Connect with us

አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ››

አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ››
ኢኦተቤ የመገናኛ ብዙሀን አገልግሎት

ነፃ ሃሳብ

አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ››

አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ››

የፋሽስት ጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን 1928 ዓ/ም በግፍ በወረረበት ወቅት፤ የኢትዮጵ ሕዝብም ሆነ ምድሪቷ ለወራሪው ጠላት እንዳይገዙ በማውገዛቸው፤ ሕዝቡ የአገሩንና የቤተክርስቲያንን ልዕልናና ክብር ለማስጠበቅ ነቅቶ እንዲታገል መሥዋዕት እንዲሆን እውነትን ይዘው በማስተማራቸው፣ በማበረታታቸው፣ በማጽናናታቸው የፋሺስት ጣልያን ወታደሮች ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን አስረው ሐምሌ ፳፪ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም በአደባባይ በጥይት ገደሏቸው፡፡ 

በወቅቱ የጣልያን ጦር አዛዦች አቡነ ጴጥሮስን ለማባበል ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ የፋሽስት ጣልያንን አገዛዝ ተቀብለው ሕዝቡን እንዳይቀሰቅሱ ፣ እንዳያስተምሩ ፣ ለሃገሩ ክብርና ለቤተክርስቲያን ልዕልና እንዳይታገል እንዲያደርጉ ለመደለል የሥልጣን ሃብትና ንብረት ገፀ በረከት አቅርበውላቸዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ግን አልተቀበሉም፡፡ እውነትን በፅናት እንደያዙ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ቸርነት የእመቤታችን ቅዱስት ድንግል ማርያምን ጥበቃ የኢትዮጵያን ክብርና አንድነት መስክረው ሕዝቦቹንም ባርከው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ 

 ይህ ታላቅ ሰማዕትነት በአንድ ወቅት የተከሰተ ታላቅ ሥራ እና ታሪክ ብቻ ሆኖ አልቀረም ትውልዱ እንዲዘክራቸው በተገደሉበት አደባባይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ምሁራን ሁሉ የታሪክ ፀሐፊያኖችና ተመራማሪዎች ደራሲያንና ገጣሚያን ወዘተ.. በርካታ ድርሳናትን ጽፈውላቸዋል፡፡ ስለ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በተለያዬ መገናኛ ብዙሐኑ ብዙ ተገልጿል፡፡ 

 በዚህም በታሪክ ፍጆታነቱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም ዓለማቀፉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የሳይንስ የባህል ድርጅት /UNESCO/ እንዲሁም የዓለም አብያተክርስቲያናት ያቋቋሙት ኮሚቴ የምዕተ ዓመቱ ሰማዕት አድረጎ መርጧቸዋል፡፡ 

 የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ታላቅ ሥራና ተጋድሎ ሰማዕትነትን በመቀበል እንዲመረጡ ባእዳን የሆኑት የባህር ማዶ ሰዎችና የሌሎች እምነት ተከታዮች ተከራክረዋል፡፡ ዓለማቀፋዊ ድርጅትና ታዋቂ ምሁራን ታሪካቸውን ጽፈዋል፤ ተርከዋል፡፡ ጽናታቸውንና ትምህርታቸውን አገልግሎታቸውንና ክብራቸውን ባገኙት መድረክ ሁሉ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እውነተኛ አባትነታቸውን ተጋድሎና ሰማዕትነታቸውን ማንም ሳይጠይቅና ሳያስገድዳቸው ከራሳቸው ልብና ፍላጎት በመነጨ ፍቃደኝነት ጽፈዋል፡፡ 

ሰማዕትነታቸውንም መስክረዋል እውነተኛ ትምህርታቸውን ለመላው ዓለም አስተጋብተዋል፣ አሳውቀዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ታሪካቸውን ጽፈው ቅድስናቸውን ተቀብለው ራሳቸው ተሟግተው አሳውጀዋል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ታሪክና የዘመናት አገልግሎት በረከት ነው፡፡

 የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲን ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ጻድቅ ዘኢትዮጵያ ›› በማለት አጽድቆ /ወስኖ/ ሠይሟል፡፡ በአዲስ አበባ አቡነ ጴጥሮስ አደባበይ የቆመላቸውን ሐውልትም ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ወጪ አውጥታ አስፈላጊው እድሳት እንዲደረግለትና ውበቱ ተጠብቆ ዙሪያው ተከብሮ እንዲቆይ አድርጋለች፡፡ሐውልቱ በአሁን ሰዓት በከረተማው እየተገነባ በሚገኝው ባቡር ግንባታ በጊዛዊነት ከነበረበት ቦታ ተነሰቶ በአ/አ ሙዝየም ግቢ ውስጥ ይገኛል፡፡

  የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሃገረ ስብከት በየዓመቱ ሐምሌ 22 ቀን ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ   የተገደሉበትን (ሰማዕት የሆኑበትን) የመታሰቢያ በዓል በደማቅ ክብረ በዓል ያከብራሉ ፡፡ ለመታሰቢቻውም በተወለዱበት ፍቼ ከተማ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በስማቸው ታንጾላቸዋል፡፡

 ቤተ ክርስቲያኑ ‹‹ የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ገዳም ›› ተብሎ የዘወትር ጸሎትና ምህላ የማይቋረጥበት ፣ የአብነት ትምህርት ቤት፣ እናትና አባታቸውን በሞት አጥተው አሳዳጊ አልባና ድሀ አደግ ሕፃናትን ማሳደጊያና ረዳት የሌላቸው አረጋውያን የሚጦሩበት ተቋም እንደሚኖረው ሀገረ ስብከቱ በምረቃቱ ወቅት/ዕለት ገልጿል፡፡

 ይህ ታላቅ ተግባር እውነተኛው  ሰማዕት በፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የፈጸሙት ታላቅ ሥራና ተጋድሎ  ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ያደርገዋል፡፡ እኒህን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን አባትና ሰማዕት መጪው ትውልድ በየዘመኑ ሁሉ ተግባራቸውን እንዲያውቅ ፤ አርአያነታቸውን እያስታወሰ ፣ እያከበረና እየዘከረ እንዲቀጥል ማስቻል የቤተ ክርስቲን ተግባርና ሐላፊነት መሆኑ ይታወቃል፡፡

 ስለዚህ ዘመን ባለፈ ትውልድ በተተካ ቁጥር ሰማዕቱ ከትውልዱ ኅሊና ሳይርቁ አርአያነታቸው እያስተማረ ዕለት ዕለት እያታሰቡ እንዲኖሩ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በፈተን ውስጥ ሆነው እንኳን እውነት ክርስቶስን የመሠከሩ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን አባተነታቸውን ያረጋገጡ ሰማዕት ናቸውና፡፡ 

 ቀዳሚ ሰማዕት እስጢፋኖስ በድንጋይ የተወገረው ፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ ተዘቅዝቆ የተሰቀለው፤ ቅዱስ ቶማስ ቆዳው በቁሙ የተገፈፈው፤ ለአርዮስ የማየገባውን ሹመት የከለከሉት ተፍጻሚተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ያለፉት ክርስቶስን በአደባባይ በመመስከራቸው እውነተኛ ርትዕተ ሃይማኖት በማስተማራቸው ነው፡፡ በእኛም ዘመንና ትውልድ ያሉ አባቶቻችን በእግዚአብሔር ፍቃድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን አደራና ሐላፊነት ለመወጣት ታላቅ ሰማዕትነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

ይህም ሲባል እንደ ቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን በድንጋይ መወገር፣ በቁማችው  ቆዳቸውን መገፈፍ ወይም ስቅላት ይደርስባቸዋል፣ እንደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በጥይት ይደብደቡ ማለት አይደለም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳስማራቻቸው ቦታና ኃላፊነት ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመኑን የዋጀ ተጋድሎና ሰማዕትነት እንደሚጠብቃቸው ግን ግልጽ ነው፡፡ 

በአገር ውስጥ በተሰማሩበት ቦታ በየሀገረ ስብከታቸው ወንጌል ላልደረሳቸው ሕዝቦች ሁሉ ዳገት ወጥተው ቁልቁለት ወርድው፣ በረሐ አቋርጠው ወንጌልን ማስተማር፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት በገጠርም በከተማም ተጠናክሮ እንዲስፋፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ በየአገሩ በሥራ፣ በትምህርት፣ በተለያዩ ምክንያት በዝርወት ያሉ ኢትዮጵያውያን ምእመናን እናት ቤተ ክርስቲያንን ተስፋ መመኪያ አድርገው፣ ሃይማኖታቸውን ሥርዓታቸውን ጠብቀው፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አጽንተው እንዲኖሩ የማድረግ የማስተማር የማጽናናት የመምከር የአባትነት ተግባራቸውን የመፈጸም ሐላፊነት አለባቸው፡፡ አገርም ሆነች ሕዝቦቿ  በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲጠቁ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው እንዲጸኑ፤ ሠላም አንድነትና ፍቅር እንዲሰፍን፣ አኅት ወንድማማችነት መከባበርና መተሳሰብ እንዲጸና ማስተማር መጸለይ የአባትነት ተግባራቸውና ሐላፊነታቸውም ነው፡፡ 

ለቤተ ክርስቲያን ልዕልና መቆም በልማት ራሷን ችላ እንድታድግና ለህዝቦቿ አለኝታ እንድትሆን ማስተባበርና መምራት ሲፈጽሙት የቆዩት የአባትነት ተግባር እንደሆነ ሁሉ ወደ ፊትም የበለጠ የሚያከናውኑት ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ 

በመላው ዓለም የኢትዮጵያን  ቤተ ክርስቲያን ተስፋ አድርገው ድረሱልን፣ አስተምሩን፣ አጥምቁን በማለት እጃቸውን ዘርግተው ለሚጠብቁ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ብርሃን ይዛ እንድትደርስላቸው በማድረግ በኩል የብፁዓን አባቶቻችን ሚና ጉልህ መሆን ይኖርበታል፡፡

ብፁዓን አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን በመደበቻቸው ቦታ ሁሉ እውነትን ይዘው ዘርፈ ብዙ ሐዋርያዊ ተልኳቸውን መፈጸም፣ ወንጌልን ማስፋፋት የምእመናንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት መጠበቅ ታላቅ ምስክርነትና ሰማዕትነት ነው፡፡ የቀደሙት ቅዱሳን አበው እንዲሁም የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አርአያነትና ዘመኑን የዋጀ ሰማዕትነት ማለት ይህ ነው፡፡ 

ኪዚሁ ጋር እንደሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ለእውነት በመቆማቸው በወራራው ፋሺስት ጣሊያን ጦር በጥቅምት ወር 1929 ዓ.ም በግፍ የተገደሉትን የጐሬውን ሊቀ ጳጳስ ብፅዕ አቡነ ሚካኤልን ማሰብ ይገባል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ልዕልና የቆሙ የእውነት ምስክር ናቸውና፡፡

በአዲስ አበባ ደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን

የምክሐ ደናግል ማርያም ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር

የመረጃ መዛግብትና ኦድዮቪዥዋል ክፍል መካነ ድር ማስተባበሪያ የተዘጋጀ

ሐምሌ 2007 ዓ.ም

(ኢኦተቤ የመገናኛ ብዙሀን አገልግሎት)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top