የካይሮ ረጃጅም እጆች ….
(እስክንድር ከበደ -ድሬቲዩብ)
” ህውሃትና ኦነግ በጋራ ይሰራሉ መባሉ አስፈግጎኛል፡፡” ስቴቨን ሳከር በቢቢሲ ሀርድ ቶክ ከጌታቸው ረዳ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ መጨረሻ የተናገረው ነበር፡፡ በመንግስት ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁት እነዚህ ቡድኖች አዲሱ ጥምረት ከመፍጠራቸው በፊት ዋነኛ ዘዋሪያቸው የውጭ ኃይል መሆኑናቸውን ያሳያል፡፡ ቀደም ሲባል የኦነግ/ሸኔ መሪ ጃል ማሮ ከህውሃት ጋር መስራት የማይታሰብ መሆኑን መናገሩ ይታወሳል፡፡
ይህ ቡድን በምእራቡ የሀገራችን ክፍል የኦነግ ወታደራዊ ክንፍ በመሆን የተፈጠረው ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ መሆኑን ማጤን ይጠይቃል፡፡ በምእራብ ኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም፣ በአማራ ማህበረሰብ ላይ በየጊዜው ግድያዎችና መፈናቀሎች በመፈጸም ለሚዲያ ፍጆታ ፎቶግራፎችና ቪዲዮ በመላክ አካባቢውን የሰቆቃ ቀጠና አድርጎት መክረሙ ይታወቃል፡፡ በአጣዬ፣በሻሸመኔ ወዘተ የፈጸማቸው ዘር ተኮር አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች ፖለቲካዊ ግባቸው የእርስበእርስ ጦርነት ለማቀጣጠል ፤አንዱን ህብረተሰብ በሌላው ላይ ማነሳሳት ነበር፡፡
የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በደረሰበት ወቅት ፤ሌተና ጀነራል ባጫ ደበሌ የሰጡት የመጀመሪያ መግለጫ ውስጥ የኦነግ ታጣቂዎች ወይም የኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ ተዋጊዎች እዙን በመውጋት ሂደት መሳተፋቸውን ጠቁመው ነበር፡፡ ይህ ሀሳብ ከዛች ጊዜ በኋላ አልተነሳም፡፡ እነዚህ ተዋጊዎች ከሰሜን እዝ የወጡ ወታደሮች ሳይሆን በትግራይ ምድር ህወሀትን እንዲያግዙ በውጭ ሀይሎች ድጋፍ ሰርገው እንዲገቡ ሳይደረጉ አይቀርም፡፡
በህወሀትና በኦነግ/ሸኔ በየፊናቸው በተናጥልና በጋራ ሀገር እንዲያፈርሱ የምትፈልግ ሀገር -ግብጽ ናት፡፡ ሸኔ መንግስትን ፋታ እንዲያሳጣ በህዳሴ ግድብ ቀጠና ፈጥራና ትጥቆችን በህገወጥ መንገድ በማስረግ( የጦርመሳሪዎቹን መንግስት የሰጣቸው ነው የሚል ወሬ በማስወራት ጭምር) በአማራና በኦሮሚያ አመራሮች መካከል መጠራጠር በመፍጠር በማህላቸው ክፍተት ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡
በምእራብ ኦሮሚያና በቤንሻጉል የተፈጠሩ ዘርተኮር ግድያዎችና የተፈጠሩ ጉልህ የጭፍጨፋ ሁነቶችን ተከትሎ ኦነግ/ሸኔ ሀላፊነት የወሰደበት ጊዜ አይታወቅም፡፡ ጋዜጠኞች በስልክ የሚደውሉላቸው ”ለታወቁ የአይን ምስክሮች ” ”ድረሱልን አምልጠን ከጫካ እየደወልን ነው” የሚሉ ይበዛሉ፡፡ እነዚህ ደዋዮች በአብዛኛው ጊዜ ለኢሳት ጋዜጠኛው ጎበዜ ሲሳይ ነበር፡፡ እንዳይነቃ የጋዜጠኛ መሳይና ወንድምአገኘሁ ስልኮች ይህው ”መረጃ” ይደርሳቸዋል፡፡ አሰቃቂ የፎቶግራፎችና ቪዲዮ ምስሎች ለማህበራዊ አንቂዎች በኢንቦክስ በመላክ ዜናው እንዲነኝ ያደርጋሉ፡፡
የሚያሳዝነው ዜጎቻችንን በግፍ ገድለውና አፈናቅለው በተደጋጋሚ ሲያሸብሩ መንግስትም የሚሰማው ከማህበራዊ ሚዲያና ወንጀል ፈጻሚዎቹ ” ድረሱልን ከሚሉ የአይን ምስክሮች ስልክ ጥሪ ነው” ይህን በተመለከተ አንድ የውጭ ሚዲያ ሪፖርተር ጠይቄ እንደነገረኝ በስልክ ውስጥ የተኩስና የጩኸት ድሞጾች በቀጥታ እያሰሙ ”መረጃዎቹን” ይሰጣሉ፡፡ በየጊዜው ከሚዲያ የሚነገሩትን የ”ጭፍጨፋዎች” ቁጥሮች ፤ የክልሉ መንግስት የተባለውን ያህል ቁጥር አይደለም ብሎ አሳንሶ በመናገር ፤የሸኔ ቡድን አባላት ተደመሰሱ ወይም ተያዙ አልያም ክትትል እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱ ይረሳል፡፡ በሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ጥቃት ይደርሳል፡፡ አንድም ጊዜ ኦነግ/ሸኔ እርምጃውን የወሰድኩት ይህንን የፖለቲካ አላማ ለማሳካት ነው ብሎ አያውቅም፡፡ መሪው ተጠይቆ ሲመልስ የራሱ ቡድን ሳይሆን ፤ የመንግስት ኃይሎች እጅ እንዳለበት በመጠቆም ማብራሪያ በመስጠት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት አመራሮች መካከል ያለውን አንድነት የሚላሉ ብሎም በሁለቱ ህዝቦች ዙሪያ መቃቃርን የሚያሰፉ ብሎም አንዱ በአንዱ ላይ በቀልን ለመጋበዝ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡
ቡድኑ በሚፈጽማቸው ጥቃትና ጉዳቶች በመገናኛ ብዙሃን ሪፖርቱን አስቀርቦ ፤ከግብጽ ያልተቋረጠ ድጋፍ ያገኛል፡፡ በየጊዜው በሚፈጽማቸው ጥቃቶች መንግስት ” የህወሃት ተላላኪ ” መሆኑን በመገናኛ ብዙን መግለጫ በመስጠት የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለፍትህ እንደሚያቀርባቸው በመዛት ጉዳዩ ይረሳል፡፡ በነገራችን መንግስት በፓርላማ ያመናቸው 113 ዋና ዋና ግጭቶች እያንዳንዱን በጥልቀት መርምሮ እና ሁሉንም የሚያስተሳስራቸው ምን እንደሆኑ አጣርቶ ይፋ አላደረገም፡፡ እንኳን በጅምላ ቀርቶ የአንድ ሰው ግድያ ወንጀልን በጥልቀት ዶሴ ፖሊሲ አጥርቶ ለፍትህ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
የህወሀትና ኦነግ/ሸኔ ፓርላማው ሽብርተኛ ብሎ ሲሰይማቸው የፈጸሙትን አሰቃቂ ወንጀሎች በዝርዝር ሚዛን ላይ አስቀምጦ ሳይሆን፤በጥቅል መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሽግግር መንግስት ወቅት ኦነግ ከህዝብ ተወካዮች ከመውጣቱ በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በ”በደኖ ጭፍጨፋ” ያደረጉት ወይይት ተላልፎ ነበር፡፡ በዛ ስብሰባ አቶ ስዬ አብረሃ ” ግድያው የተፈጸመው እንዴት አሰቃቂ እንደሆነ በተናገሩበት ወቅት ፤ሌንጮ ለታና ዲማ ነጎዎ ማስተባበል አልቻሉም፡፡
ለነገሩ በዛ ወቀት በምክርቤት ውስጥ ኦነግ 12 መቀመጫ እና እስላማዊ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ጃራ) ደግሞ 3 መቀመጫ ነበራቸው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ልዬነቶች እርስበእርስ ውጥረት የነበራቸው በመሆኑ፤ታጣቂዎቻቸው ካምፕ እንዲገቡ ለማድረግ በተደረገ ፍጥጫ የተወሰኑ መሪዎች ተገድለዋል ፤ሌሎቹም ወደ ጫካና ውጭ ሀገር እንዲሰደዱ ሆነ፡፡
ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ መውጣቱን ተከትሎ ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ኦፒዲኦ የአሮሞን ጥቄዎችን ለመመለስ የተቋቋመ መሆኑ እየተነገረ ቢመጣም፤ ኦፒዲኦ በሁለት ወገን የሚጠረጠር ከመሆን አልዳነም፡፡ በህወሀት በኩል ድርጅቱ ሲፋቅ ኦነግ እንደሆነ በግንባሩ ሊቀመንበር ሲነገር፤በኦነግ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ጥቄዎችን ለማዳፈን የተጠፈጠፈ ቅጥያ እንደሆነ ሲወቀስ ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያት አያሌ የኦሮሞ በሔር ተወላጆች ለእስርና እንግልት ሲዳረጉ ፤ በስርአቱ የከፋ ድርጊቶች ላይ ወጣቱ እንዲነሳሳና በህዝባዊ እምቢተኝነት ለውጥ እንዲመጣ ሆነ፡፡
በኢህዴግ መፍረስ ዋዜማ ድርጅቱን የመመሩት ኦህዴድን ወደ ኦዴፓ የለወጡ ይህም ፤ ሌሎችን የኦሮሞ ድርጅቶችን ወደ ለማቀፍ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ብአዴንም ወደ አዴፓ ስሙን ለወጠ፡፡ ስምና አርማቸውን የለወጡት ሁለቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች አካሄድ ያላማረው ህወሀት፤ ፕሮግራም እንጂ በስያሜ የሚመጣ ለውጥ የለም ብሎ አጣጣለው፡፡ የኦዴፓ ኦህዴድና ሌሎች ተቃዋሚ የኦሮሞ ድርጅቶችን ያሰባስባል ተብሎ ሲጠበቅ ፤ የብልጽግና ፓርቲ መፈጠር ከህወሀትና ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች በግልጸም ሆነ በተዘዋዋሪ ተቃውሞ መበርታቱ አልቀረም፡፡ በአዴፓ በኩል የአብን መፈጠርና የኢዜማ ፓርቲ መመስረት ውጥረት ውስጥ እንደከተተው ፤ ብዙም ሳይቆይ ብልጽግና ተፈጥሮ ገላገለው፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ውጥረት መሪዎቹ እንደገደሉና ከአብን የተወሰኑ መሪዎች እንዲታሰሩ ተዳረገ፡፡
ከአስመራ በድርድር ከገቡት መካከል የኦነግ 1ሺህ በላይ ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ሳይዙ በመቀሌ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል መግባታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ፡፡ ከወራት በኋላ የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው የተባሉ በምእራብ ኦሮሚያ ምልመላ እያካሄዱና ስልጠና እየሰጡ ቁጥራቸው መበራከቱ ይሰማ ጀመር፡፡ በሰላማዊ መንገድ የገቡ ታጣቂዎችን ክልሉ ማቋቋሙ ቢሰማም ፤ በክልሉ ከዚህ በፊት ሲንቀሳቀስ የልተሰማ አማጺ ቡድን ባንክ ዘረፋና በሰለማዊ ዜጎች ላይ ጥቃቶች እየከፈተ መሆኑ እየተነገረ መምጣቱ ግርታ መፍጠሩ አልቀረም ፡፡
ኦነግ/ሸኔ ሚለው ስም እየገነነ መጣ፤ በመዲናዋ አዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ግጭት በመፍጠር ብሎ በምእራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ጭፍጨፋዎች እየበዙ መጡ፡፡ የኦሮሚያ ክልል በመደበኛ ፖሊስ ሰላም ማስከበር እየተሳነው በመምጣቱ ልዩ ኃይል በገፍ በማሰልጠን ለመከላከል ጥረት ማድረጉ አልቀረም፡፡እስከዚህ ድረስ ይህ ቡድን ሽብርተኛ ተብሎ የፈረጀው አልነበረም፡፡ እንዴት እንደተፈጠረ ጥልቅ ምርመራ አልተደረገም፡፡
ኦነግ ለአርባ አመታት በዚህ መልኩ መንግስትን ሲያስጨንቅ ባልታየበት ፤ ኦነግ መሪ ዳውድ ኢብሳ በትጥቅ ትግል መንግስትን ለመጣል የጦር መሳሪያዎች እጦት እንዳገዳቸው በኤልቲቪ በተናገሩበት ሰሞን ያልታወቀ ሀይል መፈጠሩ ለምን የሚል አላገኘም፡፡ ከጀርባው ያለችው ግብጽ ብትሆንም፤ መንግስትም ደፍሮ ለመናገር የረቀቀ ድጋፏንና የግንኙነት መስመሩን አጥንቶ መበጣጠስ አልሞከረም፡፡
የህወሀትና የኦነግ ታሪካዊ ግንኙነት መተማመን አያሳይም፡፡ አሁን ግን በጋራ መንግስትን ለመጣል በድንገት ተስማምተዋል፡፡ መንግስት የሁለቱ ያልተቀደሰ ጋብቻ ድሮም ብዬ ነበር ቢልም ፤ቡድኖቹ በፍጥነት አብረው ለመስራት ጥልቅ ወይይት ሳያደርጉ በፍጥነት መግባባታቸው የሚያሳየው አንድ ሚስጥር ይኖራል፡፡ ሁለቱንም በተናጥል የምትረዳው ግብጽ ፤ ኢትዮጵያን ማፈረስ የሚቻለው ሁለቱን ማቀናጀት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳቷ ይሆናል፡፡ ድሮም አንድ ይሁኑ ተነጣጥለው ይስሩ ዋነኛ ግብ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ በመጣል የህዳሴውን ግድብ ማስቆም ነው፡፡
ለዚህም ነው አቶ ጌታቸው ረዳ ”እኛ የምንጠብቀው ፕሮጀክት የለም—-የህዳሴው ግድብ ቀፎ ሆኖ ቢድን ችግር የለብኝም ” በማለት ለግብጽ በገደምዳሜ እየሰራንልሽ ነው የሚል መልእክት የሰጣት፡፡ ያምሆነይህ ከሁለት ባላንጣ ሀገራት ስውር ድጋፍ እና ሁለት በሽብር የተፈረጁ አደገኛ ቡድኖች ሀገራችን በመወጠሯ የዛኑ ያህል የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የተከፈቱት የውጊያና የፕሮፖጋንዳ ጦርነቶችን የሚመጥን ዝግጅት በማድረግ መመከት ብሎም ስጋቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የሚሆነው፡፡
ቡድኖቹ ልዩነታቸውን በፍጥነት ወደጎን በመተው ኢትዮጵያን ለመውጋትና የተነሱበትን የፊት ለፊት ምክንያታቸው ይልቅ የጀርባ አላማውን በማጥናት ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የካይሮ እጆች ምንያህል ረጃጅም መሆናቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡