የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጠ
በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በሀገር ላይ በፈፀመው እጅግ ዘግናኝ እና አረመኔያዊ ክህደት ሳቢያ አደብ እንዲገዛ እና ሸሽቶ የቀበሮ ጉድጓድ እንዲገባ መደረጉ ይታወቃል።
ይህ ቡድን የቀበሮ ጉድጓዱም ሆኖ ዘወትር በሚታወቅበት የቅጥፈትና የውሸት ፕሮፖጋንዳ ህዝብን የማሳሳት ከዚያም አልፎ ለአለም ህዝብ የውሸት ወሬ በመንዛት የነበረውን እንዳልነበረ፣ ያልነበረውን እንደነበረ የማድረግ የማወናበድ ዘመቻውን አጧጧፈው።
ለህግ ማስከበርና ህልውና ዘመቻው የተሰማሩ የኢትዮጵያ ጀግኖች ለወንድም የትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ ለመስጠትና ወቅቱ የእርሻ ጊዜ በመሆኑ እርሻውን እንዲያርስ በሚል አርቆ አሳቢነት አካባቢውን ለቀው በመውጣት መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም ሁሌም ፀረ ህዝብ የሆነው ይህ ቡድን ህዝቡ የጥሞና ጊዜ እንዳያገኝ የተኩስ አቁም አዋጁን በመጣስ ዳግም ጦርነት ከፍቷል።
ይህ አረመኔ ቡድን አረመኔያዊነቱን ይበልጥ ለማሳየት ገና ጨዋታ ያልጠገቡ የትግራይ እናት ልጆች ህፃናትን በማሰማራት ለውጊያ አሰለፈ። ቡድኑ የሚከተለው የሴራ ፖለቲካ ይባሱን በማፋፋም ተዳክሞ ከወደቀበት አፈር ልሶ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ህልሙን ለማሳካት የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ መፏጨር ይዟል።
ይህ እኩይ ቡድን ከዚህ ያልተገባ አረመኔያዊ ተግባሩ እንዲታቀብና በሽታው እንዳይዛመትም ስርአት የማስያዝ ስራ ወንድም ትግራይ ህዝብን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀላፊነት ነው የሚሆነው።
እንደምናውቀው እናት ሀገር ኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች በውድ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ሉአላዊነቷን አስከብራ ነው ዛሬ ላይ የደረሰችው፣ አሁንም ቢሆን እኚህ ለሀገር ፀር የሆኑ ሰላም ፈፅሞ ሊገባቸው ያልቻለ፣ ቅድሚያ ለሀገር ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ያቃታው እኩይ ቡድን በሚገባው ቋንቋ በማናገር እንደ መዥገር ከወንድም ትግራይ ህዝብና አጠቃላይ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የመገላገል ስራ ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል።
መንግስታችን ሁሌም ቅድሚያ ለሰላም፣ ቅድሚያ ለልማት፣ ጦርነት አይበጀንም፣ ክላሽ ሳይሆን ዳቦ ነው ሚያስፈልገን ቢልም ይህ ቡድን አሻፈረኝ በማለት ይሄው ዛሬም ድረስ ያገኛትን መሿለኪያ ቀዳዳ በመጠቀም በህዝብ ሉአላዊነት ላይ ሴራ በመሸረብ፣ በይፋም “ኢትዮጵያን እንበታትናለን” ብለው በመፎከር፣ ከፉከራም አልፈው በአንዳንድ ቦታዎች ጥቃት በማድረስ ላይ ስለሚገኝ ይህ የጭካኔ ጥግ የደረሰ ሴራውን በጋራ ልንመክት ይገባል።
በሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ፈፅሞ የማይደራደረው ህዝባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከአያት ከቅደመ አያት የተረከብነውን አደራ በአግባቡ በመወጣት ይህ በመሀላችን የተገኘውን ደዌ የማጥፋትና ሀገራችንን ሰላሟን የመመለስ ኃላፊነታችን እንወጣ።
እናት ኢትዮጵያ ከፈጣሪ በታች በውድ ልጆቿ ጥረትና ትጋት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሃምሌ 09/ 2013
ሰመራ