“ቱርካችን… ወዳጅ ማለት ወዳጅ የጠፋ ዕለት አለሁ ማለት!”
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
እንግዲህ የቱርክ ስሟ “ቱርካችን” ነው፤ የእኛ ናታ፤ እኛ እኮ በሚዲያዎቻቸው ቱልቱላ ተታለን አውሮፓን እንደ ራሳችን አጋር ቆጥረን በየዘመናቱ ስንካድ የኖርን ህዝቦች ነን፡፡ ቢቢሲ ያወራው እውነት ነው በማለት ተጭበርብረን የነጻነት ትግሉን ሁሉ አሜሪካ ስትጠላው አብረን አሸባሪ እያልን የተጭበረበርን ነን፡፡
እውነት እንናገር ከተባለ በጥቅማችን የመጣው አሜሪካ ወይስ ኢራቅ፣ ግን ተታለናል፡፡ ከአድዋ ጦርነት የመሳሪያ ሽያጭ ጨምሮ በማይጨው ጦርነት እስከተፈረደብን ፍርደ ገምድል ውሳኔ ድረስ ተበዳዮች ነን፡፡
አሁን እንኳን እነሱ የዓለም ስጋት ያሉትን ለማጥፋት በማያገባቸው ሱማሌያ ድረስ ገብተው እና በስንዴ በማታለል ወያኔን ሰብዓዊ መብት አንልሽም አልሸባብን አጥፊ በሚል የኮንዶም ጦርነት ሲያውጁ እኛ ግን ሀገራችንን ለማዳን በሉዓላዊ ግዛታችን ህግ እንዳናስከብር ስንቱን መከራ አዘነቡት፤
አማራ ከያዛቸው መሬት ይውጣ የምትለው የዓለም ጉዷ አሜሪካ ላሊበላ ተያዘ ስትባል አማጺው በጥንቃቄ ይጠብቀው የሚል መግለጫ ስታወጣ እንደ ሀገር ከማን ጋር መቆም እንዳለብን ዘለዓለማዊ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡
አሁን ጠቅላዩ በቱርክ የቱርክን የእኛነት የሚያሳይ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ቱርክ ከዚህ በኋላ ቱርካችን ናት፡፡ በዚህ ዓለም ፊቱን ባዞረበት፤ ሁሉ ውድቀታችንን በተመኘበት ሰዓት ከኤርትራ ቀጥላ በአደባባይ ከጎናችን የቆመችው የዓለም ሀገር ቱርክ ናት፡፡ ቱርክ ቱርካችን፡፡
ወዳጃ ማለት ወዳጃ የጠፋ ቀን አለሁ ብሎ የሚታይ ነው፤ አንካራ አዲስ አበባን አለሁ ብላለች፡፡ እኛ በፍጋኒስታን የሆነውን ያየን ነን፡፡ ሶርያ የገጠማትን ሰምተን ሳይሆን መዲናችን በሶርያ ስደተኞች ተሞልተው የተመለከትን ነን፡፡ እናም የአሜሪካንን ድግስ እናውቀዋለን፡፡ ግን የቃል ኪዳን ሀገር ነን፤ በዓሊሞች ዱዓ፣ በአባቶች ምህላ ሁሉን አሸንፈን እዚህ የደረስን፡፡
ቱርካችን ባለውለታችን ናት፡፡ የኋላ ታሪኮቻችን ቢፈተሹ እንዲህ ባሉ ፈታኝ ሰዓት አለሁ ብላን ታውቃለች፡፡ ያን ታሪክ ዛሬ ደግማዋለች፡፡ ስልጣኔ ባህልና እምነት ካልተምታታባት ሀገር መወዳጀት ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ የራሷ ቀለም ያላት ነውርን የምትጠየፍ በማያገባት የማትገባ አውሮጳዊት ሀገር ወዳጅ አለችን ማለት ያኮራል፡፡ እናም በቱርካችን እንኮራለን፡፡
ይሄ እንደ ህዝብ በህዝብ ልብ የሚኖር የወዳጅነት ማኅተም ነው፡፡ ቱርክና ኢትዮጵያ ምንና ምን ናቸው ሲባል ለልጆቻችን የምንነገርው ውለታም ታሪክም ነው፡፡ ይሄ ጨለማ ቀን ሲያልፍ የብርሃናችን ምክንያቶች ከምንላቸው የወዳጅነት ግንኙነትም አንዱ ሆኖ ይኖራል፡፡
በዚህ ወቅት በአባይ ግድብና በውስጥ ችግራችን ፈተና ሲጋረጥብን እንዳላየም የቆጠሩን ሆነ ከሚጎዱን ወገን የተሰለፉት ነገ በነበራቸው አቋም የሚያፍሩበት ታሪክ እኛ ዘንድ አኑረዋል፡፡ ሃያላን የነበሩት እንደእኛ ያለ ሀገርን ለሃያል ጉዞአቸው የሚፈልጉበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡
በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ እንዲህ እንደ ወዳጅ ሀገር ቱርክ በየዘመናቱ ፈተናው ሲጠና ብቅ ብለው አለን ያሉን ብዙ ናቸው፡፡ ዛሬም ወዳጅ ነን፤ ሊያውም የወዳጅነት አደባባይ በስማቸው አቁመን፡፡ እንደ ኩባ፣ እንደ ራሺያ፣ እንደ ጎረቤት ሀገር ኤርትራ ቱርክም ከእኛ የተቆራኘ ታሪኳን ዳግም አተመች፤ ቱርካችን፡፡