Connect with us

ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ
ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ነፃ ሃሳብ

ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ

~ ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን!

በሶማሌ ክልላዊ መንግስት በሲቲ ዞን ገርበኢሴ ከተማ  በሶማሊ ንፁሀን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ የክልሉ መንግስት ዛሬ መግለጫ  አውጥቷል፡፡ ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡

***

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ቅዳሜ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በገርበኢሴ ከተማ በንፁሃን ሰዎች ላይ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ፣ በደረሰው ሞት ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት አስመልክቶ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለሟች ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ በሙሉ መፅናናትን ይመኛል።

አሸባሪው የህወሓት ጁንታ በውጪ ጠላት እየተጋለበ በሀገራችን ላይ ጦርነት በከፈተበትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ቆሞ ሀገር ለማዳን እየተረባረበ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ከጁንታው ጋር ግኑኝነት ያለው ኡጉጉማ የሚባለው ቡድን እና የአፋር ልዩ ሀይል ትኩረት ለመበታተንና የጠላትን ሀገር አፍራሽ አላማ ለማሳካት ገርበኢሴ በምትባለው በክልላችን በሲቲ ዞን ስር በምትገኘዉ  ከተማ በመቶዎች የሚቆጠር ንፁሃን ነዋሪዎችን ጨፍጭፈዋል ፤ በርካቶችን አፈናቅለዋል፤ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዘርፈዋል፣ አውድመዋል።

እነዚህ የጥፋት ሀይሎች ከጥቂት ወራት በፊት በአደይቱ ከተማ ላይ ተመሳሳይ አይነት ጥቃት በመፈፀም የበርካታ ንፁሀን ዜጎችን ህይወት የቀጠፉና ሀብት ንብረታቸውን ያወደሙ መሆኑ ይታወሳል።

ጥቃቱን ተከትሎም የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የፌዴራል የፀጥታ ሀይሎች ሀላፊነት ወስደው የነበሩ ሲሆን የአሁኑ አሰቃቂ ጥቃት የተፈፀመው የፌዴራል የፀጥታ ሀይሎች  የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው መሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አሳዛኝ ያደርገዋል።

የአገሪቱ ሁሉም ሀይሎች የውስጥ ልዩነታቸውን ወደጎን ትተው አገር አፍራሽ የሆነው አሸባሪው የህውሓት ጁንታ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በአንድ ልብ ተሰልፈው እያለ የአሸባሪው ጁንታ ተላላኪ የሆነው ኡጉጉማ የሚባለው ቡድን ለአመታት ሲያደርግ የነበረውን ንፁሃንን የመግደል፣ ንብረት የማውደምና የማፈናቀል ተግባር በዚህ ጊዜ መፈፀሙ የውስጥ አንድነታችንን ሸርሽሮ ለማዳከምና የጠላትን አገር የማፍረስ ምኞት ለማሳካት በመሆኑ ይሔ ተግባር ቡድኑ የሶማሌ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጲያ ሕዝብ ጠላት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ሕዝብ ስም የሚነግደው የአሸባሪው የህወሓት ጁንታ ተላላኪ የሆነው ኡጉጉማ የሚባለው የጥፋት ቡድን እና የአፋር ልዩ ሀይል  በዚህ ወቅት በንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ የፈፀሙት ወንድማማች የሆነውን የአፋርና የሶማሌ ሕዝብ በመከፋፈል የጁንታውን አገር የማፍረስ ምኞት ለማሳካት መሆኑን ይገነዘባል ።

በመሆኑም የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ሀገር ተወጥራ ባለችበትና የክልላችን ልዩ ሀይል አገራዊ ጥሪውን ተቀብሎ በግንባር ተሰልፎ ለሀገር አንድነት እየተፋለመ ባለበት በዚህ ወቅት ከአሸባሪው ጁንታ ጋር ትስስር ያለው ኡጉጉማ የሚባለው ቡድን እና የአፋር ክልል ልዩ ሀይል በንፁሃን ነዋሪዎች ላይ የፈፀሙትን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በፅኑ ያወግዛል።

ኡጉጉማ የተባለው የጥፋት ቡድን እና የአፋር ክልል ልዩ ሀይል በንፁሃን ላይ ጭፍጨፋና ከተማ እስከማውደም የደረሰ ጥፋት እየፈፀሙ ያሉት የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን እስትንፋስ ለማራዘም መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የአፋር ክልላዊ መንግሥት እና የፌደራል መንግሥት የፀጥታ ሀይሎች በንፁሃን ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከመድረሱ በፊት በዚህ ተላላኪ የጥፋት ቡድን ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወስዱ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ይጠይቃል።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት  አሸባሪው የህወሓት ጁንታ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በግንባር ተሰልፎ ለሚፋለመው ሀይል የደጀንነት ሚናውን እየተወጣ ጎን ለጎንም  ኡጉጉማ የሚባለው ተላላኪ የጥፋት ቡድን በንፁሃን የክልላችን ነዋሪዎች ላይ የሚያደርገውን ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት ለመከላከል ማንኛውንም ተመጣጣኝ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በአፅንኦት ለመግለጽ ይወዳል።

ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም

የሶማሊ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ጅግጅጋ

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top