የአዲስ አበባ ካቢኔ የመሬት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጀ
~ ለ አራት መቶ ኩባንያዎች ጥሪ ቀረበ
(ውድነህ ዘነበ)
አዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማናጅመንት ቢሮ ማክሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ግንባታ ለማካሄድ የመሬት ጥያቄ አቅርበው የመጀመርያውን ዙር መስፈርት ያሟሉ 400 ኩባንያዎችን ይፋ አደረገ። ቢሮው የመጀመርያውን ዙር መስፈርት አሟልታችኋል ያላቸውን ኩባንያዎች ተጠባቂውን እና እውነተኛ አልሚዎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ በሁለት ቀን ውስጥ እንዲያቀርቡ አዟል።
ከ 400 ዎቹ ኩባንያዎች የሚበዙት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፣ ሞል ፣ አፓርትመንት እና ሪልስቴት ለመገንባት ጥያቄ አቅርበዋል። የተወሰኑት ደግሞ ዩንቨርስቲዎችን፣ ፋብሪካዎችን እና የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ህንጻዎችን ለመገንባት ጥያቄ አቅርበዋል።
ጥያቄ ካቀረቡ ኩባንያዎች መካከል በርካታ አዳዲስ የንግድ ድርጅቶች ይገኙበታል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ አርቲስቶችም የመሬት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ዘለቀ ገሠሠ 3.5 ሄክታር ፣ ታደለ ሮባ አንድ ሄክታር፣ ታደለ ገመቹ ሦስት ሽህ ካሬ ሜትር፣ ምነው ሸዋ ኢንተርቴመንት 1.5 ሄክታር መሬት ጠይቀዎል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሜዳልያ ለሚያመጡ አትሌቶች የመሬት ሽልማት ካቆመ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በርካታ አትሌቶች የመሬት ጥያቄ አቅርበዎል። ከነዚህ ውስጥ አሰለፈች መርጋ አንድ ሄክታር፣እጅጋየሁ ዲባባ አንድ ሄክታር፣ ማርቆስ ገነቴ አንድ ሄክታር፣ገንዘቤ ዲባባ አንድ ሄክታር፣ አሰፋ መዝገቡ ስድስት ሽህ ካሬ ሜትር፣ መሠለች መልካሙ ስድስት ሽህ ካሬ ሜትር ፣ እልፍነሽ ዓለሙ አንድ ሄክታር፣ ጥሩነሽ ዲባባ አምስት ሽህ ካሬ ሜትር፣ ብርሃኔ ዓለሙ አምስት ሽህ ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጣቸው ጠይቀዎል።
ኢንቨስተሮች ፣ ነጋዴዎች፣ አርቲስቶች እና አትሌቶች መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡት ከ 2009 ዓ.ም እስከ 2013 ዓም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን ያቀረቡት አቅም ማሳያ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ብር እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር ድረስ ነው።
ፈታኙ እና ብዙዎቹን ጥያቄ አቅራቢዎች ይፈትናል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህን ገነዘብ 30 በመቶ በባንክ የተቀመጠ መሆኑ እና የአንድ አመት የኦዲት ሪፖርት ሰነድ የማቅረቡ ጉዳይ ነው። ከዚህም በዘለለ ወቅቱ ስራ የተቀዛቀዘበት እንደመሆኑ የአንድ ዓመት ገቢና ወጭ ሰነድ የማቅረብ ጉዳይ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የመንግስትን ግብር በአግባቡ መከፈሉን እንዲሁም አልሚው የታክስ እዳ እንደሌለበት የሚያሳይ ማስረጃ ፣ የውጭ ባለሃብት ከሆነ ደግሞ 30 ሚሊዮን ዶላር ፣ ዳያስፖራ ከሆነ ደግሞ 7.7 ሚሊዮን ዶለር እንዳለው የባንክ እስቴትመንት ማቅረብ የሚችል መሆን እንደሚኖርበት ሁለተኛው መስፈርት ያዛል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመሬት ጥያቄ ያቀረቡት ከሦስት ሽህ በለይ ባላሃቡቶች ቢሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሁለተኛው መስፈርት የተሸጋገሩት አራት መቶ አለሚዎች ብቻ ናቸው።
በመጨረሻ የመሬት ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ባለሙያዎቹ ምክንያታቸውን ሲገልፁ የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟለት አቅም ያለው ኩባንያ ቁጥር አነስተኛ ነው። ያም ሆኖ ምክትል ከንቲባ አዳነች በሁለተኛው ዙር የስልጣን ዘመናቸው የሚያሳልፉት ፈታኝ ውሳኔ እንደሚሆን ከወዲሁ በመሬት ስሪት ባለሙያዎች ታምኖበታል።
በዚህ ደረጃ ብዛት ያላቸው ኩባንያዎች የመሬት ጥያቄያቸው እየተስተናገደ ቢሆንም፣ በመስተንግዶ ውስጥ ማለፍ አልቻልንም ያሉ ኩባንያዎች ቅሬታ እንዳላቸው እየገለጹ ነው።