መንግሥትነትን በዝርፊያ አጣችሁት፤ ይኼው አመል ቢያንስ ሽፍታ ሆኖ መኖርን እንኳን ሊነሳችሁ ነው!
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ዛሬ የተሸሸጋችሁበትና ያምታታችሁት ህዝብ ትናንት ትዝ ብሏችሁ አያውቅም፡፡ በሥልጣን ዘመናችሁ ከመቀሌ ይልቅ ታይላንድ በአስረሽ ምቺው ከርማችሁ ለስካርና ለዝሙት የሚሆን ብር ሲነጥፍ ወገኔ ብላችሁ ትግራይ ገባችሁ፡፡
ክብርና ስልጣን ነበራችሁ፤ ግን ያልዘረፋችሁት ነገር የለም፡፡ ከመሬት ተነስተው ቢሊየነር ስለሆነ ጄነራሎች ንብረት መወረስ ሲነገር እንኳን “ከየት አመጡት?” ከሚለው ይልቅ “የተጋሩ ጥቃት” እያለ የሚያወራው ግልብ ደጋፊ አስክሯችሁ ሀገር አወደማችሁ፡፡
እኛ ያልተደረገንነው ምንድን ነው? ደርግን ጣልን ብላችሁ ስትገቡም ዘርፋችሁናል፤ ለውጥ ተቀብለናል ብላችሁ ስትወጡም ዘርፋችሁናል፡፡ አናሳ ሆናችሁ እኩል እንሁን እንኳን ስንል እንደ ድፍረት ቆጥራችሁ የብሔር ጥላቻን በመስበክ የተበታተነች ሀገር ለመፍጠር ደክማችኋል፡፡
መንግስት ነበራችሁ፤ ግን ሌብነትን ክብር ሰጥቶ ካልተያዘ ችግር የለውም በሚል መሪ የሚመራ መንግስት፤ ወታደር ነበራችሁ ግን ያለ እረፍት ኮንትሮባንድ በመነገድ ለሚሊዮኖች ስደትና ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆናችሁ ታጋዮች፡፡
ያካበታችሁትን ልባችሁ ያውቀዋል፤ የዘረፋችሁትም እንዲሁ ታውቁታላችሁ፡፡ አዲስ አበባን አይቶ የማያውቅ የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም እጣ ወጣልኝ ብሎ የሚመጣባትን ዋና ከተማ ምን እንዳደረጋችኋት ልባችሁ ያውቃል፡፡
ኢትዮጵያውያን ላይ መድረቅ ይቻል ይሆናል ግን ልቦናችሁ የማይክደው ጸሐይ የሞቀውና ሀገር ያወቀው ብዙ ጉድ ነበር፤ ብዙ ግፍና መከራ ስቃይ እና ስቆቃ ከአስከፊ ዝርፊያና ሌብነታችሁ ጋር ተዳምሮ መንግስትነትን አጣችሁ፡፡
ሀገር ባንመራስ ክልል ብንመራስ ብላችሁ በገባችሁበት የመቀሌ መሰባሰብ ዘመናችሁም እንዲሁ የኢትዮጵያ እልቂት ሞትና መከራ ድግስ ደጋሾች ሆናችሁ፤ ዝርፊያውና ሌብነቱ ቀጠለ፤ እንደ አራት ኪሎው መቀሌን ለቃችሁ ዋሻ ከተታችሁ፤
ደግሞ ሽፍታና ነጻ አውጪ ነን ብላችሁ ትግል ስትጀምሩ ዳግም ሌብነት መርሃችሁ ይሆናል ብሎ የገመተ የለም፡፡ መርከብ ከመስረቅ ወደ ሊጥ ይዞ ሽሽት ይገባል ብሎ ማንስ ሊያስብ ይችላል?
የትግል ታሪካችሁ ሁለት ነባር እሴቶች ቆረጣና ዝርፊያ እንደሆነ ዳግም በታሪክ ፊት ለአዲስ ትውልድ አረጋገጣችሁ፡፡ ሀገር ዘርፋችኋል ብሎ ይጠላችሁ የነበረን ገበሬ ጎጆ ዘረፋችሁ፤ ሌባ ናችሁ ስትባሉ የሚሽኮረመሙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መጋዘን ሳይቀር መዘበራችሁ፡፡
ይሄ ዝርፊያ ውድመትና ስቆቃ ምናልባትም ሀገርን አንድ አድርጎ በአንድ አላማ አሰለፈ እንጂ የትግሉን ጥንካሬ አልቀየረውም፡፡ ኢትዮጵያ እንዳትዘርፏት፣ እንዳትገድሏትና እንዳታፈርሷት በጽናት ከዳር ዳር ቆማለች፡፡
ትናንት ትጠየፉት የነበረውን የትግራይ ህዝብ ዛሬ መሸሸጊያ አድርጋችሁ ቢወልዳችሁ አምኗችሁ ወደ ከፋ ስቃይና መከራ እየገባ መሆኑ አያሳስባችሁም፡፡ እናንተ ከምትመሩት ህዝብ ይልቅ አንድ መለኪያ ውስኪ የሚበልጥባችሁ ጨካኞች ስለሆናችሁ ድል አደረገን ብላችሁ የታማኝ በየነን ቤተሰብ እንዲያ ስታሰቃዩ በአጻፋው የእኛ ቤተሰብ እንዲህ ያለ ነገር ቢገጥመውስ የሚለው አያሳስባችሁም፡፡ ንጹሃን የሚለው ቃል የፖለቲካ መነገጃችሁ እንጂ መርሃችሁ አይደለም፡፡
ለገዛ እናቱ የማያስብ እና በገዛ እናቴም ቢመጡብኝ ደስታዬ እጥፍ ነው የሚል ሀሺሻም ለገዛ ሀገሩ ያስባል ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ግን ለሀገሩ የሚያስብ ሀገሩን የሚያድን ለሀገሩ የሚሆን መቶ ሚሊዮን ህዝብ አለ፡፡