Connect with us

የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሄደ

የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ(Subspeciality in Urology) ስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሄደ
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳ.ኮ

ዜና

የኩላሊትና የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሄደ

የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  የኩላሊትና  የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ(Subspeciality in Urology) ስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር  አካሔደ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  የኩላሊትና  የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ(Subspeciality in Urology ) ስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር   ባዛሬዉ ዕለት በጥበበጊዎን ግቢ አካሔደ፡፡ የድሕረ-ስፔሻሊቲ ፕሮገራሙ የተጀመረዉ በሕክምና ትምህርት ቤት በቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ስር ሲሆን ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

በማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩ  የኮሌጁ የአካደሚክና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ደ/ር መለሰ ገበየሁ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡  ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸዉ የድሕረ-ሰፔሻሊቲ ፕሮግራሙ የተጀመረዉ የስርዓተ-ትምህርት ቀረጻና ግምገማ በማድረግ እንዲሁም የቀዶ ሕክምና ቁሳቁሶችን፣ ሳይከፈት ሕክምና መስጠት የሚያስችሉ ቀጫጭችን ቱቦዎችንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግባቶችን በማሟላት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር መለሰ አክለዉም የኩላሊትና  የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ የኮሌጁ ሁለተኛ  ፕሮግራም መሆኑንና ቀደም ሲል በማሕጸን ካንሰር የመጀመሪያዉን  ድሕረ-ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ስልጠና መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ 

የዛሬዉ ፕሮግራምም በሕክምና ትምህርት ክፍል 17ኛዉ በኮሌጅ ደረጃ ደግሞ 35ኛዉ ፕሮግራም መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቱ በ1 ድሕረ-ስፔሻሊቲ፣በ8 ስፔሻሊቲ፣ በ2 ማስተርስና በ5 ቅድመ-ምረቃ በድምሩ በ16 ፕሮግራሞች  ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝና በዛሬዉ ዕለት የተጀመረዉ 2ኛዉ ድሕረ-ስፔሻሊቲ በመሆኑ በትምህርት ቤቱ ስር የሚሰጡትን ፕሮግራሞች ቁጥር ወደ 17 ከፍ ያደርገዋል ሲሉ ዶ/ር መለሰ ተናግረዋል፡፡ ይኸዉም ኮሌጁ በ13 ዓመት ዉስጥ በ35 ፕሮገራሞች ትምህርት መስጠቱ ትልቅ እምርታ እንደሆነ ዶ/ር መለሰ ገልጸዋል፡፡ 

ኮሌጁ በዚህ ደረጃ ለስኬት የበቃዉ ከዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ፣ የኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጁ የሰኔት አባላት፣ መምህራንና አጠቃላይ ሰራኞች ከፈተኛ የሆነ የስራ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እንደሆነ በመግለጽ ያላቸዉን ምስጋና ዋና ዳይሬክተሩ አቅርበዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸዉ በሚቀጥሉት ወራት ሌሎች የድሕረ-ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን ለማስጀመር ኮሌጁ ቅድመ-ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ በተለይም የሳንባና ጽኑ ሕሙማን ድሕረ-ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ከአንድ ወር በኋላ ለማስጀመር የቁሳቁስና መሰል ግባቶችን በማሟላትና የስዐዓተ-ትምህርት ቀረጻ በማድረግ  ኮሌጁ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር መለሰ ጠቁመዋል፡፡ 

የድሕረ-ስፔሸሊቲ ፕሮግራችን ማስጀመር ከጤና ሚኒስቴርና ከሳይንስና ፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዘርፉ ላይ ካስቀመጡት አቅጣጫ ጋር አብሮ የሚሄድ በመሆኑ ኮሌጁ በትክክለኛ መስመርና ስኬት ላይ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በድሕረ-ስፔሻሊቲ ደረጃ ባለሙያወችን አሰልጥኖ ለማሕበረሰቡ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ተገቢ መሆኑን በማስጀመርያ መርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንትና የጥበበጊዎን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቦርድ አባል አቶ ብርሃኑ ገድፍ ገልጸዋል፡፡ 

አቶ ብርሁኑ አክለዉም ስርዓተ-ትምሕርት በመቅረጽ፣ የሕክምና ቁሳቁሶችን በመግዛትና ከአጋር አካላት ጋር ትብብር በመፍጠር የሕክምና አገልግሎቶችን ማሻሻል አስፈላጊ ነዉ ብለዋል፡፡  ኮሌጁ  ሁልጊዜም የሚያኮራ ስራ አየሰራ እንደሆነና በዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ አመራርም ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠዉ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡ 

በሀገር ደረጃም ባሕር ዳርን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግና በዚህም ወደ ዉጭ ሀገር የሚሄዱትን ታካሚዎች ለማስቀረት ለኮሌጁ የሆስፒታል ማስፋፊያ 138 ሄክታር መሬት ከክልሉ መንግሰት እንደተሰጠ አቶ ብርሀኑ ጠቁመዋል፡፡ ይሄ እንዲሆን የኮሌጁ ከፍተኛ አመራር እጅግ ከፍተኛ ስራዎችን እንዳከናወነ በመግለጽ አቶ ብርሀኑ የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት አስተላልፈዋል፡፡

ቀጥሎ የተካሄደዉን ዉይይት የመሩት የኮሌጁ ድሕረ-ምረቃና ተከታታይ ትምህርት ዳይሬክተር ዶ/ር ሀይለማሪም አወቀ ሲሆኑ በንግግራቸዉም በኢትዮጵያ ደረጃ በዘርፉ የሰለጠኑ  ባለሙያዎች 24 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ከአዲስ አበባ ዉጭ የሚገኙት ደግሞ 5 ብቻ መሆናቸዉን ገልጸዉ ይህ ፕሮግራም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መከፈቱ የነበረዉን ከፍተኛ የሆነ የሰለጠነ የሰዉ ሀይል እጥረት በመቀነስ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡን በእጅጉ እንደሚያሻሽለዉ አብራርተዋል፡፡

በማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ እንግዶች ዶ/ር አንዷለም ደነቀ (Urologist) እና ዶ/ር መሳይ መኮነን (Urologist) ተገኝተዉ ሀሳባቸዉንና ልምዳቸዉን ለተሳታዎች አካፍለዋል፡፡ በተለይም ደ/ር አንዷለም ኮሌጁ ማስተማር ሲጀምር በተጋባዥ መምህርነት መሳተፈቸዉን ገልጸዉ “የኮሌጁን ለዉጥ በዓይኔ አይቸዋለሁ፡፡ 

የሕክምና አገልግሎት በትምህርት ካልታገዘ ከፍተኛ ለዉጥ አይመጣም፤ የዚህ ኮሌጅ ታምራዊ ለዉጥ ሊመጣ የቻለዉ በትምህርት ስለታገዘ ነዉ” ሲሉ ሃሳባቸዉን ለተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡  

ሁሉም ነገር ከተሟላ በኋላ ነዉ መጀመር ያለበት ብሎ ማሰብ ስልጠናዎችን ለማስጀመር አስቸጋሪ መሆኑን ደ/ር አንዷለም ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም  የኩላሊትና  የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ አስፈላጊና ከፍተኛ የሆነ አቅም እንደሚፈጥር ጠቅሰዉ ከአጋር አካላት ጋር መስራት እንደሚያስፈል ዶ/ር አንዷለም ጠቁመዋል፡፡  

ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ መስራት ካልተጀመረ ማደግ አስቸጋሪ እንደሆነ በመርሀ-ግብሩ የተገኙት የዩሮሎጂ ዩኒት ሃላፊ ዶ/ር ጌታቸዉ ወንድም (Urologist) አብራርተዋል፡፡ ለነበራቸዉ ድጋፍም ከፍተኛ አመራሩን ዶ/ር ጌታቸዉ አመስግነዋል፡፡

ፕሮግራሙ የተጀመረዉ በዘርፉ የሰዉ ሀይል እጥረት ስላለና የሕክምና አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ለመጨመር እንደሆነ  የኩላሊትና  የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ ሰልጣኞች ዶ/ር መኳንንት ይመርና ዶ/ር አበበ አሳየ ተናግረዋል፡፡  ለትምህርት ስኬት የሰልጣኞች ቁርጠኝነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ስለተመዘገበዉ ስኬት ከፈተኛ አመራሩን አመስግነዉ ለወደፊትም በዚሁ ድጋፋቸዉ እንዲቀጥል ሰልጣኖቹ አሳስበዋል፡፡

የሕክምና ግባቶችን ከሟሟላት በተጨማሪ የሕትመት ስራዎች መሰራት እንዳለባቸዉ የጥበበጊዎን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዘበናይ ቢተዉ አሳስበዉ ለሰልጣኞቹ፣ ትምህርት ክፍሉ፣ለትምህርት  ቤቱ እንዲሁም ለኮሌጁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት አስተላልፈዋል፡፡

የቀዶ ጥገና ትምህርት ክፍል 46 መምህራን ያሉት በሰዉ ሀይል ብዛት ትልቅ ክፍል በመሆኑ የሚከፈቱ ፕሮግራሞችን በስኬት ለማከናዎን እንደሚያስችል የትምህርት ክፍሉ ሀላፊ ዶ/ር ደስታዉ ቢያድጌ አስገንዝበዋል፡፡

ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተደራጀ፣ ባለራዕይና ትልቅ ሕልም ያለዉ ተቋም ነዉ ሲሉ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብሩ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካደሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ ገልጸዋል፡፡ 

በንግግራቸዉም የኩላሊትና  የሽንት አካላት ቀዶ ሕክምና ድሕረ-ስፔሻሊቲ  ወደ ዉጭ የሚሄደዉን ታካሚ በማስቀረት ጉልህ ሚና ስለሚጫወት መጀመሩ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር እሰይ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር እሰይ አክለዉም ስለ ኮሌጁ የእድገትና የመስፋፋት ፍላጎትና እቅድ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልሉ መንግስትና የክልሉ ጤና ቢሮ ጥሩ መረዳት እንዳላቸዉ ጠቅሰዋል፡፡(ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳ.ኮ)

 

 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top