“አልታገስም!!”
ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታ ተከትሎ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጥሩና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እንደማይታገስ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የኑሮ ውድነት መንስኤ በመለየት እልባት ለመስጠት ያለመ ውይይት ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በዌቢናር አካሂዷል።
በውይይቱ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአካባቢያቸውን ምርትና የአቅርቦት ሰንሰለት ያለበትን ሁኔታ የዳሰሰ ሪፖርት አቅርበዋል።
በዋናነትም በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ በየዕለቱ ለሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ መንስኤ ያሏቸውን ምክንያቶች አብራርተዋል።
ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን እንደ ምክንያት በማንሳት ምርት እያለ የመደበቅና ‘በችግሩ ምክንያት ማምጣት አልተቻለም’ የሚል ሰበብ በመፍጠር ሕዝቡን ለችግር የመዳረግ ስራ በህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች አሻጥር እየተፈጸመ እንደሆነ ተገልጿል።
በቅንጅታዊ አሰራር አለመጠናከር የተነሳ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ችግር ሊፈታ እንዳልቻለም ተነግሯል።
የኅብረት ስራ ኤጀንሲዎችና ዩኒየኖች ዋጋ የማረጋጋት ስራቸውን ወደ ጎን በመተው ትርፍ ለማካበት ምርት የመደበቅ ልምድ መስፋፋቱን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉም ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል።
ያልተናበበ የኬላዎች ቁጥጥር፣ በደረሰኝ የተረጋገጠ የንግድ ሥርዓትና ወጥነት ያለው የዋጋ ተመን አለመኖርም ለችግሩ ምክንያት እንደሆነ የቢሮ ሃላፊዎቹ ጠቅሰዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል “ለዋጋ ንረቱ የተጠቀሱት ምክንያቶች የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር በመንግስትና በሕዝቡ መካከል ያለውን መተማመን ጥላሸት ለመቀባት ያለመ ሴራ ነው” ብለውታል።
አገር ህልውናዋ ተደፍሮ ባለበት አስቸጋሪ ወቅት የሕዝቡን አብሮነትና ከመንግስት ጎን የመቆም ወኔን ለማደፍረስ ሲባል እዚህም እዚያም ያሉ የአሸባሪው ቡድን አባላት በኢኮኖሚ አሻጥር እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል ነው ያሉት።
በተለይም ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻውን ተገንዝቦ በኑሮ ውድነትም ሆነ በሌሎች መስኮች ያለውን ጫና ለመቋቋም ቁርጠኛ በሆነበት ወቅት ትዕግስቱን የሚፈታተን ተግባር መፈጠር የለበትም ብለዋል።
ለዚህም አመራሩና የዘርፉ ሙያተኞች ቁርጠኛ አቋም ኖሯቸው ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎችና ርዕስ መስተዳደሮች ጭምር ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል።
ሚኒስቴሩ አላስፈላጊ ትርፍ ለማግኘትም ሆነ የኦኮኖሚ አሻጥር አጀንዳውን ለማስፈጸም የሚሯሯጡ ስግብግብ ነጋዴዎች፣ ደላሎችና የኅብረት ስራ ዩኒየኖችን እንደማይታገስም አስታውቀዋል።
መጪው ጊዜ የበዓላት መሆኑን ተከትሎ መንግስት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በግዥ እያስገባ መሆኑን ጠቁመው፤ ስርጭቱ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በአገሪቷ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ከወቅታዊ ሁኔታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በአፋጣኝ የማሻሻያና የማስተካከያ ስራዎች እንዲከናወኑ መመሪያ ሰጥተዋል።
በሕገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግምና አስተማሪ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
(ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር )