Connect with us

የነበረው እንዳልነበረ …

የነበረው እንዳልነበረ …
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የነበረው እንዳልነበረ …

የነበረው እንዳልነበረ …

(እስክንድር ከበደ -ድሬቲዩብ)

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ የ2019 የሰላም ኖቤል ሽልማት በሰጠበት ወቅት ሽልማቱን ካስገኙላቸው ምክንያቶች አንዱ  በኢትዮኤርትራ ግንኙነት ባመጡት ውጤት ነበር፡፡ በዚህ ውጤት ውስጥ የኤርትራው መሪ አንዱ ቢሆንም ነጥለው ሸለሙ፡፡ ይህ ሰላም ኖቤል ሽልማት የተሟላ አድርጎ ለመወሰድ የኢሳያስ አፈወርቂ መሸለም ነበረባቸው፡፡ 

የሽልማቱ ኮሚቴ  ተወካይ ንግግር ሲያደርጉ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ቀና ምላሽ ባይኖር  በሁለቱ ሀገራት ሰላም አይወርድም ቢሉም፤ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለምን የሰላም ሽልማቱን እንዳልተጋሩ አልተናገሩም፡፡ ይህን ፈተና ሁለቱ መሪዎች በብልህነት አልፈውታል፡፡ በተለይ ኢሳያስ የምእራባውያንን “ተንኮል“ ስለሚያውቁ አልገረማቸውም፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን አስተዋጽኦ በማበላለጥ ግንኙነቱን ማሻከር ኢላማቸው ከሸፈ፡፡

 አሜሪካ በትግራይ  ጦርነት  የተሳተፉ ኃይሎች ላይ ጫና ለመፍጠር ሌላ ሙከራ አደረጉ፡፡ አሜሪካ በኤርትራና በኢትዮጵያ እንዲሁም በህወሀት መሪዎች የጉዞ ክልከላ እንደምታደርግ ይፋ አድርጋ ነበር፡፡ የባለስልጣናቱን ስም ግን ሳትጠቅስ አለፈችው፡፡ አሁንም የሁለቱ ሀገራትን ትብብር ለመከፋፈል ያደረጉትን ሙከራ  መሪዎቹ በብልሀት አለፉት፡፡ 

የቀድሞ የአሜሪካ ባለስልጣን ሱዳን  በመምጣት  ሱዳን የቀድሞ የሀገሪቱን መሪ ኡመር አልበሽርን  በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አሳልፋ እንደምትሰጥ ወሬ እንዲናፈስ አደረጉ፡፡ አሁንም በኤርትራና በኢትዮጵያ መሪዎችን  የእናንተም እጣ እንዲህ ይሆናል የምትል ስወር ማስፈራሪያ ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡

አሁን ደግሞ የኤርትራ  መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር  ሹም ላይ የጣሉትን ማአቀብ ይፋ አደረጉ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ማእቀብ ያልጣሉበትን ምክንያት አልነገሩንም፡፡ የኤርትራው ኢታማዦር ሹም በአሜሪካ የባንክ ሂሳብ አላቸው መባሉ አስገራሚ ይሆናል፡፡ ኤርትራ ለሀያ አመታት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማእቀብ ተደርጎባት የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የተጣለባት ማእቀብ እንዲነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስመራ በሄዱበት ወቅት ከዛሬ ጀምሮ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ደርቤ እስራለሁ ባሉት መስረት የኤርትራን ማእቀብ ያስነሱት ባለፈው ሶስት አመታት ነበር፡፡

 እንዳውም ጁቡቲ በራስ ዱሜራ ደሴት ኤርትራ ይዛብኛለች ብላ ማእቀቡን ልታስተጓጉል ስትል የኢትዮጵያና የሶማሊያ ከፍተኛ ልኡካን ቡድን አቋሟን እንድታነሳ ማድረጋቸው አይረሳም፡፡ ስለዚህ የኤርትራ ባለስልጣናት በአሜሪካ ገንዘብና ንብረት አግደናል ማለት ፌዝ ይሆናል፡፡ የማእቀቡ ዋና አላማ የኤርትራና የኢትዮጵያ  ክፍተት በመፍጠር  ወታደራዊና የጸጥታ ትብብሮች እንዲዳከም መሆኑን መገመት አይከብድም፡፡  የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ ከወጣ በኋላ አቶ ጌታቸው ረዳ የኤርትራ ጦርን እንከተለዋለን ቢሉም አንድም ጊዜ ህዝቡን ዘርፏልና ሴቶችን ደፍሯል ያሉትን የኤርትራ ሰራዊት አንድም ሙከራ አላደረጉም፡፡ 

ይልቅስ ኤርትራን ለመበቀልና መልሰው ሊወጉት አልደፈሩም፡፡ ደፍሮናል..ጭፍጭፏል…ሴቶችን ደፍሯል የሚሉትን የኤርትራ ሰራዊት መበቀልም ሆነው መልሶ ማጥቃት አልሞከሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ አብሯቸው ከ20 አመት በላይ የኖረውና እራሱን መከላከል  የማይችል  ስደተኛ ተደጋጋሚ በቀሎችን ሲያደርሱ  ምእራባውያን  በተለሳለሰ መልኩ እየተናነቃቸው አውግዘዋል ፡፡

ጦሩ ከመቀሌ ከወጣ በኋላ ቡድኑ ለምእራባውያን ጠንካራ አቋም እንዳለው ለማሳየት በአማራና በአፋር ክልሎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽሞ ዜና ለመሆን ተግቷል፡፡ በዓለም ቅርስነት የምትታወቀውን  የላሊበላ  ከተማ በመቆጣጠር  አለምአቀፍ የዜና ሽፋን ለመሆን ሞክሯል፡፡ በሚሰጡት መግለጫ “ደምስሰናል“ የኢትዮጵያ መከላከያን አንኮታኩተናል የሚል የተጋነነ ምስል ለአለም በማሳየት ተገዳዳሪ ብሎም መንግስትን መጣል የሚችል ፤በአፍሪካ የጦርነት ባህሉና የመዋጋት አቅሙ ከፍተኛ የሆነ ልዩ ፍጡር መሆኑን  ዳግሞ ለማሳየት ሞከረ፡፡

 በፊትም የተሸነፍነው በኤርትራ እገዛ ነው የሚል መልእክት ጎልቶ እንዲወጣ ፤ ተራራ የሚያንቀጠቅጥ ብቸኛ መፍለቂያ መሆናቸውን  ስድብ በተቀላቀለበት  ሁኔታ ደጋግመው  ፎከሩ፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ የመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ኃይልን በፍቃደኝነት የሚቀላቀሉ ወጣቶች በብዛት ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች መግባታቸውን ቢያስፈራቸውም ፤ ከአቅማቸው በላይ ፉከራው በረታ፡፡ ጦርነቱን ሀገርአቀፍ ለማድረግ ከሸኔ ጋር መስማማታቸው፤ የሱዳን የኢትዮጵያ ድንበር ጥሰቶች ብሎም የምናውቀውና የማናውቀው ሴራ የበረታባት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በማሳጣት እንድትንበረከክ የማደረጉ ሴራ በርትቷል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚደርጉት ይፋም ሆነ ስውር  ትብብር ለሀገራቱ ህዝቦችና ሀገራት ህልውና ወሳኝ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቡድኑ በአማራና በአፋር  ለአሜሪካና ሸሪኮቿ  ማሳየት የፈለገውን የተጋነነ  ወታደራዊና ጀግንነት በፈለገው መጠን ማሳየት አልቻለም፡፡ 

ይልቁኑም  በመጠኑ  ቡድኑ ሀገሪቱን የሚያሸብርና የመረረ የበቀል ፍላጎቱን በተግባር ሚፈጽም ኃይል መሆኑን አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያ “ክተት“ በማለት አያሌ ወጣቶች ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች መትመማቸው   በተባበሩት መንግስታትድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር  ኢትዮጵያ “ “ሚኒሻ እያደራጀች“ ነው በሚል እንዳሳሰባቸው የገለጹ ቢመስሉም፤ ኢትዮጵያ  በመከላከያና  የልዩ ኃይሎች ነበርና አዳዲስ ሰልጣኞች የሀገር መከላከያ ኃይሎቿን በልኳና በታላቅነቷ መጠን እያደራጀች መሆኗን ቢያውቁም እውቅና ለመስጠት አልፈለጉም፡፡ 

አንድ ጊዜ  አሸንፌበታለሁ የሚሉት ስልት  ሁልጊዜ  አይሰራም፡፡ በ1980ዎቹ የነበሩ አለማዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች ዛሬ የሉም፡፡ የምእራባውያንና የምስራቁ ሀገራት አሰላለፍ ተለውጦ አሁን የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል፡፡ 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top