“አማን ይነጠፍ አማን ይዘርጋ፣
ተዚህ አንስቶ እስተወለጋ፤”
(ከወሎ/የወረሂመኑ ሐድረኞች ሥነ-ቃል የተወሰደ)
ሀገሬው ጦርነት ብርቁ አይደለም። ከእለት ተእለት የገጠመው ሽኩቻ አላፈናፍን ብሎት ሳለ እናቱን መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣትን ወንድሙን ችሎ ቃል ሊወረውርበት እየሳሳ ዛሬ ግን ክንዱ እየዛለም ቢሆን ሰንዝሮ ለመምታት የኸጀለ ይመስላል።
ማን ይሆን ገላጋይ? ማን ይሆን ዳኛቸው? የታላቅና ታናሽ ግብግብ።
“ማን ወደማን ይሆን የሚገሠግሠው?!
መቸም ያገናኛል መንገድ ሰውና ሰው፤” አለ ጠይሙ ንጉሥ!!
በደሴ ቆይታዬ አንድ ምሽት ላይ የዘጠኝ ዓመት ልጅ የሆነችውን የእህቴን ልጅ እስኪ ዘወር ዞር ብለን እንምጣ ብየ ይዣት ወጣሁ። በወጋችን መሃልም ብላቴናዋ ሚሚዬ ፍቅርና ሥጋት የቀላቀለ በሚመስል ድምፅ፣ በጣፋጭ አንደበቷ እንዲህ አለችኝ።
እክስትዋ “አባዋ’ኮ ሚኒሻ ሊሆን ተመዝግቧል”
“ለምን?!”
“እ… ወታደሮቹ ኸዚያ ኸትግሬ ሀገር ሊዋጉ ስለኸዱ አካባቢውን ሊጠብቅ ነዋ…!!”
ወገን ከዚህ አንደበት በላይ የሚዋጋ የለም። ኸዚያ በኩልስ ምን ይሆን የሚባል?!
… “ገንዘቤዋ እኔ አፈር ልብላ አይ አይይ”
ደረታቸውን እየመቱ እራሳቸውን በሁለት እጆቻቸው ይዘው የሚያለቅሱ የአስፌልቱን ግራ ቀኝ እጃቸውን የሚውያውለበልቡ እናቶች ሞልተውታል።ሀገሩ
ከድምፅ ማጉያ ሞንታርቦ የሚለቀቅ ድምፅ እናቶችን ብርክ ሲያስገባ ፀብ በደላላ ለሚሹት ግን ሠርግና ምላሻቸው ነበር። የወላድ አሣር ማለቂያ የለውም። መቀነታቸውን አጥብቀው የሚጋዙትን ይመለከታሉ።
ሟች’ኳ ለእናት ምድሩ፣ ለእናት ቀድሞም ከቻለ ቀስበቀስ ሥጋውን እየቦጨቀ ለክራሞቷ መትሮ ሊያጎርሳት ባይሆን ለዘለዓለሙ ሕይወቱን ፊሪዳ ሊሠዋላት ቃል አለው። መቸም የማይታጠፍ ሕያው ቃል። ኪዳኑን ላያፈርስ። ሀገሩ ሃይማኖቱ ሆና!!
… ነገር ግን ምን ተብሎ ይነገራል። ጉዳዩ ለወግ የቸገረ ነው። አባቴ እንዴት ሞተ? የት? ማን ገደለው? ቢባል ምን ይሆን ምላሹ?
“የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ”
ወንድምህ ገደለው ነው… ወይስ…?! ይህ የፈሰሰ ደም አንድ ስፍራ ደርቆ ይቀራል ወይ? የሟች ልጆች ላይ የሚያሳድረው ሥነልቦናዊ ቀውስስ ወደዘለአለማዊ ደም መላሽነት አያሸጋግርም ወይ? ጥቁር ከል የሚያለብስ… ቂመኛ ትውልድ እንዳናፈራ። የበቀል አረም እንዳናፀድቅ። ታሪካዊና መሰረቱ የጠነከረ ጥላቻን እንዳናጠላ።
… ከፊት ለፊት እሳት የሚተፋ መሳሪያ አቀባብለው ፉጨትና ጭብጨባ ከኋላ አስከትለው ዘማቾቹ መንገድ ነጎዱ። ይሄኔ፤ “የዘመድ ልፊያ ጨርቅ መጨረስ ነው፤” መባሉ ሐቅ ነው።
የወላድ ማኅፀን በከንቱ አይጨንግፍ። በየማዕዘናቱ ደጋጎች አሉና አምላካቸውም ፀሎታቸውን ይቀበል። ሰላም ለሀገራችን። ሰላም ለሕዝባችን። ሰላም ስለነገ። ሰላም ስለዛሬ። ሰላም ስለወደፊቱ።
“አማን ይነጠፍ አማን ይዘርጋ፣
ተዚህ አንስቶ እስተወለጋ፤”
(ከወሎ/የወረሂመኑ ሐድረኞች ሥነ-ቃል የተወሰደ)