Connect with us

የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የትውውቅና የቃለ መሐላ መርሐ-ግብር ተካሔደ

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

ዜና

የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የትውውቅና የቃለ መሐላ መርሐ-ግብር ተካሔደ

የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የትውውቅና የቃለ መሐላ መርሐ-ግብር ተካሔደ

የተሻሻለው የፌደራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 መጽደቁን ተከትሎ አዲስ የተደራጀው የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የትውውቅ እና ቃለ-መሐላ የመፈጸም ሥነሥርዓት ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ተካሔደ፡፡

የጉባኤ አባላቱ ቃለ-መሐላውን የፈጸሙት የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 የጉባኤው አባላት የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ባላቸው ዕውቀትና ልምድ በነጻነት፣ በገለልተኝነት እና በዚህ አዋጅና በአገሪቱ ሕጎች መሰረት በአግባቡ የሚፈጽሙ ለመሆናቸው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት በጉባኤው ሰብሳቢ አማካኝነት በቃለ መሀላ ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው በአንቀጽ 13 በተደነገገው መሠረት ነው፡፡

አጠቃላይ ብዛታቸው 15 ከሆኑት የጉባኤ አባላት መካከል በትውውቅና ቃለ-መሐላ አፈጻጸም መርሐ-ግብሩ ላይ የተሳተፉ የጉባኤ አባላት ቁጥር 14 ሲሆን ቀሪው አንድ የጉባኤ አባል የሕግ የበላይነትን ለማራመድና ለመደገፍ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ስመ-ጥር ግለሰቦች መካከል በጉባኤው አባላት እንደሚመረጥ አዋጁ በሚደነግገው መሠረት ጉባኤው ቀሪውን አባል የሚመርጥ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጉባኤ አባላት የትውውቅ እና የቃለ-መሐላ አፈጻጸም መርሐ-ግብሩ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት እና የጉባኤው ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ነባር እና በአዲስ መልክ የተሰየሙ የጉባኤ አባላትን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ መውጣታቸውን ተከትሎ በርካታ መመሪያዎች በመውጣት ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም ይህም ፍርድ ቤቱን ወደቀጣይ ውጤታማነት ለማሸጋገር የመሠረት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እንደሚያመለክት ገልጸዋል፡፡

ክብርት ፕሬዚደንቷ እና የጉባኤው ሰብሳቢ አክለውም በ2014 በጀት ዓመት በፍ/ቤቶች ሙስናን የሚጸየፍ አሠራር ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

የፌደራል የዳኝነት አስተዳደር ጉባኤ ወደፊት ከፍ/ቤቱ ዳኞች ብቃትና ተጠያቂነት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡

የፌደራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጁ ሶስት ዓላማዎች ያሉት መሆኑን ያስረዱት ክብርት ወ/ሮ መዓዛ እነዚህም ዳኞች ነጻ፣ ገለልተኛና ብቁ ሆነው ሕዝብ እንዲያገለግሉ የማድረግ፤ የፍርድ ቤቱን ተቋማዊ ነጻነት የማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብን አመኔታ የማስመለስ ጉዳዮች መሆናቸውን በመጥቀስ ጉባኤው በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ስለሚያከናውናቸው ተግባራትም አስረድተዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ባለፉት ሁለት ዓመታት የዳኝነት አስተዳደር አዋጁ እንዲወጣ ሲሳተፉ የነበሩ የፍርድ ቤቱ አመራሮችና ዳኞች የአዋጁን መውጣት እንደትልቅ ውጤት እና ስኬት እንደሚመለከቱት አስረድተዋል፡፡
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top