Connect with us

ከጉና ሰማይ ስር

ከጉና ሰማይ ስር
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከጉና ሰማይ ስር

ከጉና ሰማይ ስር

የአሸባሪው ትሕነግ/ሕወሀት ወንበዴና ዘራፊ ቡድን ለሥልጣን ካለው ገደብ የለሽ ጥም የተነሳ ለሀገር ዘብ የቆመን፣ የሀገር ዋልታ የሆነን የመከላከያ ሠራዊታችንን አጥቅቷል:: በሰሜን ዕዝ የሠራዊት አባላት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም  “ሀገር አማን” ብለው በተኙበት ግድያ፣ አፈና እና ጭፍጨፋ ማካሄዱ ታላቅ ክህደት ነበር:: በመሆኑም መንግሥት ሀገርን ለማፍረስ በተዘጋጀው በዚህ ወንበዴ ቡድን አባላት ላይ ሕግ የማስከበር ዘመቻ አካሄደ::

“አራት ኪሎ እንገባለን” ብሎ ሥልጣነ መንበሩን ለመቆናጣጥ ሲመኝ የነበረው የትሕነግ አሸባሪ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይል ሚሊሻ እና ፋኖ፣ በአፋር ልዩ ኀይል… ያረፈበትን ብርቱ ክንድ መቋቋም አቅቶት በመጣበት እግሩ ተመልሶ ለመፈርጠጥ ተገደደ:: የወንበዴው ባለሥልጣናት አራት ኪሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንገባለን ብለው ቢመኙም በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈርጥጠው ተምቤን ዋሻ ውስጥ ለመግባት የቀደማቸው አልነበረም::

መሀል ሀገር ያስገባናል ብለው ሲኩራሩበት የነበረዉ ታጣቂ ኀይላቸውም በየሜዳዉ፣ በየተራራዉ፣ በየመንገዱ የአሞራ ራት ሆኖ ቀረ:: ከሞት የተረፈውም ቀበቶውን ፈትቶ፣ ትጥቁን በየጥሻዉ ሸጉጦ፣ ወታደራዊ ልብሱን አውልቆ አንድ አንዱም ቀሚስ ለብሶ እግሬ አውጭኝ ብሎ አውራዉ እንደጠፋበት ንብ ተበታትኖ ተጠፋፋ::

መንግሥትም በአሸናፊነት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ የአካባቢው አርሶ አደር እርሻውን እንዲያርስ፣ ሕዝቡም ሆነ የትሕነግ አሸባሪ ቡድን አባላት ውስጣቸውን እንዲያዳምጡ በሚል የጽሞና ጊዜ በመስጠት መከላከያው ከትግራይ እንዲወጣ አደረገ:: የአሸባሪዉ ቡድን አባላትና መሪዎች ግን ይህን የጽሞና ጊዜ እንደ ፍርሀት በመቁጠር ከተደበቁበት ዋሻ፣ ጥሻ፣ ጉድጓድና ሸለቆ… በመውጣት ድጋሜ ሀገርን ለማፍረስ ተሰባስበዉ በአማራ እና አፋር ላይ ወረራና ዘረፋ ማካሄድ ጀመሩ::

ከተንቤን ዋሻ ውስጥ መነሻውን ያደረገዉ ይህ አሸባሪ ቡድን ከደቡባዊ ትግራይ ተነስቶ በአማራ ክልል ኮረምን፣ አላማጣን ቀጥሎም የቆቦን ከተማ በመውረር ዘረፋና ውንብድናውን ዳግም ጀመረ:: መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የአማራ ሕዝብ “ምከረው፣ ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው” በማለት ቅድሚያ ትንኮሳውን እንዲያቆም እንደ ወንድም፣ እንደ እህት በመሆን “ተው!” ብሎ መከረ::

ሀገሪቱ ካልፈረሰች፣ መንግሥት ካልተወገደ፣ ወይ እኛ ካልገዛን ማንም ሰላም ማግኘት የለበትም በሚል እኩይ ባህርይ ተገፋፍቶ ወደ ተለያዩ ከተሞች ህፃናትን ለጦርነት አሰልፎ፣ በአደንዛዥ ዕፅ እያደነዘዘ ሴቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ በወረራዉ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ የለየለት የሀገር ጠላት መሆኑን፣ ለራሱ ሕዝብ እንኳን የማያስብና የማይጨነቅ መሆኑን በተግባር አስመሰከረ::

በኮረም እና አላማጣ የጀመረው ወረራ እስከ አራት ኪሎ አልጋ በአልጋ እንደሚሆንለት አስቦ ወረራውን እንዲሁም ዘረፋውን ማጧጧፍ ጀመረ:: 

የአራት ኪሎዉ ምኞቱ ባይሳካ እንኳን የወልቃይትን ምድር ዳግም በመውረር ከሱዳን ጋር መሿለኪያ በር ማግኘት የቋመጠበት ምኞቱ ነበር:: ኮረም፣ አላማጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ መርሳ፣ ላሊበላ… እያለ በዚህ ሳይወሰን በፕሮፖጋንዳም፣ በባንዳም እየታገዘ ወደ ደቡብ ጐንደር በመሻገር ጋይንትን፣ ክምር ድንጋይን አልፎ ጋሳይ ደረሰ::

እነዚህ የደቡብ ጐንደር የጉና ተራራዎች ለትሕነግ ትልቅ የራስ ምታት የነበሩ ቦታዎች ስለመሆናቸዉ ከእኛ በላይ ራሱ አሸባሪዉ ትሕነግ ያውቀዋል:: ከጉና ተራራ ስር ጥጥራ፣ ነጮ ሜዳ፣ ጎብጎብ፣ ክምር ድንጋይ… የትሕነግ ዘራፊና ወንበዴ ቡድን በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደ ቅጠል የረገፈባቸውና መፈጠሩን የጠላባቸው ቦታዎች ናቸው::

ይሁን እንጂ ትሕነግ ይህን የትናንቱን ታሪክ ረስቶ ዛሬም ወረራውን በጉና ተራራ ስር አድርጐ መስፋፋቱን ቀጠለበት:: በመሆኑም የአማራ ሕዝብ ከመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ ሊሠራ ከየቦታዉ እየተጠራራ ሆ! ብሎ በተባበረ ክንድ ሊያጠፋዉ በአንድነት ተነሳ፤ ጋሳይ ላይ ሲደርስም “ይበቃሀል” አለው:: ተመክሮ፣ ተለምኖ አልሰማ በማለቱ “ምከረው ምከረው፤ እምቢ ካለ መከራ ይምከረው” በማለት ጀግኖቻችን ወገባቸውን ጠበቅ አድርገዉ፣ መሳሪያቸውን ወልውለው ትናንት በተቀጠቀጠበት ቦታ ላይ ዳግም ሌላ ታሪክ እንዲሠራበት ወሰኑ::

ጀግኖቻችን ወንበዴው የጉና ተራራን አልፎ ወደ መሀል ሀገር እንደማይገባ ጠንቅቀዉ የተረዱ ይመስል ነበር:: ጋይንትን ከወረረ 10ኛ ቀኑን አስቆጥሯል:: ጋሳይንና ክምር ድንጋይን ከያዘ ደግሞ አራት ቀን ሆኖታል:: ጠላት ፍላጐቱ ወደ ፊት መሄድ ነበር:: 

የአማራ ሕዝብ፣ የአማራ የፀጥታ ኀይል፣ መከላከያ ሠራዊት ግን ከጋሳይ በኋላ አንድ ስንዝር መሬት መርገጥ እንደማይችል ያውቁታል::

ውጊያዉ የሚደረገዉ ከማይታወቅ አካል ወይም ቡድን ጋር አይደለም:: በተደጋጋሚ ሽንፈትን እና ውርደትን ከተከናነበው የትሕነግ አሸባሪ ቡድን ጋር ነው:: ይህ ደግሞ ለማንም የሚያስደነግጥ አልነበረም:: ከሚሳኤል እስከ ሮኬት፣ ከታንክ እስከ መድፍ፣ ከቢኤም እስከ ሞርታር አፍንጫዉ ድረስ ታጥቆ በነበረበት ጊዜ እንኳን ሊፈረጥጥ፣ ውርደትን ከሞት ጋር ሲጋተው ሳምንት አልፈጀበትም ነበር:: በመሆኑም ድሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ድሉ ለመከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ለአማራ የፀጥታ ኀይል እንደሚሆን ጥርጥር አልነበረውም::

ወደ መሀል ሀገር በቅዠትና በምኞት ለመገስገስ የቋመጠው ቡድን ጋሳይ ላይ ተጠራቅሟል:: የመከላከያ ሠራዊቱ ቦታውን በተገቢ መንገድ ይዟል:: መድፎች፣ ታንኮች፣ ቢኤሞች፣ ሞርታሮች አፈሙዛቸዉን ወደ ጋሳይ አዙረዉ ተቀምጠዋል:: የትሕነግ ወንበዴ ቡድን ጋሳይ ለመግባት አስራ አንድ ቀን ፈጅቶበታል::

የወገን ጦር ቦታውን ይዞ የመጨረሻዋ ፊሽካ እስክትነፋ እየጠበቀ ነበር:: እስከዚያው ግን ኳሷ እየነጠረች ነው፤ ወደ ጠላት ልትመታ:: ፊሽካው ተነፋ፤ ጠላት ደነገጠ፤ መግቢያ መውጫ አጣ:: ወደ መሀል ሀገር ለመግባት የቋመጠለት ምኞቱ በደጋማዉ የጉና ተራራ ስር ብን ብሎ ጠፋበት:: ይህን ጊዜ በፈጣሪ ባያምንም አንዳች ኀይል የሚያማርር ይመስላል፤ “ምን አድርጌ ነው ከጉና ተራራ ስር ሁሌ ውርደትን፣ ሁሌ ሽንፈትን የምታሸክመኝ” በማለት::

የትሕነግ አሸባሪ ቡድን ቅድመ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ትግል ላይ በነበረበት ጊዜ ከጉና ተራራ ስር ጥሎት፣ ቀብሮት የሄደውን ወገኑን ከኛ በላይ እሱ ያውቀዋልና እርግማኑ በተራራዉ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን አይቀርም:: “አንተ ተራራ፣ አንተ ጉና ሁሌም በአንተ እንደተዋረድን ነውና ቁመህ ቅር! ከአንተ ተራራ ስር ሁሌም ደሜ እንደፈሰሰ፣ ነፍሴ እንደጠፋ ነውና ከዚህ ቦታ አንዳች ኅይል ያጥፋህ!” ብሎ እንደሚረግመው ለመገመት ከሱ ጐን መቀመጥ አይጠይቅም::

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የቢ ኤም 21 ቁምቡላዎችን፣ ሞርተሮችን… እያስወነጨፈ ነው:: የጉና ሰማይ ከሰላሳ ዓመት በኋላ ሌላ የጥይት ናዳ ለማስተናገድ ተገዷል:: ከቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በነበራቸዉ የ17 ዓመታት የትግል ዘመን እንደ ቅጠል የረገፉት የትሕነግ ዘራፊ ቡድን አባላት ሳያንሱ ዛሬም ተረኞች እዚያው ቦታ ላይ ለመርገፍ ተገደዱ::

የጋሳይ ምድር በጠላት አስክሬን ተሸፈነ:: ደብረ ታቦር፣ ወረታ፣ ባሕር ዳር… በቅርብ ቀን እንደሚገባ ይቃዥ የነበረዉ የጁንታዉ ትርፍራፊ ተስፋው የተሟጠጠ ይመስላል:: ለዚህ ማሳያው ደግሞ ከፊት እንደ ማገዶ ሲቆሰቁሳቸዉ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች አንድ ስንዝር ወደ ፊት መራመድ ተስኗቸው ለምሽግ በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ መቀበር መጀመራቸው ነበር::

“በቆረጣ ውጊያ፣ በመልሶ ማጥቃት፣ በመከላከል የውጊያ ስልት የተካንኩ ነኝ!” እያለ ሲኩራራ የነበረዉ ተስፋፊው ቡድን አማራጩ አንድ ብቻ ነበር፤  ጓዙን፣ ትጥቁን እና አስክሬኑን… አዝረክርኮ ወደ መጣበት መመለስ:: በመሆኑም ለዘረፋና ለአስክሬን መጫኛ ከኋላ ያዘጋጃቸውን ተሽከርካሪዎች ፊታቸውን ወደ መጡበት እንዲያዞሩ አደረገ:: 

በቻለው መጠን በሲኖትራክ አስከሬኑን ጫነ፣ ያልቻለውን እንደተዝረከረከ አፈር እንኳን ሳያለብስ ወደመጣበት ፈረጠጠ::

በጉና ሰማይ አሁንም ቢ ኤም እና መድፍ ያጓራል:: የወገን የጦር ኀይል በከባድ መሣሪያ ጠላትን እየደመሠሠ ነው:: የከባድ መሣሪያ ድብደባውን መቋቋም የተሳነው አሸባሪዉ ቡድን መበታተን ጀመረ:: ግማሹ እየተደናገጠ መሣሪያውን በአዝመራው መሀል እየጣለ ወደ መጣበት እየሮጠ ነው:: አንዳንዱ ከመደንገጡ የተነሳ መሄጃዉ፣ መግቢያው፣ መውጫዉ… ጠፍቶበት ባገኘው ድንጋይና ዛፍ፣ ጉድጓድና ድልድይ ውስጥ መሸሸግ ይዟል:: አንዳንድ ከፍተኛ የወራሪው እና ዘራፊው ጦር መሪዎችም የደረሰባቸዉን ጥቃት መቋቋም አቅቷቸው ለመማረክ ተገደዱ::

ደቡብ ጐንደር ዞን ጋሳይ ለመግባት አስራ አንድ ቀን የፈጀባቸዉ የትሕነግ ዘራፊ ቡድን አባላት ወደመጡበት ለመመለስ አንድ ቀን አልፈጀባቸውም:: የጉና ሰማይ ከፍተኛ የከባድ ጦር መሣሪያ ጩኸት ወደ መካከለኛ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች ጩኸት ተቀይሮለታል:: በዚህም አንፃራዊ ፋታ አግኝቷል::

ሞርታር 85፣ ዲሽቃ፣ መትረየስ፣ ክላሽ… እንደተልባ እየተንጣጡበት ነው:: ጀግኖቻችን በከባድ መሣሪያ ድብደባ የፈረሰውን የጠላት ቡድን እያሳደዱ እየለበለቡት ነው:: እግሬ አውጭኝ ብሎ የሚፈረጥጠዉ የትሕነግ ዘራፊ ቡድን በየደረሰበት ሱቆችን፣ ሆቴሎችን፣ መኖሪያ ቤቶችን… እየዘረፈ ወደመጣበት እየሄደ ነው:: ከካልስ እስከ ቀሚስ፣ ከሽሮና በርበሬ እስከ ጨውና ዱቄት… ያገኘውን እየዘረፈና እየለቃቀመ ከጋሳይ በክምር ድንጋይ፣ በጥጥራ፣ በነጮ ሜዳ፣ በሳሊ፣ በጐብጐብ፣ በነፋስ መውጫ አድርጐ ሲመጣ አስራ አንድ ቀን የፈጀበትን መንገድ በአንድ ቀን ውጊያ ጨጨሆን ወርዶ ወደ ሰሜን ወሎ ደብረ ዘቢጥ እንዲፈረጥጥ ተገደደ::

በየመንገዱ ታንኩን፣ ዲሽቃውን፣ እያንጠባጠበ ሲፈረጥጥ ልምምድ ያደረገዉ ለውጊያ ሳይሆን ለታላቁ ሩጫ ውድድር ይመስል ነበር:: ደቡብ ጐንደርን ተገዶ፣ ተቀጥቅጦ፣ ሽንፈትን ቀምሶ ለቅቆ የወጣዉ አሸባሪው ቡድን ሌላ እሳት ይጠብቅዋል:: ከጋሸና እሳት ለብሶ እሳት ጐርሶ የሚጠብቀዉ የወገን ጦር አለ:: ከኋላውም እንደ ከብት የሚነዳዉ የወገን ጦር አለ:: ጠላት መሀል ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል:: መጨረሻውን በቀጣይ አብረን እናያለን::

ድል ለኢትዮጵያውያን!!

(ሱራፌል ስንታየሁ)

በኲር ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top