀግኖችንና የዋልያዎቹን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍስ ማን ይዘነጋል?   በእነዚህ አገራዊ ሰቀቀኖችና ደስታዎች ሁሉ ኢትዮጵያውያን አብረን አዝነናል፤ ስቀናልም። 

አገራችንን በሚያናውጣት ብርቱ ወጀብ እጅጉን ተፈትነናል። ብርቱዎች አርበኝነትን ሲጎናፀፉ ሰነፎች በባንዳ ስምሪት ተገኝተዋል።

የ2013 ዓመትን አሮጌ ብለን 2014ን እንኳን ደኅና መጣህ ለማለት እየተሰናዳን ባለንበት የጳጉሜን የመጀመሪያ ቀን ላይ ሆነን ማስታዎሻችን ስንገልጥ በመጀመሪያ የምናገኘው የበርካታ  ሚሊዮን ወገኖቻችን ጉዳይ ነው። አገርን ከመፍረስ፥ ሕዝብን ከመፍለስ ለመታደግ የሚደረገው የኅልውና ተጋድሎ እንደተጠበቀ ሆኖ ሚሊዮን ወገኖቻችን የሚያሳድድና የሚጨፈጭፍ ጠላት ብቻ ሳይሆን እኔን የሚል እምባ አባሽ፤ ፍቅር አጉራሽ ወገን እንዳላቸው በተግባር ማሳወቅ ይኖርብናል። ጳጉሜን ደግሞ ለወገናዊ በጎ ምግባር ሁነኛ ሰሞን ናት።

ውድ ኢትዮጵያውያን፦

ኢትዮጵያዊ ወግ ባሕላችን በሞት መካከል ብንሆን እንኳን ከቶውንም ሊረሳን የማይችል፤ በፈተናዎች የማይደበዝዝ የመሆኑን ኃቅ የምታውቁት ነው። ስለሆነም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የአዲስ ዓመት ወግ ልማድ ይገባቸዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ሁላችንም ተፈናቃይ ወገኖችን፣ የኅልውና ዘማች ቤተሰቦችን፣ የኑሮ ሁኔታዎች ያልተሟሉላቸው ወገኖችን፣ በእስር ቤት ያሉ ወንድምና እህቶችን፣…ልንዘይራቸው ይገባል። 

ይህን በማድረጋችን በሰማይም በምድርም በጎ ተብሎ ይፃፍልናል። አዲሱ ዓመት የስኬት እንዲሆንላችሁ ትፈልጋላችሁ? እንግዲያውስ በበጎነት ይጀምሩት! በድጋሚ እንኳን አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

የበጎዎች ምድር ኢትዮጵያ በክብር ትነሳለች!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top