Connect with us

እስቲ ልዩነትን እናምጣ

እስቲ ልዩነትን እናምጣ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

እስቲ ልዩነትን እናምጣ

እስቲ ልዩነትን እናምጣ

(መኩሪያ መካሻ)

አሁን የደረስንበት የፖለቲካ ሁኔታ “በዝም አይነቅዝም” አባዜ የሚያስጉዘን አይደለም። ከተነጋገርንና ከተመካከርን የተሻለ ፖለቲካዊ ባህል ልናዳብር እንችላለን። ካልተነጋገርንና ከተኮራረፍን ግን ሁላችንም ተያይዘን ወደ መቀመቅ እንወርዳለን።

በኢትዮጵያዊነታቸው የማያምኑ ወገኖች ቢኖሩ እንኳ በጋራ ፖለቲካዊ ባህላችን አለማመን መብታቸው ነው። ብሔርተኛ ወገኖች የሆኑትም እንዲሁ። ሁሉም ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ይዘምር አንልም። ዳሩ ግን በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ የጋራ ፖለቲካችን ላይ እንወያይ ነው ቁምነገሩ። ምናልባትም እነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያ “የጋራ ነፍስ” የላትም ሊሉን ይችላሉ።

 የጋራ የሚያደርጋት ባህል የላትም ብለው አክ እንትፍ ሊሉንም ይችላሉ። ምንም አይደለም፤ ይከራከሩን። እኛ ግን መድረኩን እንፍጠርላቸው ነው ዋናው ጉዳይ።

እውነቱን እንነጋገርና ለመሆኑ ኢትዮጵያ የጋራ ነፍስ የላትም? እንዴት ነው ነገሩ? እንዴት ነው ኢትዮጵያን በጋራ ነጽሮት የምንመለከተው? ለዚህ መልስ የምናገኘው በጋራ ቆመን ስንወያይ ብቻ ነው። ከኋላቀር ፖለቲካዊ ባህል ተላቀን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሲቪል- ባህል ለመዝለቅ ብቸኛው መንገድ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መመካከር ነው። 

ከቆየው ወገኛና ነፍጣዊ አመለካከት ተላቀን ሰውኛ መንገድ መከተል ይኖርብናል። በሀሳብና በሀሳብ ብቻ ላይ የተመሠረተ ተቺ አርበኛ መሆን ያስፈልጋል። እንደዚያ ሲሆን ነው ሀገራችን የሁላችንንም ልብና ስሜት የምትገዛው። ከፖለቲካዊ ቀውስ ወጥተን ፖለቲካዊ ለውጥ ማምጣት የምንችለው። እስቲ ሁላችሁም ቆም ብላችሁ አንድ ጥያቄ ጠይቁ። ለመሆኑ ሲቪላዊ ፍቅርን (civic love) ለኢትዮጵያ ልናመጣ እንችላለን?

ዛሬ የምናያቸው የአውሮፓ ሀገራት ከሁለት ምዕተ-ዓመታት በፊት እንደዛሬዎቹ የአውሮፓ ሀገራት አልነበሩም። የተበጣጠሱ፣ በፖለቲካ ልሂቃን ፍላጎት አርቴፊሻል የወሰን ክልል የተሰጣቸው ነበሩ። እነ ቢስማርክ፣ እነ ጋሪባልዲ ስማቸው የገነነው ይህን ወሰን በመጣሳቸው አልነበረምን? የትናንቷን ኢትዮጵያም ከዚህ ለይተን መመልከት የለብንም። ወደፊት ልናያት ስለምንመኛት ኢትዮጵያ ስናስብ የሰከነ፣ ሁሉንም ዜጋ “ዜጋ” ያሰኘና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ የሀገር ፍቅር ኖሮን ፖለቲካዊ ባህላችንን ስናበለጽግ ነው የምንጠነክረው።

ወደ አውሮፓ እንመለስና ታሪኳን ስንቃኝ የምንደርስበት እውነታ አለ። እስከ ቅርቡ 1945 (እ.ኤ.አ) አውሮፓውያን በትርምስ፣ በጦርነትና በጡንቸኝነት ላይ ነበር የተመሠረቱት። ለዚህም ነው ቲምቲ ጋርተን አሽ የተሰኘ ጸሐፊ የዛሬዋን አውሮፓ ሲመዝን “በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተች ኤምፓየር” ሲል የጠራት። እኛስ ተመሳሳይ ሀገረ-መንግሥት አያስፈልገንም?

እጅግ ወሳኝ የሆኑ ለውጦች ወይም ንቅናቄዎች የሚጀምሩት ከሥር ወደ ላይ እንጂ ከላይ ወደ ታች አይደለም። ጆኒ ኔይስቢት እንደጻፈው “በባህልም ዘርፍ ሁኔታው እንደዚያ ነው። እውነተኛ የሆኑና አስፈላጊ የባህል ለውጦችም ከባለሥልጣናት ወይም ከዕውቅ ሰዎች ሳይሆን የሚጀምሩት ከተራው ሰው ነው። እያንዳንዱ ሰው ልዩነትን ለማምጣት ከፈለገ ዕርዳታውን የሚፈልጉትን በመርዳት ማሳዬት ይኖርበታል” ሲል አሳስቧል። እኛ የምንለው ልዩነትን እናምጣ ነው።

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top