ጻድቃን ገብረትንሳዔ አዲሱ የወያኔ ፊት! ከቢቢሲው ጁሊያን ማርሻል ጋር (ኦሃድ ቤንዓሚ)
በቅርቡ ጻድቃን ከቢቢሲ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አደመጥኩት፤ እናም የወያኔ ነገር አልኩኝ፤ ራስ ምታትም ያዘኝ፤ ለእምነት የማይበቃው ድርጅት በስተርጅናው ስንቱን የወያኔ ጀግና እንዳኮላሸው ተገነዘብኩ፤ ጀነራል ጻድቃን ውትድርናው ላይ ጎበዝ እንደነበሩ ሲነገርላቸው ብሰማም ኢትዮጵያዊ ሕዝባዊነት ላይ ግን የተከለለባቸው ነገር እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ችሎታ ሁሉ ሙሉ ሰው እንደማያደርግ ሕያው ምስክር ሆኑልኝ፡፡ አገሬም ትግራይም አሳዘኑኝ፡፡
የቢቢሲው ጁሊያን ማርሻል የጦርነት አላማቸውን ሲጠይቃቸው፣ ሶስት ነገሮች አስቀመጡ፤ አንደኛ መሬቶቻችን ያሏቸው ቦታዎች እንዲለቀቁና ትግራይን ከከበባ ለማውጣት፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ያሉ የትግራይ ተወላጅ እስረኞች እንዲፈቱ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ በኢትዮጵያ መጻኢ እድል ላይ ያተኮረ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያመጣ የሽግግር አካል ተፈጥሮ ውይይት እንዲካሄድ መንግስትን ለማስገደድ ነው አሉ፡፡ ህወሓትና መንግስት እንዲሁም ሌሎች ፓርቲ ነን የሚሉ አካላት ቁጭ ብለው ኢትዮጵያ ስለምትባለው ግዛት ለመወሰን?
ጁሊያን ቀጠለና “ግን እናንተ እንደ አንድ ክልል እነማን ናችሁ የመላ አገሪቷን መጻኢ ዕድል ለመወሰን የሚያስችላችሁ ምን ስለሆናችሁ ነው?” አለ፡፡ እሳቸውም ላሽ እጥፍ አሉና ጥያቄው የሳቸው ብቻ እንዳልሆነ ግን እነሱም አጋር ሆነው ከሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኃይሎች ጋር በመሆን አንዴ ተኩስ አቁሙ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ኢትዮጵያን ምን እናድርጋት አይነት ውይይት ማለታቸው እንደሆነ አብራሩ፡፡
አንድ ከአገራዊ ሥልጣን በዘቀጠ አመራር ችግር በሕዝብ ተቃውሞ የወረደ፣ ክልሉን እንዲመራ ያለውን ኃላፊነት ትቶ ክልሉን ሲጠብቅ የኖረን መከላከያ ሰራዊትን ያጠቃ፣ 1,565 ሰላማዊ ዜጎችን ትግርኛ ተናጋሪ ስላልሆኑ ብቻ የዘር ጭፍጨፋ ያካሄደ ቡድን ከሕጋዊ ማዕከላዊ መንግስት ጋር ከክልሉ አልፎ በሃገር ጉዳይ ላይ ለመደራደር ያላቸውን ድፍረት ስሰማ ሰውየው ጥሩ ወታደር ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል ነገር ግን በፖለቲካው ረገድ ጦር ሜዳ ላይ ከሚማግዱዋቸው ሕጻናት የሚሻል የፖለቲካ አቅም እንደሌላቸው አስተዋልኩ፡፡
ይህን ቀደም ብለው ያወቁት ጠ/ሚ አብይ አሕመድ እኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነን እንጂ ብሔር ብሔረሰቦች የሚለውን አገላለጽ እንደማይቀበሉትና አብጠልጥለው የተናገሩት፤
የ68 አመቱ አዛውንት ወታደር ጻድቃን ብዙም ኢትዮጵያን እንደማያውቋት ገባኝ፡፡ የትግል ጓዳቸው ሳሞራ በተደጋጋሚ ወታደር ተጠሪነቱ ለሕገ-መንግስቱ እንጂ ለፓርቲ እንዳልሆነ ያስቀመጡት እውነታ ጻድቃንን ሽው እንዳለባቸውና ወታደርነት ከጥሩ ፖለቲከኛነት እንደማይከለክል ሳሞራ አስረጅ ሆኑልኝ፡፡ ጻድቃን አንድ ነገር ዘንግተዋል፡፡
ልክ እንደ 1983 ዓ.ም.ቱ አዲስ አበባ ገብተው የሽግግር አካል ተፈጥሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እሳቸውና ድርጅታቸው እንዲያቦካ ያልማሉ፡፡ ያ ዘመን እና ይህ ዘመን ምን ያክል እንደተለወጠ እንኳን አላስተዋሉም፡፡
ህወሓት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ዳግሞ ተቀምጦ ሊወያይ ይችላል ብለው ማሰባቸው በውትድርና እና በፖለቲካ መካከል ያለው ልዩነት እንዳልገባቸውም ግልጽ ነው፤ ምንአልባት የክፋት ባልደረቦቻቸው አገሮች የሰጧቸው ምክር ሊሆን ይችላል፡፡
ጻድቃን ግን አንድ ነገር ስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሚያውቋት በላይ ተለውጣለች፡፡ ይህ ሶስት አመት እና የህወሓት ጦርነት ኢትዮጵያውያንን ምን ውስጥ እንደከተታቸው አልተገነዘቡትም፡፡ አብይ በሶስት አመታት ውስጥ የቆረጠ እና ራዕያቸውን ተቀብሎ ኢትዮጵያን ከፍ ሊያደርግ የሚችል ትውልድ ማፍራታቸውን አላስተዋሉትም፡፡ ጦርነታቸው ከመከላከያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር መሆኑንም ያሰሉት አልመሰለኝም፡፡
የትግራይ ጽንፈኛ ብሔረተኝነት ምርጫ አካሂዶ በማግስቱ ጦርነቱን አስጀምሮ አገር ሲተራመስ ትግራይ ነጻ ወጥታለች ብሎ ለማወጅ የሄደበትን ዝቅጠት ምንነት የህጻናት ወታደሮች ጀነራል ጻድቃን የገባቸው አይመስልም፡፡ ድርጅታቸው አሁንም ጦርነቱን ማቆም የማይፈልገው ያን ያላለቀ ከአለቆቹ የተሰጠውን የቤት ሥራ ለመጨረስ ነው፤ ለዚህ ነው ሁላችንም መነሳት ያለብን፤ የህወሓት ብልግና ቅጥ ሲያጣ ዳር ቆሞ የሚያይ አይኖርም፡፡
አገር እንዳያፈርስ ብለን ህወሓትን ለሃያ ሰባት አመት ታግሰን በሰላም አርፈህ ኑር ብለን ሸኘነው፡፡ አሁን ደግሞ አገር ሳያፈርስ እሱን ለማፍረስ የሚጠብቀንን የቤት ሥራ በብቃት ለመወጣት ሁላችንም ተነስተናል፡፡
ህወሓት በ27 አመታት ውስጥ የሰራውን እናውቃለን፤ እሱ ባፈራረሰው እና ባበላሸው ሜዳ ላይ ቆመን ትግሉን ማካሄድ እና በተለይም የትግራይን ሕዝብ ልብ በሚመልስ ደረጃ ያለብንን የቤት ሥራ ለመጨረስ የሚጠይቀን ሁለንተናዊ አቅም ከባድ ቢሆንም ሸሽተን የማናመልጠው ኃላፊነት ተደቅኖብናልና ሁላችንም እንሰራለን፡፡