ትናንት ዓለም ደግፏችኋል፤ ዛሬ ዓለም ዝም ብሏችኋል፤ ነገ ዓለም ይፈርድባችኋል፤ እየሆነ ያለውን የሰው ልጅ ሁሉ ያየዋልና!
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ትንናት ምን ፈልጎ እንደነበር ባናውቅም ብዙ ጉዳችሁንና ብዙ ገበናችሁን እያወቀ ዓለም ደግፏችኋል፡፡ የሰራችሁትን ድራማ አምኖም ይሁን ኢትዮጵያን ለመጉዳት ከእናንተ የተሻለ ጥሩ ምርጫ እንደማይኖር አውቆ ከጎናችሁ ቆሟል፡፡ በወታደሩ ላይ የፈጸማችሁትን እንዳላየ በማለፍ ወታደሩ ያላደረገውን በማስጮህ ንጹሃን ሆናችሁ እንድትታዪ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
ግድቡን ከግብ ማድረሳችን ያስቆጫቸውም ሆኑ ፖለቲካ~ ኢኮኖሚ አቋማችን ያበገናቸው አሰልፈዋችሁ ሲዖል ድረስ ወርደን ኢትዮጵያን እናጠፋለን ስትሉ አይባልም ያላችሁ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያላችሁን ቦታ ዓለም እያወቀ የትግራይን ህዝብ ጭምር አወናብዳችሁ ገደል ስትጨምሩት ከጎናችሁ ሆነ፡፡
ዛሬ ዓለም እናንተን መደገፍ ትቶ ዝምታን መርጧል፡፡ በትግራይ ነጻ መንግስት ነን ማረስም እርዳታ ማግኘትም አልቻልንም ስደተኛና ተፈናቃይ በዝቶብናል ያላችሁትን ሰምቶ ከጎናችሁ ቢቆም የማይካድራን በአጋምሳና በአፋር ደገማችሁት፡፡ ከአማራ ወራሪ ጋር ነው ጠባችን ብላችሁ የአፋር ንጹሃንንና ሴቶችን ስትገድሉ ዓለም አየ፤ ሊጥና ቡሃቃ ዘርፋችሁ ስትሮጡ ከዓለም አልተሰወረም፡፡ የንጹሃን ቤት በከባድ መሳሪያ ስትመቱም ቢሆን አለም የሆነውን እየተመለከተ ነው፡፡
ለዚህ ነው አሁን ያ ከጎናችሁ የነበረውና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ምቹ ናችሁ ብሎ በማሰብ ሲያግዛችሁ የነበረ ሁሉ ስልት አልባ ሆናችሁ ስታዋርዱት ዝም ያለው፡፡
የተወረረብን መሬት አለ በሚል ድራማ አዲስ አበባ መግባት እንፈልጋለንና ልንገባ ነው በሚል ህጻናትን በግዳጅና በእርዳታ እህል ቀለብ መያዣነት አስገድዳችሁ ለጦርነት ስትማግዱት የተመለከተው አለም አሁን ዝም ብሏል፡፡
ነገ ደግሞ ይሄ ሁሉ አደባባይ ይወጣል፡፡ የተደፈሩትን ሴቶች አለም ይመለከታቸዋል፡፡ በወሎ ህዝብ ላይ የደረሰውን ወረራ ዘረፋና ቂም አደባባይ ወጥቶ ተግባራችሁ ለአለም የሚታይበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡
በንጹሃን ቤት ላይ ከባድ መሳሪያ ተኩሶ መኖሪያ ቤቱ የተቀመጠን ዜጋ መግደል ምን ማለት እንደሆነ አለም ያውቃል፡፡ በአጋምሳ የተፈጸመውን ዘር ማጥፋት ሳይወድ በግድ እንዲሰማው ይደረጋል፡፡ በአፋር የተፈጸመው ዘግናኝ እልቂት የሰው ልጅ ጋር ሁሉ እንዲደርስ ሲደረግ ያኔ የደገፋችሁ ዝምታውን ሰብሮ ይኮንናችኋል፡፡
አለም የፈጸማችሁትን የሚያውቅበት ቀን ቀርቧል፡፡ ንጹሃንን በመግደል ለገባችሁበት የጦር ወንጀል የምትሰሩትን ድራማ የሚኮንንበት ጊዜ ቀርቧል፡፡ የፈራረሱትን ከተሞች እንሰራቸዋለን፡፡ የሞቱብንን እንቀብራለን፤ ወገናችን ባላችሁት የትግራይ ህዝብ ላይ ጭምር ያመጣችሁትን ፍዳና መከራ ታሪክ አንድ በአንድ እየቆጠረ ትውልድ እየተተካካ እንዲሰማው ይደረጋል፡፡
እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ ማብቂያና ማቆሚያው ጋር ደርሷል፡፡ የትግራይን ህዝብ ከወገኑ ለመነጠል የሄዳችሁበት የከፋ ርቀት እየተሳካ ይመስለኛል፡፡
የተደበቃችሁበት ዓለም ከጉያው አውጥቶ የሚጥላችሁ ቀንም እንዲሁ በእናንተው ተግባር ቀኑ ደርሷል፡፡ ዘርፋችሁናል፤ ገድላችሁናል፡፡ መንግስትም ነጻ አውጪም ሆናችሁ መዝረፍና መግደል ጸጋችሁ እንደሆነ አምነናል፡፡ ከዚህ በኋላ ስለእንናንተ የሚነገርም የምንሰማው የለም፡፡ በየቤታችን የገባ ግድያ ስርቆት ሌብነትና ውንብድናን አይተናል፡፡ ይሄንን ሁሉ እናልፈዋለን፡፡ እያለፍነውም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትስቃለች!!