Connect with us

ከሁለት ዓመት በፊት ጋዜጠኛ ደረጄ ትዕዛዙ ከአንጋፋው ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ጋር ያደረገው ቃለምልልስ

Social media

ነፃ ሃሳብ

ከሁለት ዓመት በፊት ጋዜጠኛ ደረጄ ትዕዛዙ ከአንጋፋው ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ጋር ያደረገው ቃለምልልስ

ከሁለት ዓመት በፊት ጋዜጠኛ ደረጄ ትዕዛዙ ከአንጋፋው ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ጋር በሕይወትና በሥራዎቹ ዙርያ ያተኮረ ቃለምልልስ አካሂዶ ነበር። ቃለምልልሱ የታተመው “ታዛ” በተሰኘው መፅሔት ላይ ሲሆን ለትውስታ ያህል እነሆ አቅርበነዋል። መጠነኛ የአርትኦት ሥራ ተደርጓል። መልካም ንባብ።
***
“ጤናማ ነኝ… ዘፈን አላቆምኩም!!”አለማየሁ እሸቴ

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ጥበብ እድገት ውስጥ አሻራቸውን ካኖሩ አንጋፋ ድምጻውያን አንዱ ዓለማየሁ እሸቴ ነው። በተለያዩ ዘመናት በሸክላ፣ በካሴትና በሲዲ ያሳተማቸው አልበሞች ብዛት አላቸው። በዘፈኑ ያልዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የሉም።

ስለአገር፣ ስለ እናት፣ ስለ አባት፣ ስለ ልጅ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ይቅርታ …። በስሜትና በተመስጦ ሲዘፍን ተመልካችና አድማጮችን ቀልብ የመግዛት ልዩ ኃይል ያለው ዓለማየሁ፤ በመድረክ ላይ በሚያሳያቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎችና ዳንስ ይማርካል። በዚህም «ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ» የሚል ቅጽል እስኪሰጠው ድረስ የተወደደ ነው። ዛሬ እንግዳችን ነው።

እንዲህ ያለ ተወዳጅ የጥበብ ሰው «አንቱ» አይባልም በሚል እሳቤ «አንተ» ልለው ወደድኩ። እርሱም ደስ ብሎት ፈቀደ። እናም እንዲህ ቀጠልን።

ታዛ፦ አንድ ወቅት ዘፈን ማቆምህ ተሰምቶ ነበር። ምናልባት ያ የሆነው ከዚሁ ከጤንነትህ ጋር ተያይዞ ይሆን? በእርግጥስ ዘፈን አቁመሃል?

ዓለማየሁ፦ እዚህጋ ትልቅ ስህተት አለ። የእኔን አባባል ጥቂት ሰዎች ያወላገዱት መስሎኛል። «አልዘፍንም» ብዬ ስገልጽ በዚህ ዕድሜዬ በየምሽት ክለብ እየዞርኩ አልዘፍንም ማለቴ እንጂ፤ ዘፈን ሙሉ ለሙሉ አቆምኩ ማለቴ አልነበረም።

በእነዚህ ክለቦች ስዘፍን የልጅ ልጆቼ የሚሆኑ አንገቴን እያቀፉ «ውስኪ ጠጪ» ይሉኛል። «አንቺ »እያሉ። ክብሬን ዝቅ የሚያደርግ ቦታ በመገኘቴ ነው ያ የሆነው። በዚህ ጊዜ ሰው ላይ ከመፍረድ ፋንታ እራሴ ላይ ለምን አልወስንም ብዬ የምሽት ክለቦች ውስጥ አልዘፍንም ማለቴ ለእኔ ትክክል ነው። ቃሌን በሌላ ትርጓሜ የተረዱ ካሉ በዚህ ይስተካከል።

ትልልቁን ስራ፣ ቁምነገሩንማ የግድም መስራት አለብኝ። እኔ ዘርፌ አላድር፣ ድሮም ቤተሰቦቼን ሳስተዳድር የኖርኩት እኮ ዘፍኜ ነው። ለስሜቴ ብቻ ሳይሆን ለእንጀራዬ እዘፍናለሁ። የሕዝብን ፍላጎት አከብራለሁ። አድናቂዎቼ፣ አክባሪዎቼ ስራዎቼን እስከወደዱ ድረስ በሙያዬ እቀጥላለሁ።

ዝም ብሎ ቁጭ ማለት ራሱ ዝገት ያመጣል። ጤናዬን እስካገኘሁ፣ እግዚአብሔር እስከፈቀደልኝ ድረስ በመጠኑም ቢሆን እየዘፈንኩ ኑሮዬን እመራለሁ።

ታዛ፦ በሕይወት ዘመንህ ምን ያህል ስኬታማ ሆነሃል?

ዓለማየሁ፦ ከመጠን በላይ ስኬታማ ነኝ። ጥሩ ኖሬያለሁ፣ ዛሬም ድረስ ጥሩ ሕይወት አለኝ። በሙያዬ ከአገሬ አልፎ ዓለምን ዞሬያለሁ። በወገኖቼ ዘንድ በዚህ ሙያዬ ተወዳጅነትን አትርፌያለሁ።

በጥፋቴ እየመከሩኝ፣ እየገሰፁኝ፣ በመልካም ስራዬም እያመሰገኑኝ ያሳደጉኝ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ናቸው። ይከበሩልኝ።

ታዛ፦ ስለ ማንነትህ ሲነገር ኤልቪስ ፕሪስሊ አብሮ ይነሳል፤ በወጣትነትህ ከአለባበስና ከፀጉር አበጣጠርህ ጀምሮ በዘፈንም እሱን የመሆን ስሜት እንደነበረህ ይታወቃል:: ይህ ከምን መጣ?

ዓለማየሁ፦ ከመውደድ እና ከማድነቅ ነው። ያኔ በሕልሜ ጭምር የማየው እሱን ነበር። ስጀምር የሱን ዘፈን ነበር የምዘፍነው። የአማርኛ ዘፈን አላውቅም። በ1955 ዓ.ም አካባቢ ወደ ፖሊስ የሙዚቃ ከፍል ስገባ ነው በአማርኛ መዝፈን የጀመርኩት።

የጥላሁን ገሠሠ የአዘፋፈን ስልት ነው ወደዚያ የጎተተኝ። ከመጠን በላይ እወደውም የነበረው እሱን ነው።

ታዛ፦ ለመሆኑ ኤልቪስን አግኝተኸው ታውቃለህ?

ዓለማየሁ ፦ በፍፁም! የት ደርሼበት። ባገኘው ደስ ባለኝ ነበር። ወደ ውጪ መውጣት ስሜቱ ያደረብኝ በዚህ ነው። በአሰብ በኩል ጠፍቼ ልሄድ ብዬ መርከብ ላይ ተይዤ ተመልሻለሁ።

ኋላ ላይ ተሳክቶልኝ በዘፈኔ አሜሪካና አውሮፓን ጨምሮ በርካታ አገራትን ለማየት ችያለሁ። እሱን ግን ላገኘው አልቻልኩም።

ታዛ ፦ ወደ ሙዚቃው ዓለም ስትገባ የፖሊስ የሙዚቃ ክፍል መነሻህ እንደሆነ ይታወቃል፤ የአገባብህን ሁኔታ እንዴት ታስታውሰዋለህ?

ዓለማየሁ፦ እሱ ታሪክ አለው። በ1955 ዓ.ም አካባቢ ነው። ያኔ አባቴ ኑሮውን ለውጦ ሙዚቃ ክፍል ባልደረባና ሌሎችም ችሎታዬን የተረዱ እያባበሉ ወደፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ዘንድ ስቀመጥ ተቆጣጣሪ አልነበረኝም። ታዲያ እየሾለኩ ምሽት ክለብ ዘፈን ማየት ጀመርኩ።

ነፍሱን ይማረውና ፒያኖ እና አኮርዲዮን ይጫወት የነበረ አሰፋ ረዲ የሚባል ሰው በፖሊስ የሙዚቃ ከፍል ውስጥ ነበር። በትርፍ ጊዜው መርካቶ ውስጥ አዲስ አበባ ሆቴል ይጫወታል። ተዋወቅኩት። ያኔ ትምህርት ቤት የአንግሊዝኛ ዘፈኖችን እንደምጫወት ሰምቶ ኖሮ በሆቴሉ እንድዘፍን ያበረታታኝ ጀመር። መዝፈን ጀመርኩ።

ከዚያ ተስፋዬ መኩሪያ የሚባል የታወቀ የፖሊስ ዘፋኝ፣ ጥበቡ በላቸው የሚባል የግጥም ደራሲና የሐረር ሙዚቃ ክፍል ባልደረባና ሌሎችም ችሎታዬን የተረዱ እያባበሉ ወደፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ወሰዱኝ። ኮሎኔል ረታ ዘንድም አቀረቡኝ። በዚያን ጊዜ ሻለቃ ነበሩ። ቦርጫም ናቸው። በኋላ ሳውቃቸው በጣም ሳቂታ፣ ገርና ደግ ሰው ነበሩ።

ጭንቅላቴን አሻሹኝና «እስኪ ዝፈኚልኝ» አሉኝ። በዚያን ጊዜ ይህን ያህል መብሰል የለምና ማፈር የለም። ነፍሱን ይማረውና ሃምሳ አለቃ አያሌው አበበን ፒያኖ ያዝ አሉት፤ ያዘ። የመጣልኝን እዘፍን ጀመር። እርሳቸው በዘፈኔ ተማርከው ዳንስ ጀመሩ። ወዲያው የሙዚቃ ክፍሉ ባልደረቦች ከበቡኝ። «ይሄ ልጅ ከዚህ ቤት አይሄድም» ብለው አስቀሩኝ። እዚያው ግቢ ቀረሁ። ቀረሁ። እርሳቸው አባት ሆኑኝ፣ በቃ።

እግዚአብሔር በፈቀደው ነው የሚሆነው። የእኔ መንገድ ያ ነው ብዬ አላስብም ነበር። የሆነ ሆኖ ወደ ስድስት ዓመት አካባቢ ፖሊስ ውስጥ ሰርቼ ነው ወደ ተለያዩ ናይት ክለቦች ተዟዙሬ መስራት የጀመርኩት። የራሴ ባንድም ነበረኝ።

ታዛ ፦ ወደ ሙዚቃው መግባት ስትጀምር ቤተሰብ ፈቀደልህ?

ዓለማየሁ፦ በፍፁም! በፍፁም አልፈቀደልኝም። በተለይ ለአባቴ ብርቱ ሀዘን ነው የሆነበት። አባቴ ከነበረው መጥፎ አጋጣሚ የተነሳ ትምህርት ለመማር አልቻለም ነበረ። በዚህም ከጣሊያኖች ጋር በአሽከርነት ተቀጥሮ መኪና መንዳትና ሜካኒክነት ሁሉ ሰልጥኖ ኑሮውን ለመምራት ታግሏል። ከዚያ ደረጃ ወጥቶ በጥረቱ ነው ሀብት ያገኘው።

አንድ ልጁ እኔ ብቻ ስለሆንኩኝ ያንን ቁጭቱን በእኔ ሊወጣ ይፈልግ ነበር። እንድማርለት ነበር ድካሙ። ሳልሆንለት በመቅረቴ ክፉኛ አዝኖ፣ ተበሳጭቶ በሽጉጥ ሊገለኝ ፍለጋ ይዞር ነበረ። እንደ አባቴ የማያቸው ኮሎኔል ረታ ናቸው እየደበቁ ያተረፉኝ። እስከታረቅን ድረስ።

ታዛ፦ ስለዚህ «ተማር ልጄ» የተሰኘው ዘፈንህን በዚህ መነሻነት ይሆን የዘፈንከው?

ዓለማየሁ ፦ አዎ ትክክል ነው። በዚያ ነው የዘፈንኩት። ግጥሙም ዜማውም የራሴ ነው። እውነተኛው የእኔና የአባቴ ታሪክ ነው። ከጊዜ በኋላ ነው የዘፈንኩት እሱንም።
ታዛ ፦ እርሳቸው ካለፉ በኋላ?
ዓለማየሁ ፦ አይደለም፤ በሕይወት እያለ ነው። መጀመሪያ «ሕይወቴ አባቴ ነው፤ ሴት ያሳደገው ልጅ ከመባል ዘወትር…» የሚለውን ዘፈንኩ።

ታረቅን። ከዚያ እዚህ ራስ ሆቴል (ቃለ መጠይቅ እያደረግን ያለንበት ሆቴል ነው) የራሴን ባንድ አቋቁሜ ጥሩ ስራ እየሰራሁ ባለሁበት ወቅት ሌሎች ሙዚቀኞችን ያባብሉና ድንገት ወደ አስመራ ይዘውብኝ ይሄዳሉ። እዚህ ኮንትራት ፈርሜያለሁ። ምን ይዋጠኝ? ተበሳጨሁ። አዘንኩ። ውስጤ ተነካ።

በዚህ ቅፅበት ብዙ አሰብኩ። አባቴ ተማር ልጄ እያለ ሲወተውተኝ ባለመማሬ የነበረኝ ቁጭት ድንገት ገነፈለ። ታዲያ ወዲያው ብቻዬን ጊታሬን ይዤ መድረኩ ላይ ወጣሁና እያነባሁ «ተማር ልጄ»ን ዘፈነኩ። በግጥምም ሆነ በዜማ ቀድሜ ያልተዘጋጀሁበትን ይህን ዘፈን ስዘፍን የአባቴን ምክር ባለመስማቴ የማያዋጣኝ ሙያ ውስጥ ገብቼ መጎዳቴን የሚነግር ነበር።

ይህን ዘፈን ሳንጎራጉር እኔ ሳላያትና ሳላውቀው ባለቤቴ በመስኮት በኩል ሆና በቴፕ ትቀዳኝ ነበር። (ሳግ ተናነቀው)። ያ ወደ እውነትነት ተለወጠ። ስሜቴን ለማርገብ በአጋጣሚ ያንጎራጎርኩት ይህ ግጥምና ዜማ ጎልብቶ ባልገመትኩት ሁኔታ ኋላ ላይ የብዙዎች መማሪያ ሆኖ ዘለቀ።

ታዛ ፦ ያ በባለቤትህ የተቀረፀው ነው እንዴ እስካሁን የሚሰማው?

ዓለማየሁ፦ አይደለም። እግዚአብሔር ይስጣቸው ዛሬም በሕይወት አሉ፤ ፊሊፕስ ኩባንያ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ አቶ ካሳሁን እሸቴ እና አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ ጎትጉተው «ሌላ ሳንጨምርበት ይህንን ብቻ እንቅረፀው» ብለው እንደገና ስቱዲዮ አስቀረፁኝ። እውነትም ይኸው ታሪክ ሆኖ ቀረ።

ይህን በማንጎራጉርበት ጊዜ አባቴም ነበረ። ምን ያህል ቁጭት ውስጥ እንደገባሁ የተረዳው ያኔ ነው። እውነተኛ ይቅርታና ፍቅር የመጣውም ከዚያች ቀን በኋላ ነው። የሰው ልጅ የእንጀራ ገመዱ ምን እንደሆነ አይታወቅም፤ እኔም በትምህርቱ ባይሳካልኝ በሙዚቃው ያው የምታየኝ ደረጃ ላይ ነኝ።

ታዛ ፦ የዘፈኑን ምክር አዘል መልዕክት ልጆችህ እንዲገነዘቡ አድርገሃል?

ዓለማየሁ ፦ በሚገባ። እነሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎቸንም እየመከርኩበት ነው። ‘ለእኔ ብለህ ስማ’ ይባላል እኮ። ብዙ ሰው ምን ማለት እንደሆነ እየተረዳ ተጠቅሞበታል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቴ ደግሞ አባቴ ነው።

ታዛ ፦ በአሁኑ ማንነትህ የሚገለጽ ሌላ የአባትህ ውርስ ይኖር ይሆን ?

ዓለማየሁ ፦ አባባ መልካም ሰው ነበረ። እኔ በጥረቴ ባድግም ችግርን እንዳይ አልሆነም። ከባድ መኪናዎች፣ የድንጋይ ካባ መኪናዎች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የቡና እርሻ ሁሉ ነበሩት። ነፍሱን ይማረውና ዛሬም በልጅነት አዕምሮዬ የቀረፅኩት ትዝ ይለኛል።

ድንጋይ ካባ ላይ ሲሰሩ የቆዩት ወዛደሮች ልክ ከስራ ሲወጡ፤ የስጋ አገር ከሆነችው ቦዲቴ ከተማ በመኪና ሮጦ ሽንጥ ስጋ ገዝቶ ይመጣና ጠረዼዛ ላይ አጋድሞ ጠጅ አስመጥቶ «በሉ ብሉ። እንብላ የእናንተ ላብ አኮ ነው» እያለ አብሮ ይበላ ነበር። አባቴ ትምህርት ከሰጠኝና ካወረሰኝ ባህሪው አንዱ ይህ ነው። ፍቅርን፣ የሰው ልጅ እኩልነትን፣ ቀናነትን…።

ታዛ ፦ በበእግረ መንገድ ስለ እናትህ የምትለን ካለ?

ዓለማየሁ ፦ ገርና ደግ ሰው ነበረች። ይህንን በልጅነቴ ብዙም አላውቀውም፤ ምክንያቱም እኔ በእንጀራ እናት ነው ያደኩት። እሷን ካወቅኩኝ በኋላ ህመም መጣ። የፍቅር ህመም ታውቃለህ? ለካስ እንዲህ ያለች እናት አለችኝ የሚያሰኝ የቁጭት ህመም! ያኔ ግፋ ቢል 11 ዓመት ይሆነኛል። በቅሎ ቤት አካባቢ ክርስቲያን ትሬኒንግ ኢንስቲቲዩት (CTI) በአዳሪነት እማር ነበር።

በወር በወር ከአርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ዮሐንስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ካለው የአባቴ ቤት ከቤተሰቦቼ ጋር እንዳሳልፍ ፈቃድ ይሰጠኛል። ታዲያ አንድ ቅዳሜ እኔን ለማየት ብላ አባቴ ዘንድ መጣች። አባቴ ደግሞ በላይነሽ መጣች ብሎ ከፍተኛ ድግስ እንዲደረግ ለእንጀራ እናቴና ለቤት አገልጋዮች አዟል። ቤት ስገባ ብዙ ሰው ተሰብስቦ ድግሱን ይቋደሳል።

ቤተሰቦቼንና የማውቃቸውን ስሜ እናቴን ዘለልኳት። አላውቃትማ። «እንዴ ማነች ይህች ሴትዮ? አታውቃትም እንዴ?» አሉኝ። «አላውቅም» መለስኩ። «ማንን ትመስልሃለች?» ሲሉኝ። «እማማ ቦሰናን ይመስላሉ» አልኩ። እማማ ወሰና አክስቴ ነች። የእሷው እህት። በዚህ ጊዜ እናቴ ከማዕዱ ስጋ የምትቆርጥበትን ቢላ አንሰታ አባቴን ልትገድለው ነብር ሆና ተነሳች። «ስጋዬን ቆርጠህ ጣልከው» እያለች አምርራ አለቀሰች።

ተቃቅፈን ተላቀስን። ስለእኔ ሳትነግረው፤ ሳታስተዋውቀኝ በመቆየትህ ይህ ተከሰተ ነው የእሷ ሀዘን። እንደማትጠግብ ሆና እየሳመችኝ አምስት ብር ሰጠችኝ። ያንን ይዤ ወደ ውጪ ወጣሁ። ብስክሌት መንዳት እወድ ነበርና ተከራይቼ መንዳት ያዝኩ። እናቴ ቤት እያለች። ከአባኮራን ሰፈር ወደ ቢስ ቤት ቁልቁለቱን ስወርድ ቶፖሊኖ የምትባል ትንሽዬ የጣሊያን መኪና ከፊት ለፊቴ ዳገቱን ትወጣለች።

እየነዳሁ በሀሳቤ ደስ ብሎኝ እናቴን ነበር የማያት። የብስክሌቴ ጎማ የሚረግጠው ደሞ የፈረስ ፋንዲያ ነበር። ካፊያ ነበር። ድንገት አንሸራተተኝና ተጠቅልዬ የመኪናዋ አፍንጫ ስር ገባሁ። እግዚአብሔር ትረፍ ሲለኝ የሚነዳው ፈረንጅ ሾፌር ቶሎ ፍሬን ያዘ።

ከእኔ ይበልጥ እሱ በጣም ደነገጠ። «ማሙዬ… ማሙዬ… ምነው ምን ሆንክ? ምንድነው ችግርህ?» ፀጉሬን እያሻሸ በሀዘኔታ ጠየቀኝ። ሁኔታውን ነገርኩት። በጣም ተሰማው። የማላስታውሰውን፤ በወቅቱ በርከት ያለ የሚባል ገንዘብ ሰጠኝና ሸኘኝ። ታዲያ ያቺ ቀን አሁን እንኳ ሸምግዬ በብሩህ ትታየኛለች።

“አባቴ ከጣሊያኖች በ30 ብር የገዛት ክፉንችላ ውሻዬ ጓደኛዬ ነበረች። ግጥሙ የእኔን ታሪክ የያዘ ይመስል ነበረ። ብዙ የተመሳሰለ ነገር ስለነበረው ጥርጣሬ አሳደረ። የሚያሳዝነው እንጀራ እናቴም፤ እሷ ከሌላ የወለደችው ወንድሜም እስኪያልፉ ድረስ በዚህ ዘፈን አኩርፈውኛል”
ከዚያ በኋላ አብረን የመኖር ሁኔታዎች ባይመቻቹልንም እየተጠያየቅን በጥሩ እናትና ልጅ ፍቅር እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ ኖርን። በዚሁ ዓመት አለፈች። መልካምነቷን በቃላት ለመግለጽ ያዳግተኛል። (እንባ አቀረረ)።

ታዛ ፦ ዘፍነህላቸዋል ልበል?

ዓለማየሁ ፦ አዎ! «በልዬ በልዬ አሞራ እንዳይበላኝ እኔ ላንቺ ብዬ…» የሚል ነው። በላይነሽ የሱፍ ትባል ነበር። ግጥሙም ዜማውም የእኔ ነው።

ታዛ ፦ አንዳንዶቹ ዘፈኖችህ ምክንያታዊ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ። ስለ እንጀራ እናትም የዘፈንከው አለ?…።

ዓለማየሁ ፦ አዎ አለ፤ ግን አጋጣሚ ነው። እኔ በእንጀራ እናት ስላደኩኝ ሆን ብዬ የዘፈንኩት አይደለም። በእርግጥ በአባቴ ቤት ይደረግ የነበረው እዚያ ግጥም ላይ አለ። ለምሳሌ አባቴ ከጣሊያኖች በ30 ብር የገዛት ክፉንችላ ውሻዬ ጓደኛዬ ነበረች። ግጥሙ የእኔን ታሪክ የያዘ ይመስል ነበረ። ብዙ የተመሳሰለ ነገር ስለነበረው ጥርጣሬ አሳደረ። የሚያሳዝነው እንጀራ እናቴም፤ እሷ ከሌላ የወለደችው ወንድሜም እስኪያልፉ ድረስ በዚህ ዘፈን አኩርፈውኛል። እነሱ ላይ የዘፈንኩባቸው መስሏቸው። ግን አይደለም። እንጀራ እናቴ ጥሩ ሰው ነበረች።

በህልፈቷ ማግስት በህልሜ አይቻት ስጨነቅላት ነበር። ያ ህልም የመጣው እውነተኛ አክብሮትና ፍቅር ስለነበረኝ ነው ብዬ አስባለሁ። ዘፈኑ ስለተሰጠኝ ዘፈንኩት እንጂ እንጀራ እናቴን የሚገልፅ አልነበረም።

ታዛ ፦ እንዴ የዚህ ዘፈን ግጥምና ዜማ ያንተ አይደለም አንዴ?

ዓለማየሁ ፦ የኮሎኔል ግርማ ኃይሌ ነው። ሌሎች በጣም የተወደዱልኝ ግጥምና ዜማዎችንም የሰጠኝ እሱ ነበር፤ ይህንንም ሲሰጠኝ የራሱ ምከንያት ሊኖረው ይችላል። ነፍሱን ይማረውና … ።

ታዛ ፦ ልጆች እንዳሉህ አውቃለሁ፤ ስንት ናቸው?

ዓለማየሁ ፦ ሰባት። አራት ወንድ ሦስት ሴት። ከውዷ ባለቤቴ ያገኘኋቸው ናቸው። ሁሉም ለቁም ነገር በቅተውልኛል። ሁሉም ተምረዋል። ስራ ይዘዋል፣ ውጪ የሚኖሩ፣ ያገቡም አሉ። ለአያትነት ወግም አብቅተውኛል። ዛሬ ከልጅ ልጆቼ ጋር ነው ኑሮዬ። በዚህ እድለኛ ነኝ። ከዚህ በላይ ምን ፀጋ አለ? ያ ሁሉ ዘመን ታልፎ፣ ዕብደቱ ቀርቶ፣ መጠጡ፣ ጭፈራው …ጤናዬ ተመልሶ … እግዚአብሔር ይመስገን።

እንደ ጅማሬዬ መጥፎ ቦታ ልወድቅ ይገባኝ ነበረ፤ ነገር ግን በእኔ ዕውቀት ሳይሆን በአምላኬ እርዳታ ቀና መስመር ውስጥ ገብቼ ነው ለዚህ የበቃሁት። ታዛ ፦ ከባለቤትህ ጋር በጽኑ ትዳር ከ50 ዓመት በላይ እንደኖሯችሁ ሰማሁ፤ የወርቅ ኢዩ በልዩ አልተከበረም?
ዓለማየሁ ፦ ወጉን አልፈለኩም፤ እውነተኛውን ፍቅር ነው የምመራው፤ መታየትን፣ በዚህ መወደስን አልፈለኩም። እርግጥ ለሌሎች ምሳሌነትን ማሳየት ክፋት የለውም። ያንን ግን አላደረግንም። ምናልባት ወደፊት…።

ታዛ ፦ ባለቤትህን «አባዬ» እያልክ እንደምትጠራት ሰማሁ? ስለምን ይሆን?
ዓለማየሁ ፦ እጅግ በጣም ጥሩ ሰው ስለሆነች፤ በጣም ስለምወዳት፣ ስለማከብራት… ምን ልበልህ በቃ በእናት መሰልኳት። መቼስ ስለ እናት ምንነት መናገር አይጠበቅብኝም፤ ሁሉም ስለሚረዳው…።
ታዛ ፦ ስማቸው?

“አሁን አጓጉል ነገር እየተፈጠረ ነው ያለው እኮ። ድሮ በእኛ ጊዜ ያላመንበትን ነገር ለህዝብ አናቀርብም። ዛሬ አሰሱም ገሰሱም አልበም ይባላል። እኔ እዚያ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ጥራት ያለው ነገር አንድ ወይም ሁለት ነገር ብንሰራ ጥበብ ይጎለብት እንደሆን እንጂ፤ አይኮስስም ”

ዓለማየሁ ፦ ዓየሁ ከበደ ደስታ። በነገራችን ላይ እኔ ነኝ እንደዚያ አሳጥሬ የምጠራት እንጂ፤ ዓየሁ አለም ነው ስሟ። የእኔ ስም ተገልብጦ ሲነበብ የእሷን ስም ያመጣል። ጥምረታችን እዚህ ድረስ የተሳሰረ ነው። ይህንን ደግሞ እግዚአብሔር በተአምር የሰራው ነው ብዬ አምናለሁ።

ታዛ ፦ በመድረክ ላይ የምታሳየው የዳንስ እንቅስቃሴ ቀልብ ይገዛል፤ እኔም ይህን የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም 60ኛ የልደት በዓልና ትወና የጀመረበት 40ኛ ዓመት በብሔራዊ ቴአትር ሲከበር አይቻለሁ፤ ይህ የኤልቪስ ፕርስሊ ተጽዕኖ ይሆን?

ዓለማየሁ ፦ አይደለም። አይደለም። ምናልባት እራሴን ማሞገስ አይሁንብኝ እንጂ የሙዚቃ አስተማሪያችን ሙሴ ነርሲስ ናልቫዲያን ለሰው ሁሉ የሚናገሩት አንድ ቋንቋ ነበራቸው። «ይሄ ልጅ ውስጡ የሚነዝር ስሜት አለው። ውስጡ ልዩ ፍጥረት ነው» ይሉ ነበር። እውነታቸውን ነው። ስዘፍን ስለማንም ሰው ደንታ የለኝም። ስሜቴን ነው የማዳምጠው። ለዚህም ነው ስዘፍን ዓይኔ የሚጨፈነው። ራሴ ውስጥ ነው የምገባው።

ታዛ ፦ ሆደ ቡቡ ነህ ልበል ጋሽ ዓለማየሁ?

ዓለማየሁ ፦ በሚያስደስት ነገር እደሰታለሁ፤ በሚያስከፋው ነገር እከፋለሁ። የህዝብ ጉዳት ያንገበግበኛል። ምሳሌ ላንሳልህ። መጀመሪያ ላይ ያነሳህልኝ ህመም በተከሰተ ጊዜ ነው። ኮልስትሮል ነው ከልብ ጋር የተያያዘው። የደም ማዘዋወሪያዎች የሆኑ ሦስት አርተሪዎች ተዘግተው ነበረ። ያንን የሚያፈርስ ነገር በአስቸኳይ ይፈለጋል። ይህንን ህክምና ሊሰጡ የሚችሉ አልተገኙም። አንዲት መድኃኒት ግን አለች። እሷ መድኃኒት በአስቸኳይ መገኘት አለባት ብለው ዶክተሮች አዘዙ።

በየፋርማሲው፣ በየሆስፒታሉ ቢፈለግ ጠፋ። ከቤቴ ብዙም ሳይርቅ ሲ ኤም ሲ አካባቢ አንዲት ሴት ባላቸው ይሁን ወንድማቸው ይህ ነገር ገጥሟቸው ኖሮ የገዙት ክኒን እንዳለ በወሬ ወሬ ተሰማ። ከሞት ያተረፈችኝ ይህች ክኒን በተገዛችበት ዋጋ አምስት ሺ ብር ተገዛች። ያቺን ክኒን ወሰድኩ:: ወዲያውኑ የተዘጋው ቦታ ተከፈተ። ያውም ከሦስቱ አንዱ። መለስ ሲልልኝ የአውሮፓ ትኬት በአስቸካይ ተዘጋጀ፤ ለከፍተኛ ህክምና ጣሊያን ሀገር ሄድኩኝ።

እዚያ ባገኘሁት ዘመናዊ ህክምና ክፍሌ ውስጥ ባለ ስክሪን ስከታተል፤ ዶክተሮቹ ከፀጉር የቀጠነ ነገር በእጄ ጠርቁሰው ወደ ልቤ በመስደድ ተዘግተው የነበሩትን የደም መዘዋወሪያዎች ከፈቷቸው። ህክምናው ሲጠናቀቅ 40 ደቂቃ አልሞላም ነበር። ለእነሱ ቀላል ህክምና ነው። ይህን የሚያደርጉት እያዋሩኝ ቢሆንም፤ እኔ ግን በሁለቱም ዓይኖቼ እንባ ይፈስ ነበር።

ታዛ ፦ ለምን ?

ዓለማየሁ ፦ ለእኔ የተደረገውን ለሌሎች ማድረግ ባለመቻሌ። እኔ ደጋፊ አግኝቼ፤ አቅም ኖሮኝ ታከምኩኝ፤ ዳንኩኝ። ገንዘብ የሌለው ግን ዓይኑ እያየ ይሞታል። ይህን ሳስብ ነው አምርሬ ያለቀስኩት። በአገራችን ህጻን ልጁ ታሞበት እየተሳቀቀ ሞቱን የሚጠብቅ፣ አስፕሪን መግዣ እያጣ በህመም የሚሰቃይ ድሃ ሞልቷል። እንዲህ በቀላሉ ልንቋቋመው የማንችለው ችግር በብዙሃኑ ላይ ይታያል። ይህ ነው ያስለቀሰኝ። ሃብት እንደጎርፍ ጥርግ ብሎ በአንድ አቅጣጫ እየሄደ የተወሰኑ ሰዎች ዘንድ ይገባል።

በሌላ በኩል ብዙሃኑ የሚበላው እያጣ፣ የሚታከምበት እያጣ «ዜጋ ነኝ» ይላል። ያ ብር ያለው ልጄን፣ ቤቴን ንብረቴን፣ ገንዘቤን እንጂ አገሬን አይልም። ተሽቀዳድሞ ስለ አገሩ የሚሞተው ግን ድሃው ነው። አስፕሪን መግዣ የሌለው። (አሁንም ዓይኑ እንባ አቀረረ፤ ሳግ ተናነቀው)

ታዛ ፦ ስለ አገር ስታነሳ አገራዊ ዘፈኖችህ ላይ ስሜትህ ጥልቅ እንደሆነ ተስተውሏል…፤

ዓለማየሁ ፦ አዎ አገር አገር ናት! ለማንም አልዘፈንኩም። እያንዳንዳችን አገሬ ልንል ይገባል‐ በዜግነታችን። ሌላ አገር የለንማ! ቢጨፈልቁኝ፣ እንደገና ቢሰለቅጡኝ አሜሪካዊ ልሆን አልችልም። እንግሊዛዊ ልሆን አልችልም። እኔ የዚህ የድሃው ወገኔ ዘር ‐ኢትዮጵያዊ ነኝ። በዚህ እኮራለሁ፤ እደሰታለሁ።

ስዘፍንም ከዚያ ስሜት አንጻር ነው። በአገር ወረራ ጊዜ እንደ ጓደኞቼ ድንበር ድረስ ዘምቼ፤ በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዘፍኛለሁ። እኔ ስናገርም ሆነ ስዘፍን በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ላስተምርም አልፈልግም። ሁሉም ስለ አገሩ ያውቃል፤ ይረዳል ብዬ የማምን ነኝ። የግል ፍላጎቴን ግን እናገራለሁ።

ታዛ ፦ ዛሬ ተመልሰህ ልታደርገው የማትችለውና ቁጭት ውስጥ የከተተህ ነገር አለ?

ዓለማየሁ ፦ አለ። አለ። አንዱን ልንገርህ። «ማሪኝ ብዬሻለሁ» ከተሰኘው ዘፈኔ ጋር የተያያዘ ነው። ርዕሱ እና ጅምሩ በጋሽ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ነው የተጻፈው። በ1958 ዓ.ም ይመስለኛል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ውስጥ በእንቁጣጣሽ ፕሮግራም ላይ እንድዘፍን ተደረገ። በዚህ ዘፈኔ ተለሳልሼ ነው የቀረብኩት። የዜማውና የግጥሙ ባህሪ ነው እንደዚያ ያደረገኝ።

ህዝብ ያልጠበቀው ስለሆነ ሁኔታዬ እንደሌላው ጊዜ ጭብጨባ አላስገኘልኝም። የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ባልደረባ የነበሩ ሻምበል ኑሩ ወንዳፍራሽ የተባሉ ሰው ግን ዘፈኔን እጅግ ተመስጠው ይመለከቱ ኖሯል። ከመጠን በላይ ተደስተዋልም። እኚህ ሰው የአንዲት ታዋቂ ዘፋኝ የትዳር አጋር ናቸው። እንደ ቅጣት በግዞት ጋምቤላ አካባቢ ተልከው ለበዓሉ መምጣታቸው ነው። ዘፈኔን ጨርሼ ከመድረክ እንደወረድኩ ወዲያው መጡ። ሳሙኝ።

በጣም ሳሙኝ። እኔ ከኮሎኔል ረታ ጋር ቆሜያለሁ። «አንቺ ዱርዬ አሁን የዘፈንሻት ዘፈን በጣም ጥሩ ነች፤ አንድ ግጥም እሰጥሻለሁ ጨምረሽ ትዘፍኛታለሽ» አሉኝ። ወዲያውም «ኮሎኔል እባክዎ ይፍቀዱልኝና ይቺ ዱርዬ ግጥሜን ጨምራ ትዝፈንልኝ» ሲሉ ተማጸኑ። «አምጣው ችግር ይለም ትዘፍናለች» አሏቸው። በማግስቱ መኪና እየነዱ ካምፕ ድረስ ይዘውት መጡ።

አነበብኩት። ወደድኩት። «ፀጉርሽን ኮፍሺው በአልማዝ ማበጠሪያ ይሁንልሽ ላንቺ የስምሽ መጠሪያ በስም መጠራቱ ላንቺ ያንስሻልና የቆንጆዎች ንግስት እንዲያው በደፈና… ቆዳዬ ተገፎ ይሁንልሽ ጫማ ስጋዬም ይደገም ላንቺ ከተስማማ አጥንቴን ይብረደው እራቁቴን ልሂድ ካንቺስ የበለጠ አላገኝም ዘመድ … »ግድል የሚያደርጋትን ግጥም። … ይህንን ሲሰጡኝ ግን በሰዎች መሃል «እኔ ሳልሞት ዝፈኚልኝ፤ አደራ!» ብለው የአደራ መልዕክት ሰጥተውኛል። ይሁንና ግጥሙን ከዜማው ጋር ደስ ብሎኝ አንጎራጉረዋለሁ፤ ግን አልተቀረፀም። በተለያየ ምክንያት ሊሳካ አልቻለም።

ለአምስት ዓመታት እንደቆየ ለማስቀረፅ አቡነ ጴጥሮስ የሚገኘው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሬዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ተገኘሁ። ልክ ይህ ዘፈኔን እያስቀረፅኩ ባለበት ቅፅበት ሻምበል ኑሩ ሂልተን ሆቴል በር ላይ ወደቁ። ሲወድቁም በግንባታ ላይ የነበረው የሆቴሉ የውጪ አጥር ድንጋይ ፍንጣሪ የሆነች አንዲት ጠጠር ጭንቅላታቸውን ስለመታቻቸው እዚያው ሞቱ። … እኔ እየቀዳሁት። «ሳልሞት በፊት» እያሉኝ‐ ይህ ሆነ። የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው።

በዚህ ክስተት ለብዙ ጊዜ ሲቃ ይዞኝ ኖሬያለሁ። እድሜ ልኬን እየሰቀጠጠኝ ይኖራል። አሁንም ዘፈኑን ሳደምጠው ያ ስሜት ይመጣብኛል።

ታዛ ፦ ከዚህ በኋላ ካንተ ምን እንጠብቅ?

ዓለማየሁ ፦ አሁን አጓጉል ነገር እየተፈጠረ ነው ያለው እኮ። ድሮ በእኛ ጊዜ ያላመንበትን ነገር ለህዝብ አናቀርብም። ዛሬ አሰሱም ገሰሱም አልበም ይባላል። እኔ እዚያ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ጥራት ያለው ነገር አንድ ወይም ሁለት ነገር ብንሰራ ጥበብ ይጎለብት እንደሆን እንጂ፤ አይኮስስም። ቴክኖሎጂውም እንደጠቀመ ሁሉ፤ ጉዳት አለው።

ልፋትና ድካምን በነጻ ነው የሚወስደው። እግዚአብሔር ጤናዬን ይጠብቅልኝ እንጂ አሁንም ለአገሬ፣ ለወገኔ እጠቅምበታለሁ፣ አስተምርበታለሁ የምለውን ነገር አዘጋጅቼ አቀርባለሁ። ከአሁን ወዲህ በኮንሰርት መልክ ነው የማቀርበው። የተከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚረዳኝ እተማመናለሁ። አሁን ያለንበት አገራዊ ሁኔታ አስደሳች ነው። መጨረሻችንን ያሳምርልን እላለሁ። አመሰግናለሁ። አይበቃም?

ታዛ ፦ ይበቃል። እኔም በጣም አመሰግናለሁ። ቀሪ ዘመንህ የጤናና የስኬት እንዲሆን እመኛለሁ።

ዓለማየሁ ፦ አሜን፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top