Connect with us

አሸባሪው ህወሓት በራያ ግንባር በሶስት አቅጣጫ የላካቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአማራ ክልል አስታወቀ

Ethiopian news agency

ዜና

አሸባሪው ህወሓት በራያ ግንባር በሶስት አቅጣጫ የላካቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአማራ ክልል አስታወቀ

አሸባሪው ህወሓት በራያ ግንባር በሶስት አቅጣጫ የላካቸው ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰዱን የአማራ ክልል አስታወቀ

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በራያ ግንባር በሶስት አቅጣጫዎች በላካቸው ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰዱን የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አስታውቀዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ እንደ ማዕበል ገፍቶ የደፋቸው የጥፋት መልእክተኞቹ በአማራ ልዩ ኃይል፤ ሚሊሻ፣ በብሔር ብሔረሰቦች ጥምር ኃይል እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት በኩል በተሠጣቸው አጸፋ በወጡበት ለመቅረት እንደተገደዱ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ አባላት ላይ በተወሰደው ራስን የመከላከል እርምጃ አሸባሪው ትህነግ ታጣቂዎቹን እንደማዕበል በማትመም ወረራ ለመፈፀም የሚጠቀምበትን የሰው ኃይል እንዲያጣ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ብጥስጣሽ ቁጥር ያላቸውን ቡድኖች በማዋቀር በተበታተነ መልኩ ሽብር የመፍጠር ሥልትን መከተል ጀምሯል ብለዋል፡፡

ተስፋ የቆረጠው የሽብር ቡድኑ በትላንትናው እለት በወልዲያ ከተማ ሠላማዊ ሕዝብ ላይ በሠነዘረው የመድፍ ጥቃት ለግዜው ቁጥራቸው ባልታወቁ ንጹሃን ላይ የህይወት እና የአካል ጉዳት ማድረሱንም አቶ ግዛቸው አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በዚሁ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል።

***************************

ማንኛውም የረጋ የውኃ አካል ቀድሞ ከነበረበት ሥፍራ ወደ አልነበረበት ሥፍራ ተገፍቶ ለመውጣት ማእበል መሆን የግድ ይለዋል፡፡ ማእበል ለመሆን ደግሞ ከውኃው ውስጣዊ ወይም ውጫዊ አካል የሚነሳ የእሳተ ገሞራ አሊያም የአውሎ ንፋስ ግፊት ያስፈልገዋል፡፡

በውስጣዊም ይሁን በውጫዊ አካል ግፊት የተነሳ የውኃ ማእበል ተረጋግቶ የነበረበትን ስፍራ ለቆ መንጎድ፤ ነጉዶም በደረሰበት ቦታ ላይ ተደፍቶ የመቅረት እንጂ ወደተነሳበት የመመለስ እድል የለውም፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ገፍቶ የላከው ታጣቂም ፍጻሜው በነፋስ ተገፍቶ እንደተነሳ የውኃ ማእበል ሁኗል፡፡ ለሽብር ቡድኑ የከሰረ ፍላጎት ተገፍተው የወጡት ሁሉ በወጡበት መቅረት እንጂ ተመልሶ የመሄድ እድል አላገኙም፡፡

ህልውናችንን በመጻረር ከፊታችን የተጋረጠው አብዛኛው ማእበል ክምር በጋራ ክንዳችን ብርቱ ምት መክኗል፤ አሁን የቀረ ማእበል አለ ከተባለም የቀረው የስኒ ላይ ማእበል ሊባል የሚችለው ብቻ ነው፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በራያ ግንባር በሶስት አቅጣጫዎች እንደ ማዕበል ገፍቶ የደፋቸው የጥፋት መልእክተኞች በአማራ ልዩ ኃይል፤ ሚሊሻ፣ በብሔር ብሔረሰቦች ጥምር ኃይል እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት በኩል በተሠጣቸው አጸፋ በወጡበት ቀርተዋል፡፡

በተወሰደባቸው ራስን የመከላከል እርምጃ ትህነግ እንደማዕበል በማትመም የአማራ ክልልን ለመውረር የሚጠቀምበት የሰው ኃይል እንዲያጣ ተገዷል፡፡ በዚህም ምክንያት ብጥስጣሽ ቁጥር ያላቸውን ቡድኖችን በማዋቀር በተበታተነ መልኩ ሽብር የመፍጠር ሥልትን መከተል ጀምሯል፡፡

በተበጣጠሰ አደረጃጀት ተበታትነው በስሪንቃ እና አካባቢው የተወሸቁት የሽብር እንደራሴዎች በወገን ኃይል ተከቦ ተገቢው እርማት እየተሠጣቸው ይገኛል፡፡

አሸባሪው ትህነግ በአዲስ አውሎ ነፋስ ከመሃል የትግራይ ከተሞች አዲስ ቀልጦ ቀር የታጣቂ ማእበል ለማስነሳት የሚያደርገው ጥረትም በተለያዩ ግባሮች ባሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየመከነ ይገኛል፡፡

በዚህ አቅሙ የወገን ኃይልን መቋቋም ሥለተሳነውም በትላንትናው እለት በወልዲያ ከተማ ሠላማዊ ሕዝብ ላይ በሠነዘረው የመድፍ ጥቃት ለግዜው ቁጥራቸው ባልታወቁ ንጹሃን ላይ የህይወት እና የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡ በሰላማዊ ዜጎች የመኖሪያ ቤቶችና ንብረቶች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ልባዊ ሀዘን እንገልጻለን፡፡

ሊያወድመን ተገፍቶ የመጣን የጥፋት ማእበል ባገኘንበት ስፍራ ሁሉ እንዳይመለስ አድርገን ከማስቀረት ውጭ ሌላ አማራጭ የሌለን መሆኑን በመገንዘብ መላው የአማራ ህዝብ በያለንበት ቦታ ላይ ህልውናውን የማስጠበቅ ተጋድሎውን አጠናክሮ ሊያሰቀጥል ይገባል፤ ግድ ይላልም፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከትግራይ ክልል ተጨማሪ ማዕበል እየገፋ ወደ ክልላችን በመላክ የእኛን ሙሉ ጊዜ፤ የሰው ኃይልና ሀብት የታጣቂ ማእበል በመቅበር ሥራ ላይ ብቻ ተጠምደን እንድንኖር ለማድረግ የሚሞክረውን ጥረትም ከስር ከስር ለመቅጨት መረባረብ የኃይላችንና የመላው ህዝባችን ተግባር እንዲሆን እናሳስባለን፡፡

ሥለሆነም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ በህልውናችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ በአጭሩ ለመቅጨት ከእንግዲህ ዋናው ኢላማችን ሊሆን የሚገባው ተግፍቶ የመጣብንን ቀልጦ ቀር ማእበል መቅበር ብቻ ሳይሆን ለማእበሉ መነሻ ምክንያት የሆነውን አውሎ ንፋስ ከመነሻው የማጨንገፍ ትግልም ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም አውሎ ንፋሱ ከሌለ ማእበል ብሎ ነገር የለምና፡፡

ስለሆነም ውድ የክልላችን ነዋሪዎች፣ በአውደ ውጊያው ያላችሁ ታሪካዊ ጀግኖቻችን፣ የክልላችን የፖለቲካ ሊህቃን፣ ምሑራን፣ የማህበራዊ አንቂዎች፣ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ሰራተኞች፣ መላው የክልላችን ወጣቶችና የኃይማኖት መሪዎች የጀመርነው ጦርነት አማራንና መላውን ኢትዮጵያዊያንን ለመበታተንና እድል ካገኘ እርስ በራሳችን እያባላ ስልቱን እየቀያየረ በሁሉም አከባቢዎች ጦርነትና እሳት እየለኮሰ እረፍት ከመንሳቱም ባሻገር ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ጭምር በመወገን እንደለመደው ታሪካችንን ማበላሸት፣ ስነልቦናችንን ዝቅ ማድረግ፣ ቅርሶቻችንን፣ በወንድማማችነት አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን፣ በአጠቃላይ ሰባዊ፣ ቁሳዊ፣ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ትውፊቶቻችንን የመዝረፍ፣ የማቆሸሽ አላማን አንግቦ በግላጭ እስከ ሲዖል ሊፋለመን ቆርጦ የተነሳ ያለማችን ቀንደኛ አሸባሪ ጋር መሆኑን ተገንዝበን ለእያንዳንዳችን የተሰጠንን ተልዕኮ ከልብ በመተግበር ህልውናችንን መታደግ ግዴታችን መሆኑን ከልብ ልንገነዘብ ይገባናል። ምርጫችን ሁለት መሆኑ ግልፅ እየሆነ መጥቷል።

ይሄውም የመጀመሪያው አማራጭ የመጣብንን አደጋ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለን በጋራ ከፍለንና ተፋልመን ህልውናችንን ማስቀጠል፣ ታሪካችንን ከፍ ማድረግ፣ ትክክለኛ ዴሞክራሲና ሰላም የተረጋገጠበት ክልልና አገር መገንባት።

ሁለተኛው አማራጭ ህልውናችን አደጋ ውስጥ የሚገባበት፣ የጠላት አላማ ተሳክቶ በዓለማችን በሴራ እንደተበታቱኑን ጥቂት አገራት ለአብነትም እንደ ሶሪያ፣የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቪያ እንደመሳሰሉት ሀገራትና ሕዝቦች የምንበታተንበት፤ አሳፋሪ ታሪክ የምንከናነብበት፤ በዓለም አደባባይ የምንኮራበት ታሪካችንን የምናጠለሽበት፣ ሰይጣናዊ የጠላት አማራጭን መከተል ነው።

መቼም ቢሆን ጀግናው ሕዝባችንና ታጋዮቻችንን ምርጫችን የመጀመሪያው መሆኑ አያጠራጥርም። እናም የመጀመሪው ምርጫችንን አሳክተን በዓለም አደባባይ ኩሩ ሕዝቦች ለመሆን በስህተት የበቀለውን የአሸባሪውን የህውሓት አረምና የሕዝባችን የጋራ ጠላትና ካንሰር በተባበረ ክንድ በአንድነት ነቅሎ መጣል የግድ ይለናል። ደግሞም ይሆናል።

ድል ለጀግኖቻችን!!!

Ethiopian news agency

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top