ስግብግብ ነጋዴዎችን ከጁንታው ለይተን አናያቸውም!!
~ የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነትን ያላንዳች መንገራገጭ ለማስቀጠል ዘብ መቆማቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ሕዝብ አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ኦነግ-ሸኔ ግንባር ፈጥረው የወጠኑትን ሀገርን የማፍረስና እልቂትን የመፍጠር አጀንዳ በማምከን ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነትን ያላንዳች መንገራገጭ ለማስቀጠል ዘብ መቆማቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የውስጥና የውጭ ፈተና ለመታደግ እዘምታለሁ፤ የትም፤ መችም፤ በምንም የሚለዉን ሀገራዊ መሪ ቃል በተጨባጭ በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡
አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ኦነግ-ሸኔ ግንባር ፈጥረው የወጠኑትን ሀገርን የማፍረስና እልቂትን የመፍጠር አጀንዳ በማምከን ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነት ያላንዳች መንገራገጭ ለማስቀጠል ዘብ ቆመዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የሉዓላዊነታችን ጋሻና መከታ ለሆነው ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ደጀን ለመሆን ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከወጣት እስከ አዛውንት፤ አንድም ሳይቀር በኢትዮጵያዊነት የማሸነፍ ወኔ የተቃኘው የክልላችን ሕዝብ የተባበረ ክንድ በሚታይም ሆነ በስውር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሰፈሰፉ የውስጥና የውጭ ኅይሎችን አስደንግጧል፡፡
ሕዝቡ በገንዘብና በቁሳቁስ ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊታችንን ከመደገፍ አልፎ በተለይ ወጣቱ በአካል ሠራዊቱን በመቀላቀል እስከ ህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ያሳየው ጀግንነትና ቁረርጠኝነት ታሪክ የማይረሳው ነው፡
ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ጠንካራ ደጀን ለመሆን የተጀመረው እንቅስቃሴ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሀገርን ለመታደግ በተወጠነው መርኃግብር ጀግናው የክልላችን ሕዝብ በሁሉም የትግል አውድ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ከትንሹ ቁሳዊ አስተዋጽኦ እስከ ሕይወት መስዋእትነት ለመክፈል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ያለው ብቻ ሳይሆን የለውም ጭምር በሚችለው ሁሉ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፏል፡፡
በዚህ ፈታኝ ምዕራፍ ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉ-አቀፍ ርብርብ በምናደርግበት በዚህ ወቅት ሁኔታዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማይገባውን ሀብት ለማካበት የሚውተረተሩ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች እንዳሉ ተደርሶበታል፡፡
እነኚህ ራስ ወዳድና ለሕዝብና ሀገር ደንታ የሌላቸው ግለሰቦችን በኢትዮጵያ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተው ከአሸባሪው የሕወሓት ጁንታ ለይተን አናያቸውም፡፡ ስለሆነም፤ ያለ ዕውቀት ሀብት ለማካበት ብቻ በዚህ የሀገርና ህዝብ ክህደት ተግባር ውስጥ የተሳተፋችሁ ነጋዴዎች እጃችሁን በፍጥነት እንድትሰበስቡ መንግስት ያሳስባል፡፡ በአመለካከትና በድርጊት የባንዳነትና ተላላኪነት ተግባር ለመወጣት የንግዱን ሥርዓት ለማዛባት በዘመታችሁ ቡድኖች ላይ መንግሥት አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ይገልፃል፡፡
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቂት ግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲጋለጥ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የተሰጠውን ኅላፊነት በመዘንጋት የሕዝቡን መብትና ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ውስጥ ሲሳተፍ በተገኘ የመንግሥት የሥራ ኀላፊም ሆነ ባለሙያ ላይ መንግሥት የማያወላዳ እርምጃ እንደሚወስድ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፤ መችም፤ በምንም!
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ፤ 2013
ምንጭ፡- የኦሮሚያ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ